>
6:50 am - Wednesday December 7, 2022

"...መሰናክሉ ብዙ፣ ቆሻሻው ተጠርጎ የማያልቅ  ሆኖ ስለታየኝ  ወደ ኢሳት ቢሮ አልተመለስኩም!!!" (አበበ ገላው)

“…መሰናክሉ ብዙ፣ ቆሻሻው ተጠርጎ የማያልቅ  ሆኖ ስለታየኝ  ወደ ኢሳት ቢሮ አልተመለስኩም!!!”

 

አበበ ገላው
ወደ ፓሪስ የሄድኩት እኔ ነበርኩ!
ከጥቂት ቀናት በፊት የቀድሞ የስራ ባልደረባዬ ኤርሚያስ ለገሰ በኢሳት ዙሪያ የግንቦት ሰባት አመራሮች ጎጂ ጣልቃ ገብነትና አሉታዊ ተጽኖውን  በማስመልከት የሰጠውን ማብራሪያ ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሲመላለስ ባጋጣሚ አየሁት። ኤርምያስ ከዚህ ጋር አያይዞ ሲሳይ አጌና አምስት ሚሊዮን ዶላር ለመቀበል ፓሪስና አዲስ አበባ መመላለሱን ሲናገር በመገረም ሰምቼ ነገሩ ላም ባልዋለበት አይነት መረጃ ስልሆነብኝ እርምት ማድረግ አስፈላጊ መስሎ ታየኝ። ኤርምያስ በኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ትልቅ ሃላፊነት ይዞ በብሄራዊ ደረጃ የሰራ ሰው በመሆኑ የመረጃ መዛባት ህዝብን ግራ ከማጋባትና ከማደናገር አልፎ በታሪክ እንደ እውነታ ሊመዘገብ ስለሚችል በእርምቱ ቅር ይሰኛል የሚል እምነት የለኝም።
በዚህም አጋጣሚ ሰሞኑን አፍ ለማዘጋት በሚመስል ቀቢጸ ተስፋ ሙከራ ለምን ተተቸን በሚል ወያኔያዊ እሳቤ የኢሳት ሃላፊ በነበርኩበት ጊዜ ለኢሳት የመጣ “አምስት ሚሊዮን ዶላር” ለመጥለፍ መሞከሬን እና ሌሎች ርካሽ የፈጠራ ድርሳኖችን የቀድሞ ወዳጆቻችን በኔትውርክ ሲያሰራጩ በመታዘቤ ከዚያም አልፎ አንዳንዶች በማያውቁት ጉዳይ አስተያየት ሲሞነጫጭሩ በመታዘቤ በዶሴ ተጠርዞ በመረጃ ተደግፎ ከተቀመጠው አንኳር እውነታ ለጊዜው በጥቂቱ ይፋ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተሰማኝ።
በቅድሚያ ሲሳይ አጌናን በተመለከት ኤርምያስ ያነሳው ጉዳይ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው። ለኢሳት ገንዘብ ለማፈላለግ ከፓሪስ አዲስ አበባ በራሴ ኪሳራ የተመላለስኩት እኔ ነበርኩ። ይሄም ጉዳይ ሚስጢር ሳይሆን ማንም ኢሳት ውስጥ በወቅቱ ይሰራ የነበረ ሁሉ የሚያውቀው ሃቅ ነው። ሲሳይ ከስራ ድርሻው እንጻር በዚህ ጉዳይ ምንም አይነት ተሳትፎ ኖሮት አያውቅም።
ወደ ፓሪስ ያቀናሁት እኤአ ኦክቶበር 29፣ 2018 ነበር። ወቅቱ ኢሳት አዲሱ መንገሻ (ገድሉ ኪዳኔ) እና ግብረ አበሮቹ በሚሸርቡት ማለቂያ የሌለው ተንኮልና የበስተጀርባ ወሳኔዎች ተሸምድምዶ አደጋ ላይ መውደቅ ብቻ ሳይሆን የዲሲና የአውሮፓ ስቱዲዎች ይዘጉ፣ ሰራተኛ ይቀነስ  ብለው ያለበቂ ዝግጅት እቅድ የነደፉበት ጊዜ ነበር። ለዚህ ውሳኔ ከቀረበው ምክንያት አንዱ የበጀት እጥረት ነበር። ስለሆነም አስተማማኝ የገንዘብ ድጋፍ ማፈላለጉ፣ ምንም እንኩዋን እንቅፋቱ ብዙ ቢሆንም፣ ወሳኝ ነበር።
የፓሪሱ ጉዞዬም አላማ የኦፐን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን (Open Society Foundations) ፕሬዚዳንት የሆኑትን አምባሳደር ፓትሪክ ጋስፓርድን ኢሳትን በገንዘብ እንዲረዱ ለማግባባት ነበር። በአለም ዙሪያ ለስራ የሚዘዋወሩትን አምባሳደሩን ኒው ዎርክ በሚገኘው ቢሯቸው ቀጠሮ ይዤ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሞክሬ ስላልተሳካልኝና ፓሪስ ላይ የመገናኘት አጋጣሚ ስለተፈጠረ ተጣድፌ ነበር ወደዚያው የበረርኩት።
የፕሬዚዳንት ኦባማ አማካሪና የፖለቲካ ስትራቴጂስት ከነበሩት ከአምባሳደር ጋስፓርድ ጋር የተገናኘንው ለመጀምሪያ ጊዜ ሲሆን ስለኢሳት አመሰራረት፣ በኢትዮጵያ ለመጣው ለውጥ ስለነበረው ግዙፍ አስተዋጾ፣ ስለወደፊት እቅዱና መሰል ጉዳዮች ለማስረዳት እድል አግኝቼ ነበር። እርሳቸውም በርካታ ጥያቄዎችን አንስተውልኝ በሚቻለኝ አቅም አጥጋቢ መልስ ሰጥቻቸው ኢሳትን በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች እንዲረዳ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተውልኝ ተለያየን።
ከዚያም በኢሜይልና በስልክ በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ መረጃ ስንቀያየር ከቆየን በሁዋላ አምባሳደር ጋስፓርድን በድጋሚ አዲስ አበባ ላይ የማግኘት እድል ገጠመኝ። ሰውዬው በቀላሉ የማይገኙ በመሆናቸው እሁንም በራሴ ወጪ እኤአ ኤፕሪል 30 2019 በድጋሚ ወደ አገርቤት አቀናሁ። የአለም የፕሬስ ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀውን አለም አቀፍ ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡትን አምባሳደር ጋስፓርድን በማግስቱ  ያገኘሁዋቸው ሸራተን ነበር። ከርሳቸው ጋር የነበረኝ ተከታይ (follow-up) ስብሰባ ወሳኝ ነበር። ሰውዬው የመጡት በደንብ ተዘጋጅተው ነበር።
በስብሰባችን መሃል ኢሳት ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ገንዝብ እንዳያገኝ እንቅፋት የፈጠሩ ሁለት ጉዳዮችን አነሱ።
አንደኛው ከግንቦት ሰባት ጋር ስላለው ቁርኝት ነበር። ኢሳት ትርፋማ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ የተመዘገበ የራሱ ህጋዊ ሰውነት ያለው የሚድያ ተቁዋም መሆኑን ሙሉ በሙሉም ነጻ ሆኖ አቅሙን ገንብቶ ለመንቀሳቀስ ማቀዱን አስረዳሁ። ሁለተኛው ጉዳይ የኢሳትን የገንዘብ አያያዝ ሊያሳይ የሚችል የኦዲት ሪፖርት እንድልክላቸው ጠየቁኝ። ይሄኛው ጉዳይ ደግሞ በጣም ቀላል ቢመስልም ግን ደግሞ ከዚህ በፊት ውስብስብ ችግር የፈጠረ ነገር ነበር።
ጉዳዩ እንዲህ ነው። ኢሳት ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ባግባቡ ኦዲት አይደረግም። የድርጅቱ የገንዘብ አያያዝ ዝርክርክና ለብክነት የተጋለጠ ነው። የኢሳትን አመራር በሃላፊነት ከተረከብኩ በሁዋላ ይህንኑ በመገንዘብ ችግሩን ለማስተካከል ሙከራ አድርጌ ነበር።
ለዚህም መነሻ ምክንያት የነበረው በ2017 መጀመሪያ ላይ ለኢሳት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት የነበራቸው ሁለት ለጋሽ ድርጅቶች የኦዲት ሪፖርት እንድናቀርብ ጠይቀውን ነበር። በዚሁ መሰረት የፋይናንስ ሃላፊዋን ሂሩት ልሳነወርቅን ጉዳዩን አስረድቼ የኦዲት ሪፖርት እንድትሰጠኝ ጠየኩዋት። አንድም የኦዲት ሪፖርት አልነበረም!
እንደ ምንም ብዬ የሁለት አመታት ኦዲት እንዲደርግ አደረኩ። የቀረበው ሪፖርት ኢሳትን የሚያህል ህዝባዊ ድርጅት የገንዘብ አያያዙ ከሚጠበቀው በታች የወረደና ብልሹ መሆኑን ግልጽ አደረገ። ደረሰኝ ባግባቡ ፋይል አይደረግም፣ ሂሳብ በየግዜው አይወራረድም፣  ወስጣዊ ቁጥጥር (internal control) የለም፣ የባንክ ሂሳብ በዘፈቀደ ይዘጋል ይከፈታል፣ አዲሱ መንገሻ የሚያንቀሳቅሰው የሳተላይት አገልግሎት ክፍያ ከፍተኛ  ወጪ ክፍተት ያለበት ብቻ ሳይሆን ባግባቡ አይወራረድም። ግለሰቡም በድርጅቱ ፋይናንስ ውስጥ፣ ምንም እንኩዋን የቦርድ እባል ቢሆንም፣ እንደፈለገ እጁን ያስገባል። አስፈላጊ ከሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ ያሰባሰብኩትን መረጃ አንድ ባንድ ይፋ አደርገዋለሁ።
እንደ ሃላፊ በአዲሱ መንገሻና በገንዘብ ያዧ በዘፈቀደ የሚንቀሳቀሰውን የኢሳት ፋይናንስን ለማስተካከል የጀመርኩት እንክስቃሴ በሁለቱ ግልሰቦች እንቅፋት በዛበት። እኔም እንደ ድርጅቱ ዳይሬክተር ቁጥጥር ማድረግ እንዳልችል፣ ስራ እንዳልሰራና ጥያቄ እንዳልጠይቅ አዲሱ መንገሻ የቦርድ ሃላፊነቱን ያለ አግባቡ በመጠቀም ከባድ ችግር ፈጠረብኝ።
ለጊዜው ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና ከኦፐን ሶሳይቲው ፕሬዚዳንት ጋር ፍሪያማ ውይይት አድርገን ተለያየን። ይሁንና ዲሲ ላይ ብዙ ደስ የማይሉ የእነ “ገድሉ” ውስብስብ የበስተጀርባ ውጊያዎችና እንቅስቃሴዎችን በተመለከት መረጃዎች ደረሱኝ። በእቅንርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ምንም እንኩዋን ኢሳት ትርፋማ ያልሆነ ህዝባዊ ድርጅት ሆኖ የተመዘገበ ሚድያ ቢሆንም ግንቦት ሰባት የኢሳት ፈጣሪና ባለቤት መሆኑን በመግለጫ ይፋ አደረገ። ሁላችንንም ያሰባሰበ የነጻ ሚድያ የነጻነት ትግል ጥሪ ዲስኩር ገደል ገባ።
በድጋሚ ቁጭ ብዬ አሰብኩበት። ምንም እንኩዋን የኦፐን ሶሳይቲን ድጋፍ ጉዳይ እልባት መስጠት ብፈልግም ወደ ኢሳት መመለስን ግን ልቤ እልፈቀደውም። እኔ እስከማውቀው ኦፐን ሶሳይቲም ይሁን ሌሎች ፋውንዴሽኖች የፖለቲካ ፓርቲ ልሳን ለሆነ ሚድያ የገንዝብም ይሁን የሞራል ድጋፍ አይሰጡም። አላማችን ትልቅ ቢሆንም መሰናክሉ ብዙ፣ ቆሻሻው ተጠርጎ የማያልቅ አታካች ሆኖ ስለታየኝ ከአዲስ አበባ መልስ ወደ ኢሳት ቢሮ አልተመለስኩም። እኔ የማውቀው አውነታ ባጭሩ ይሄው ነው!
Filed in: Amharic