ለ እግዜር የተላከ ደብዳቤ!!!!
አሌክስ አብርሀም
እንደምነህ እግዜር
ሰማይ ቤት እንዴት ነው
እመጣለሁ ብለህ ቆየህሳ ምነው?
እኛማ…
ለእልፍ አዕላፍ አለቃ
ማመልከቻ ፅፈን፣
ለወፈ ሰማይ ህዝብ
መድረክ ላይ ለፍፈን፣
ፆለት ቤታችንን
እኛው ላይ ቆልፈን፣
የምድር አተካራ
ህግጋቱን አልፈን
ደብዳቤ ላክንልህ፤
አይንህን ካየነው
ሁለት ሺህ ዘመን
እንደቀልድ አለፈ
የመምጣትህ ተስፋ እየኮሰመነ መቅረትህ ገዘፈ…
እንደውም እንደውም…
“በእመጣለሁ ተስፋ
ሁለት ሺህ ዘመን
ገትሮን ከጠፋ፣
በቀጠሮው ሰአት
መምጣት ከተሳነው፣
እግዜር አበሻ ነው”
እያሉ ያሙሃል…
እኔ ምን አውቃለሁ…
አመስግነው ሲሉ እልልታ የማቀልጥ፣
ቃሉን ስማ ሲሉኝ…ሰባኪው እግር ስር በደስታ እምቀመጥ፣
‘እግዚኦ! በሉ’ ሲባል…እንባዬን የማፈስ፣
ሃሌ ሉያ ሲሉኝ…በሳቅ ልቤ ‘ሚፈርስ፣
ምናምኒት እውቀት ውስጤ ያልፀደቀ፣
እንበረከክበት ጉልበቴ ያለቀ፣
እኔ ምን አውቃለሁ…
ግን አንተ ደህና ነህ?
ከምር እንደሚያሙት ምፅአት ቀረ እንዴ?
የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አትከፋም አንዳንዴ!
የሆነስ ሆነና ሰማይ ቤት እንዴት ነው?
አብረሃም ሰላም ነው…?
እዛስ ቤት ገነባ ዛሬም በድንኳን ነው?
እኛማ ይሄውልህ…
በቤት ኪራይ ችንካር እየተሰቀልን፣
“ኤሎሄ” እንላለን ጎጆ እንድትጥልልን….
ወደላይ ገነባን ወደጎን አሰፋን፣
ወደላይም ከላይ ወደጎንም ከጎን
እንደጉድ ተገፋን…
ቤት ለእንግዳ ማለት ጭራሹኑ ጠፋን!!
አባታችን ሙሴ እንዴት ነው ለክብሩ፣
ውቂያኖስ መክፈያው ደህና ናት በትሩ?
እኛማ ይሄውልህ…
እንጀራ ፍለጋ ባህር ስናቋርጥ፣
የተስፋዋን ምድር አሸዋ ሳንረግጥ፣
የትም ውሃ በላን የትም አሳ ላሰን፣
ንገርልንና በትሩን ያውሰን…
እናልህ እግዜር ሆይ…
ከተስፋዋ ምድር ወደሌላ ተስፋ አለን እየኳተን
መሄጃው ሲገርመን መመለሻ መንገድ መቆሚያ ቦታ አጥተን…!
ላባታችን ሙሴ እንደምትልልን..
“የመሄድ ዘመን ነው ባህር የመሻገር
ዱላህን ላክልን” ብሎሃል በልልኝ…
“ሰማይ ቤት እንዴት ነው?
ዳዊትስ ደህና ነው?
ዛሬም ይዘምራል?
ዛሬም ይፎክራል?
ሰላም ነው ጠጠሩ?
ሰላም ናት ወንጭፉ?
እዛስ አቅል ገዛ ጎሊያድ ተራራው ጎሊያድ ግዙፉ?
እልፍ አዕላፍ ጎሊያድ ከቦን ሲደነፋ፣
ወንጭፉን ጠቅልሎ ምነው ዳዊት ጠፋ?
ብሎሃል በልልኝ!!
ለረከሰ ጠጠር ለሞላ ወርዋሪ፣
“ወንጭፍህን ስጠው ለዚህ ታሪክ አውሪ”
ብለህ እዘዝልን…!!
እንዴት ነህ ጌታ ሆይ? ሰማይ ቤት እንዴት ነው?
የሙሴ አልጋ ወራሽ እያሱ ሰላም ነው?
ያቆማትን ፀሃይ ግቢ ቢላት ምነው?
ያው እንደምታውቀው፣
አስራ ሶስት ወራት ነው ፀሃይ የምንሞቀው
ኧረ ፀሀይ በዛ፣ኧረ ፀሀይ በዛ
የመጣው ወር ሀሉ ፀሀይ እያዘለ፣
የተሾመው ሁሉ “ፀሀይ ነኝ” እያለ
የአስራ ሶስት ወር የግዜር ፀሃይ፣
የአስራ ሶስት ወር የሰው ጀምበር፣
ባቃጠላት ምድጃ አገር፣
ምን ታምር ሊኖር ይችላል ፀሀይ ሁኖ እንደመፈጠር
ኧረ እግዜር በናትህ በጭንቅ አማላጇ፣
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ፣
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና፣
ሙቀት ገደለና!
እናልህ እግዜር ሆይ ማጣፊያው አጥሮናል፣
ስም ያለው ሞኝ ነው ሁሉም ይጠራናል
ጳውሎስ ሲሉን…አቤት
ጴጥሮስ ሲሉን…ወይዬ
ይሁዳ ሲሉንም አቤት እንላለን፣
ስማችንን ሸጠን…ሰላሳ ጭብጨባ እንቀበላለን
ተወው የኛን ነገር…ሰማይ ቤት እንዴት ነው….
ሄዋንስ ደህና ናት?
ያው የልጅ ልጆቿ በእግሯ ተተክተው
የፍሬው ሲገርምህ ግንዱንም አንክተው
ለፍጥረተ አዳም ባይኑ ያገምጡታል፣
ሰይጣንም ደህና ነው ኑሮ ተስማምቶታል…
ሰውን ለማሳሳት ላይ ታች ማለት ትቷል፣
ሳይጠራው የሚጎርፍ ህዝብ በዝቶለታል…!!
ኧረ እግዜር በናትህ በጭንቅ አማላጇ፣
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ፣
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና፣
ሙቀት ገደለና…