>
2:25 am - Tuesday May 24, 2022

የአገር ባለውለታው ፊታውራሪ አመዴ ለማ!?!  (ብሩክ አበጋዝ)

የአገር ባለውለታው ፊታውራሪ አመዴ ለማ!?! 

 

ብሩክ አበጋዝ
…… በሃይማኖት ብዙ አክራሪ (ፋናቲክ) አይደለሁም፤ ሰወችን የምወደው ሰው በመሆናቸው ብቻ ነው። የሰው ልጅ ሆኖ የተፈጠረ አእምሮ ያለው አካባቢውን በመቀየር ከዚህ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለ ስለሆነ ለሰው ልጅ ከፍተኛ የሆነ ክብር አለኝ እንጂ በሃይማኖት ምክንያት ሰውን ከሰው የማበላልጥ አይደለሁም።
.
አንድ ወቅት <<ምስራቅ አፍሪካ>> የሚል መጽሀፍ ይጻፋል፤ ነቢዩ መሀመድን የሚነቅፍ ነበር። መጽሀፉን ካነበብኩት በኋላ ለአንዳንድ ወገኖቼ ነገርኳቸው፤ በተለይም ለሀጂ መሀመድ አሚን የወሎ ጠቅላይ ግዛት ቃዲን አማከርኳቸው። <<ይኼማ አገራችንን ጉዳት ላይ የሚጥል ነው፤ ከውጭ እንደምንሰማው የሃይማኖት ጦርነት በዚህ መልኩ ነው የሚቀሰቀሰው>> አሉ። ሁኔታውን ለወሎ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ለደጃዝማች መንገሻ ወ/ጊዮርጊስ ገለጽንላቸው [የራሳቸው የፊታውራሪ አመዴ ዘመድ ናቸው]። <<የመጻፍ ነጻነት ስላለ ምን ማድረግ እችላለሁ>> የሚል መልስ ሰጡን።
.
ከዚያ ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቴሌግራም አደረግን፤ ሰወችም ወደ መቀለና አዲስ አበባ ተላኩ። ግርማዊነታቸውም <<እንዲህ ዓይነት የሃይማኖት ብጥብጥ የሚያመጣ ነገር መጻፍ አልነበረበትም>> አሉና የመጽሀፉ ስርጭት እንዲታገድ ተደረገ። ጸሀፊውም ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር ተደረገ፤ ከዚያ በኋላ ሰላም ሆነ። በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አወደሰብ ፕሮግራም ላይ የሕይወት ታሪኬን ስናገር ስለ ሃይማኖት ጉዳይ ፈጽሞ አላነሳሁም ነበር። አንዳንድ ሰወች እየመጡ <<አንተ እስላም ሆነህ ለምን ስለ እስልምና ሃይማኖት እያጎላህ አልተናገርክም>> አሉና ወቀሱኝ።
.
<<እኔ ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ባለው መልኩ [ከተጠየቅኩት ጥያቄ አንጻር] እናገራለሁ እንጂ ሳልጠየቅ ሃይማኖትን እያነሳሁ ሕዝብን አልከፋፍልም። አይ ካላችሁ ደግሞ ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ሲኖረው ወደፊት እናገር ይሆናል>> አልኳቸው። በዚህ የሃይማኖት ጉዳይ የምጨምረው ትውስታ አለ፤ ወደ ፓርላማ ከገባሁ በኋላ የ1951 የፍትሀ ብሄር ሕግ ቀረበ። በሕጉ ቁጥር 3347 ላይ <ከዚህ በፊት በልማድ ወይም ተጽፈው ይሠራባቸው የነበሩ ደንቦች ካሉ ይህ የፍትሀ ብሄር ስለተተካ ተሽረዋል>> ይላል። ወደ ፓርላማ ተመርጠን ከገባነው ከ210 ሰው ውስጥ እስላሞች ወደ 35 ገዳማ እንሆናለን።
.
<<ይህ አንቀፅ ለቃዲ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ስልጣን ስለሚቃረን ባይሆን ለቃዲ ፍርድ ቤት የተሰጠው እንደተጠበቀ ነው የሚል አንቀጽ ወይም ዐረፍተ ነገር ይግባበት>> ብለን የምክር ቤቱን የጋራ ስብሰባ ለሚመሩት ፕሬዝዳንት አቀረብን። እሳቸውም ጉዳዩን በፓርላማው አሠራርና ሥርዓት ተነጋግረው ውሳኔ እንዲሰጥበት አቀረቡና ከ210 ውስጥ [በአብላጫ ድምፅ] ከተደገፈ ይገባል አሉ። በድምጽ እንደምንበለጥ ስላወቅነው ምክር ቤቱን ለቀን ወጣን። ወዲያውኑ ጉዳዩን ጃንሆይ ይሰማሉ። የኢትዮጵያ እስላም ከዳር እስከ ዳር ተንቀሳቀሰ። እሳቸውም አፈ ንጉሥ እሸቴ ገዳን አስጠርተው <<እስኪ ይኼንን ጉዳይ ጠለቅ ብለህ ተመልከተውና ሰላም የሚፈጠርበትን ሁኔታ ፈልግ>> ብለው አዘዙ።
.
አፈ ንጉሥ እሸቴ ገዳም ሁኔታውን ካጠኑ በኋላ <<እውነታቸውን ነው ጉዳዩ በኋላ ብጥብጥ ያስከትላል>> አሉ። ከዚያ ቀደም ሲል ለቃዲወች በነጋሪት ጋዜጣ ቁጥር 62 የተሰጠው ስልጣን ሳይሸራረፍ እንዲጠበቅ የሚል ሰርኩላር ተሰራጨ። በዚህ መልኩ ለሃይማኖት መከበር ያደረግሁት አስተዋጽኦ ለአንድ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላምና በእስልምናና በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ፀንቶ ለሚኖረው ወንድማማችነት በማሰብ ነው። የሃይማኖት ጉዳይ ካነሳን ያካሄድኳቸው ሌሎች እንቅስቃሴወችንም መጥቀስ ይቻላል።
.
ጊዜው 1958 መጨረሻ አካባቢ ነው፤ ምክር ቤቱ ሰኔ ላይ ሲዘጋ ታላቁ ቤተ መንግስት እየሄድን ጃንሆይን እንሰናበታለን። የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጀነራል ዓቢይ አበበ ግርማዊ ጃንሆይ ዘንድ ይዘውን ቀረቡ።
.
<<እስኪ ያን የወሎ ልጅ ጥራው>> አሉ ጃንሆይ፤ እኔም ቀረብኩና እጅ ነሳሁ።
 .
<<አንተ እንዲያው ወሎ! ወሎ! እያልክ ያለ ወሎ ሌላ አታውቅም?>> አሉኝ።
.
<<ግርማዊ ሆይ ኢትዮጵያ ነው የምለው>> አልኩና መልስ ሰጠሁ።
.
<< አሁን ኦጋዴን ብንልክህ ትሄዳለህ?>> አሉ።
.
<<ለምን አልሄድም? ግርማዊ ሆይ!>> አልኳቸው።
.
<<በል ከሠዓት በኋላ ትሄዳለህ>> አሉ።
.
<<እሺ ግርማዊ ሆይ ጠመንጃ ይስጡኝ>> አልኩኝ።
.
<<ጠመንጃ ምን ያደርግልሃል?>> አሉኝ።
.
<<እንዴ ግርማዊ ሆይ ወንድ ልጅ ኦጋዴን ሲሄድ እንዴት ያለ ጠመንጃ ይሄዳል?>> አልኩኝ።
.
ደርግ ወሰደብኝ እንጂ አንዲት የእጅ መትረየስ ሰጡኝ። መሳሪያውን የተቀበልኩት ከፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ  ከጀነራል ድረሴ ዱባለ ነበር። ያቺን መትረየስ ያዝኩና ምሳየን ልበላ ወደ ቤቴ ስገባ፤ <<ደግሞ ምን ይዘህ መጣህብኝ>> አለች ባለቤቴ፤ <<ኦጋዴን እንደሄድ ስለታዘዝኩ ግርማዊ ጃን ሆይ የሰጡኝ ጠመንጃ ነው>> አልኳት። ከሠዓት በኋላ በዶ/ር ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ የሚመራ ከፈረንሳይ 2፣ ከእንግሊዝ 3 መሀንዲሶች፣ የኦጋዴን አዛዥ ጀነራል አበበ ገመዳና እኔ ያለንበት ቡድን በአውሮፕላን ተጉዘን ድሬደዋ ራስ ሆቴል አዳር አደረግን።
.
ዶ/ር ኃይለጊዮርጊስ ከዚህ ቀደም አያውቁኝም፤ በተለይም እስላም መሆኔን። ሁላችንም አብረን እንበላለን፣ አብረን አንጠጣለን ጉዟችንን ወደ ጎዴ አድርገን ቀጠልን። የጉዟችን ዋናው ምክንያት የዛሬዋን ጎዴ ከተማን ለመቆርቆር ነበር። ጎዴ ስንደርስ ዶ/ር ኃይለጊዮርጊስ ፕላናቸውን አወጡና ቤተ መንግስቱ፣ አስተዳደሩ፣ የመንግስት መስሪያ ቤት ቢሮዎች፣ ቤተ ክርስቲያኑ የሚሰሩባቸውን ቦታወች በዝርዝር አሳዩ። በዚህን ጊዜ አንደኛው መሀንዲስ <<ይኼ የሱማሌ ጎረቤት የሆነ ሕዝብ እስላም ስለሆነ ለፖለቲካውና ለአስተዳደሩ ጥሩ ስለማይሆን መስጊድና መድረሳ ት/ቤት ያስፈልገዋል>> አላቸው።
.
<<ሕዝቡ ዘላን ስለሆነ ወደ ፊት እየተጠመቀ ክርስቲያን ይሆናል እንጂ መስጊድና መድረሳ አያስፈልገውም>> አሉ። እኔ ይኼንን ስሰማ ምንም አልተናገርኩም። አባባሉ በአእምሮየ ቢቀረጽም እኔ የተላኩበት ዓላማ ሕዝቡ አካባቢውን እንዲያለማ ለመቀስቀስ ስለሆነ ዝም አልኩ። ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ልማቱን በተመለከተ በጋዜጣ ላይ አንድ ጽሁፍ ጻፍኩ። <<ዋቢሸበሌ መሀል ለመሃል ሰንጥቆት የሚሄድ፣ ግራና ቀኙ የዳበረ መሬት፣ ባለሙያ ሴት እንደምትጠምቀው ጠላ ድፍርስ ውሀ የሚንኳለልበት [ለም አፈር ያለው ለማለት ነው] ለመስኖ አመቺ የሆነ መሬት ስለሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደዚያ ሄደህ ያንን ተፈጥሮ ያዳበረውን መሬት አልማ።>> የሚል ነበር።
.
ጃንሆይ የፍልሰታን ጾም (ነሀሴ 1 – 15) የሚያሳልፉት ድሬደዋ ነው፤ እዚያው እያሉ ለጽህፈት ም/ሚኒስትር ለአቶ ሰሎሞን ወ/ማርያም ስልክ ይደውሉና <<ያ ልጅ ዶ/ር ኃይለጊዮርጊስ ያቀረበውን ፕላን እንዴት እንደታዘበው ቶሎ ጠይቅና ዛሬውኑ ሪፖርት አድርግልኝ>> ይሏቸዋል። እሳቸውም ከምኖርበት አካባቢ መርካቶ መጡና ጠየቁኝ፤ እኔም በዚህ ጊዜ ለካ ጃንሆይ የላኩኝ ለስለላ ኖሯል የሚል ስሜት ተሰማኝ።
 .
<<ፕላኑ ትክክል ነው ነገር ግን መሀንዲሱ እንዳለው ያ አገር እስላም ስለሆነ፣ ጎረቤቱም ሱማሌ ስለሆነ ችግር እንዳይመጣ መድረሳና መስጊድ ያስፈልገዋል>> በማለት በጽሁፍ ሀሳቤን አቀረብኩ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሬዲዮ ስከፍት <<ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ በጎዴ 90 ሺህ ብር የሚያወጣ መስጊድ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ>> የሚል ዜና ሰማሁ።
.
አንድ ወቅት ደግሞ የአትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እስራኤል ዴር ሰልጣን ያለውን ገዳም ግብጾች እንወሰዳለን ሲሉ አቡነ ቴዎፍሎስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቃውሞውን እንዲያሰማ በጠየቁት ሕዝባዊ ሰልፍ በመቀስቀስ ድጋፌን አሳይቻለሁ። በ1966 ከፓርላማ ወጥቼ የራያና ቆቦ አውራጃ ገዥ በነበርኩበት ጊዜ ቄሶች ወደ ቢሮየ መጡና <<ባላገሩ ፍርቅ ስለከለከለን ረሀብ መሞታችን ነው>> አሉና አቤቱታቸውን አቀረቡ። እሁድ ቤተክርስትያን ድረስ ስለምመጣ እዚያው ጠብቁኝ አልኳቸው። እነሱም ግራ ገብቷቸው ቅር ተሰኝተው ሄዱ። ከዚያ የከተማውን ሹም አስጠራሁና <<የአውራጃው ገዥ እሁድ ቤተክርስትያን ስለሚመጣ አንድም ሰው እንዳይቀር በጥሩምባ ይቀስቀስ>> የሚል ትዕዛዝ አስተላለፍኩ።
.
እሁድ ስብሰባው ከመድረሱ በፊት እስላሞቹ ተሰብስበው ወደ ቢሮዬ መጡና <<አንተም እንደ እከሌ ልታደርገን ነው?>> በማለት ወደ ቤተክርስትያን መሄዴን ተቃወሙ። እኔም <<በዚያች እለት አንዳችሁም ሳትቀሩ በስብሰባው እዚያው ቤተ ክርስቲያን መጥታችሁ እንድታዳምጡ>> አልኳቸው። የከተማውን ሹምም <<እስላሞችም ከስብሰባው እንዳይቀሩ አስነግር>> አልኩት። እሁድ እለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ስሄድ ቤተ ክርስቲያኑ ሰው በሰው ሆኗል። አንዲት ከበግ ፀጉር የምትሰራ ምንጣፍ ላይ[ስጋጃ] ወንበር አስቀምጠው ስገባ መቆሚያ ዘንግ ሰጡኝና ንግግሬን ጀመርኩ።
.
<<የሃይማኖት መሪ ማለት ምን ማለት ነው? የሃይማኖት መሪወች ሰወችን ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚመሩ፣ ከፈጣሪ ጋር የሚያወዳጁ፣ ሕጻናትን የሚያስተምሩ፣ በሀገር ላይ መቅሰፍት እንዳይመጣ ፀሎት የሚያደርጉ አባቶች ናቸው። ስለዚህ የእናንተ የሃይማኖት መሪወች ሌት ከቀን እያገለገሏችሁ ለምን ለልመና ከተማ እንዲገቡ ታደርጓቸኋላችሁ? ለቄሶች ፍርቅ ስጡ እንዳልል መሬቱ ላይ ሰው የለም፤ ጊዜው የረሃብ ነው፣ እናንተ እየበላችሁ እንዴት የሃይማኖት አባቶች ይቸገራሉ? በዚህ ካየነው እስላሙም ክርስትያኑም ሃይማኖታችሁን አላከበራችሁም ማለት ነው። እኔ አንድ ጊዜ እንግሊዝ ሀገር ሄጄ ፓርላማውን ከጎበኘሁ በኋላ ሴንትፖል ወደሚባል ቤተክርስትያን ሄድኩ። ወደ ቤተክርስትያኑ የሚገባው ሰው ከበሩ ላይ እንደ ገንዳ ሆና ከተሰራች ነገር ሳንቲም ይጨምርባታል። ቤተክርስትያኗ ከምታገኘው ሌላ ገቢ ላይ ያንን በገንዳው የሚጠራቀውን ገንዘብ ጨምራ ራሷን ታስተዳድራለች። ስለዚህ ሁላችሁም ትንሽ፣ ትንሽ ብትሰጡ እስላሙም የእስልምና ሃይማኖት አባቱን፣ ክርስትያኑም የክርስትና ሃይማኖት አባቱን ሊያስተዳድር ይችላል። በሉ አሁን መጀመሪያ አንድ ሸማ ይነጠፍ።>>
.
አልኩና በቅድሚያ እኔ 10 ብር አስቀመጥኩ፤ ከዚያ ሰው ሁሉ ያለውን አዋጥቶ ብዙ ብርና ሳንቲም ተሰበሰበ። በጣም የደነቀኝ  ግን አንድ በሽተኛ እየተንቀጠቀጠ መጥቶ የያዛትን 25 ሳንቲም እዚያች ሸማ ላይ ማስቀመጡ ነበር። ከዚያ በኋላ ሁሉም ሃይማኖት በየወሩ የሚከፍለውን በጀት ደልድሎ ተመለሰና ችግሩ ተቀረፈ።……
——————————
አቤቱ ፈጣሪ እንደ ፊታውራሪ አመዴ ለማ ዓይነት ሩቅ ዓላሚ፣ ለወገን ተጨናቂ፣ ልባቸው ለአድሎ የማትፈቅድ ሰወችን አበርክትልን። አላህ የልፋትና የቅንነታቸውን ብዛት አይቶ ፊታውራሪ አመዴን በበረከቱ ይዳስልን አሚን።
Filed in: Amharic