>
2:05 pm - Thursday December 8, 2022

በአግባቡ ያልገዛ ትርፉ ኪሣራ ነው (ይነጋል በላቸው)

በአግባቡ ያልገዛ ትርፉ ኪሣራ ነው

 

ይነጋል በላቸው

 

አንዳንዴ ዝምታህን የሚሰብሩ ጉዳዮች ይገጥሙህና ለፈጣሪህ ወይም ለትውልድ ፍርድ ትተህ ላትጽፍበት ወይ ላትናገርበት ለራስህ የገባኸውን ቃል ትሰብራለህ፡፡

ሰሞነኛው የሀገራችን ሁኔታ ጥቂቶቻችን ስንጮህበት የባጀነውን ኢትዮጵያዊ የምጽዓት ቀን መርዶ ጠቋሚ ዋዜማ ላይ መሆናችንን በግልጽ አፍ አውጥቶ እየተናገረ ይገኛል፡፡ ይህንንም የማያምን እጅግ ብዙ ነው፡፡ አውቆ የተኛን መቀስቀስ ከባድ ነው፡፡ ሲመክሩት የማይሰማም ሲቀብሩት ያልፍለታል፡፡

ዶ/ር አቢይ ከጠ/ሚኒስትርነት ይልቅ ወደ ቲያትረኛነት ያዘነበለ ተፈጥሮ እንዳለው በሰሞነኛ ኦሮሞኣዊ እንቅስቃሴዎች በሚገባ ተረድቻለሁ፡፡ የምታውቁትን ነው የምነግራችሁ፡፡

“ፍትህ ዐዋቂውና ሀገርን ያለ አንዳች አድልዖ የሚያስተዳድረው ሰባተኛው ንጉሥ አፄ” ዶ/ር ኮሎኔል አቢይ ደሴ ላይ በአማሮች የበጀት አጠቃቀም ዙሪያ ምን ብሎ ቀለደ? አስታውሱ፤ የቅርብ ጊዜ ድራማዊ ቃለ ተውኔት በመሆኑ አትዘነጉትም፡፡ ከረሳችሁ – “ባጀታችሁን በልዩ ኃይል ሥልጠና እየጨረሳችሁ…(እኔ ምን ላርጋችሁ ዓይነት?)”

ሰውዬው ከእውነት ይልቅ ለድራማ የተመቸ ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ሰውዬው የአማራን የሰኔ 15/2011 ዕልቂት በልዩ ሰይጣናዊ ጥበብና ሥውር ደባ እንዳቀናበረ የምናምነው ለዚህ ነው –  እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ድርጊቱ ከመፈጸሙ ሚዲያዎች ሁሉ ራዳራቸውን ወደ ባህር ዳር አሹለው በጦር ልብስ አስቀድሞ ተዘጋጅቶ የሚጠብቀውን ጠ/ሚኒስትርና “አማራ”ውን ቃል አቀባይ ንጉሡ ጥላሁንን እየተቀባበሉ “የመፈንቅለ መንግሥቱ”ን ዜና ባላራገቡ ነበር – ይህን ክስተት መካድ ዘረኝነት፣ ሆዳምነትና ሥልጣን ወዳድነት ነው፡፡ ሰውዬው አማራን ካላንበረከከና ትግሬዎችን በተለዬ ዘዴና በጥቅማ ጥቅም ከፖለቲካው መድረክ ካላገለለ በኦሮሚያ ስም ዝንታለሙን ሊቆጣጠረው የሚፈልገውን አፄያዊ ሥልጣን ሊያጣ እንደሚችል ያምናል ብለን የምንናገረው ለዚህ ነው፡፡ ሰውዬው ዛሬ የተናገረውን ነገር የሚቃረን ወይ የሚያፈርስ ድርጊት የሚፈጽመው ሊቆጣጠረው የማይችለው ውስጣዊ የኢጎ ደዌ ወይም በልዩ የ“ይህን ካላደረግህልን ይህን ገመናህን እናወጣብሃለን/እንዲህ እናደርግሃለን” በሚል የblackmailing ጦስ ውጫዊ ጠላት የሰጠውን ተልእኮ ለመወጣት መሆኑን የምናምነው ለዚህ ነው፡፡ …

የዚህን ወጣት የሃሳዊ መሲሕ ጉዞ ለመተንተን ጊዜውም ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ግን በርሱ አመራር ሥር አንዱን ክልል ለማፍረስና ከናካቴው ለማጥፋት ሌላውን ለማባበልና የክፉ ቀን ረዳት አድርጎ በተጠባባቂነት ለማስቀመጥ እንዲሁም ወጣሁበት ያለውንና እወክለዋለሁ የሚለውን ክልል እንደ አንዱ ኃያል ሀገር ለማድረግ የሀገርን የሀብት ምንጭ እያሟጠጡ ማድረቅ የዞረ ድምር ያለው መሆኑን የምትቀርቡት ንገሩት፡፡ ዛሬ ትናንት እንዳይደለ ነገም ሌላ ቀን ይሆናልና የፋሲካዋን ገረድ አንሁን፡፡

ተመልከት፡፡ ኦሮሚያ የሚሉት የአሜባ ቅርጽ ተሰጥቶት የተቋቋመ ክልል ሰሞኑን ለ29ኛ ጊዜ ጦረኞችን አስመረቀ – በአንድ ዙር 5 ሽህ ቢያስመርቁ ወደ 145 ሽህ የሚደርስ ሣይሠራ የሚበላ ተቀላቢ “ቦዘኔ” አለ ማለት ነው፤ በነገራችን ላይ በየስንት ወር አስመርቀው 29ኛ ዙር እንደደረሱ ለመገመት አስቸጋሪ ነው – በሁለት ዓመታት ውስጥ ይህን ያህል ገዳይ ሠራዊት ካስመረቁ በአሥር ዓመት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ገደማ ሊያስመርቁ መሆኑ ነው፡፡አቢይ አማራን እያጠፋ ኦሮሚያን ሽቅብ ማስወንጨፉን ተውት ግዴለም፤ የኛው ነው፡፡ ግን በዚህ ሂደት የሚባክነው ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ዕውቀትና የሰው ኃይል ይታያችሁ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ ለልማት ሳይሆን ለጦርነትና ለውድመት መሆኑ ይበልጥ ያሳስባል፡፡ የጦርነቱን አሸናፊ ባለበት እናስቀምጠውና በዝግጅቱ የሚከሰተውን እናጢን፡፡

አማራ 20 ሽህ የአካባቢ ሚሊሻ እንዲያሰለጥን በብአዴን በኩል ከአቢይ ተፈቀደለት እንበል፣ ትግራይ አንድ ሚሊዮን ሥልጡን ኮማንዶ አለው እንበል፣ ኦሮሞ ሁለት ሚሊዮን ጦረኞችን አዘጋጀ እንበል… ደምሩልኝ፡፡ 3,020,000፡፡ ይህ ሕዝብ ከገበሬ የሚመለመል ነው፡፡ የተማረ ሰው መቼም ቢሞቱ አይመለምሉም፡፡ “ለምን”ን ያውቃላ! ይህን አምራች ሕዝብ ለአውዳሚ ጦርነት ማዘጋጀት በተለይ በድሃ ሀገር ውስጥ ትልቅ ወንጀል ከመሆኑም ባሻገር ሰው ሠራሽ ርሀብን ሆነ ብሎ ማስፋፋት ነው – ይህን ያህል ቁጥር ሕዝብ በፋብሪካ ወይም በግብርና ሥራ ቢሠማራ ስንትና ስንት ችግር ሊቀርፍ እንደሚችል አስት፤ አሁን ባለው ችግራችን ላይ ይሄና ከዚህም እየጨመረ የሚሄደው በላተኛ ሲታከልበት ከድጥ ወደ ማጥ ነው፡፡ ያደለውና ጥሩ መሪ ያለው ሀገር ዜጎችን በፍቅር በማስማማት ለእህል ምርትና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት እያበቃ ርሀብን፣ እርዛትን፣ ድንቁርናን፣ ስደትንና የዘመናት የኋላ ቀርነት ችግሮችን ለመቅረፍ ይነሳል፡፡ እነዚህ አስተዳደግ የበደላቸው ጡንቸኞች ግን አሸናፊነት ለማይኖረው ጦርነት ሕዝብን እያነሳሱ የሥልጣንና የሀብት አራራቸውን እየተወጡ በምትኩም ማኅበረሰብኣዊ ትርምስን ይፈጥራሉ፡፡ አዲስ አበባን ተመልከቱ፡፡ በሥራ መግቢያና መውጫ አካባቢ በተለይ ወደ ከተማ ወጣ በሉ፡፡ የአሥር ደቂቃ የመኪና መንገድ ሁለት ሰዓት ሊፈጅብህ ይችላል፡፡ ሥራ አጥነቱ፣ ሆን ተብሎ በየቀኑ የሚሰቀለው የኑሮ ውድነት፣ ሙስናው፣ ወዘተ. ይቅር አይነሣ፡፡ ጀግና መሪና ጀግና አክቲቪስት ማለት እነዚህንና መሰል ማኅበራዊ ችግሮችን ለማስወገድ የሚጥር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ፈጽሞ አልታደለችም፡፡

ለማንኛውም “እማሆይ! ባፈሱ ሣይሆን በጎረሱ ነው!” የተባለውን ብሂላዊ ሥነ ቃል ላስታውስና ላብቃ፡፡ “ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም” የሚለውንም ልመርቅ፡፡ “ነገር በሦስት ይጸናል” ይባላልና “ዘጠኝ ሱሪ ፈስ አይቋጥርም”ንም ልሰልስልህ – ሁሉም እውነት ነው፤ የእውነት አንጻራዊነት በጊዜ ጽላሎት ሥር እንደሚገኝ መረዳት ግን ብልኅነት ነው፡፡  የሚሻለው ታዲያ ወደ ልቦና መመለስ ነው፡፡ የሚበልጠው ወንድማማችነትንና የአንዲት ሀገር ልጅነትን ማስቀደም ነው፡፡ በወፈሩ ሞትን ማስቀረት፣ በቀጠኑ ዛሬውኑ መሞት የለም፡፡ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፡፡ አሸናፊነት ከላይም ከታችም የሚገኝ ፀጋ እንጂ በጉራና በጦር ብዛት ብቻ አይደለም – ደግሞም የታች አሸናፊነት ጊዜያዊ ሲሆን የላይ አሸናፊነት እውነተኛና ዘላቂም ነው፡፡ እኔ በበኩሌ የምፈራው ክፋትንና ክፉ ሥራን ብቻ ነው፡፡ ከክፋት የራቀ፣ መልካም ሕዝባዊ ዓላማ ያነገበ፣ የተገፋና የተበደለ፣ በሌሎች የማይሳለቅና ፍትህን ምርኩዙ ያደረገ ማንም ኃይል ቢዘገይም አሸናፊው እርሱ ነው፡፡ ምሥራቅ አፍሪቃን በፍርሀት ያራደው የደርግ ጦር፣ አውሮፓን ያንቀጠቀጠው የሂትለር ጦር፣ መካከለኛው ምሥራቅን አንገት ያስደፋው የሣዳም ልዩ ጦር … አነሳሳቸውንና አወዳደቃቸውን ማጤን ይገባል፡፡ ለስሜት ሳይሆን ለኅሊና ቅድሚያ እንስጥ፡፡ ለወረት ሳይሆን ለአመክንዮ ቦታ እንስጥ፡፡ ለተረኝነት ሳይሆን ለዘላቂ የወል ሕይወት ትኩረት እንስጥ፡፡ ቀናነት ይኑረን፤ ነገርን አናጣምም፡፡ አበቃሁ፡፡ 

Filed in: Amharic