>
5:13 pm - Sunday April 19, 7992

አይጠየፍ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

አይጠየፍ

 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም
አድገናል፤ ተሻሽለናል፤ የክርስተስም፣ የመሀመድም ትምህርት ገብቶናል፤ የፈረንጁንም ተምረናል እያልን በምናጓራበት ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በጎሳና በሃይማኖት ልዩነቶች የተነሣ የመገዳደል ወሬ እንሰማለጠን፤ እንደነግጣለን፤ እናፍራለን፤ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ያለ የመንፈስ አዘቅት ውስጥ እንደገባን በሐዘንና በትካዜ እንገነዘባለን፤ ሌላውን ሁሉ አልፎ፣ ኩራትና ክብራችንን አልፎ ሰው መሆናችንን እየተፈታተነ ነው፡፡
የማይነኩት ብቻ ሳይሆን የማያናግሩት፣ እሱን መቅረብ እንደነውር የሚቆጠር፣ የሚያዋርድ፣ ወራዳ፣ የሚናቅ ሰው አለ፤ ግን ሰው መሆኑ ብቻ ሲታወቅ ሌላው ሁሉ ይቀራል፤ ዋጋ ያጣል፤ ዋጋ ያለው ሰው መሆን ብቻ ነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍቅር የነገሠበት፣ መሞካሸት ተራ ነገር የሆነበት፣ እሱ ማን ነው? እስዋ ማን ነች? የማይባልበትና ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የሚታወቅበት እንደወሎ ያለ ቦታ አላውቅም፤ ዱሮ እኔ የማውቀው ያልተማረው የወሎ ሕዝብ ዛሬ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተባሉ ክብር የተሰጣቸውና በጎሣና በሃይማኖት ልዩነት ከሚጋደሉት ጋጠ-ወጥ ጎረምሶች የትናየት የተሻለ ነበር፤ በዩኒቨርሲቲዎች ግቢ ወስጥ ደም እየተፋሰሱ ኒቨርሲቲውን የጦር ሜዳ ያደረጉት በግቢው ውስጥ ያሉት ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ወይም በቤተ መስጊድ እንደገባ ውሻ ለቃቃሚዎች ናቸው፤ ሰው መሆናቸውን አያውቁም! ሰው አለመሆናቸውን ቢያውቁ በዚያ በተቀደሰ ግቢ ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡
ለዚህ ነው ወይዘሮ አሰለፈች በቲቪ በሬሣቸው ላይ እየየ! እያለች እንባዋን ያፈሰሰችው! አሰለፈች የምትወዳት አገርዋ የተማሩ ሰዎችን ታፈራለች ብላ ስታስብ ሰው አጣች፤ በአገርዋ ሰው ማጣትዋ ነፍስዋን አቆሰለባት! ለዚህ ነው እየየ! ያለችው! አሰለፈች እንደሰው፣ እንደኢትዮጵያዊት፣ እንደእናት የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ስንት ኢትዮጵያውያን ተሰምቷቸዋል? ስንቶችስ አልቅሰዋል? ከዚህም በላይ የተለቀሰላቸውን ድንጋች የአሰለፈች እንባ ረጠብ አድርጓቸው ይሆን?      እንኳን ተራው ሰው ንጉሡም ሰውን መናቅና ማዋረድ የሚያዋርድ መሆኑን ተገንዝበው ‹‹ግብር›› የሚያበሉበትን አዳራሽ ‹‹አይጠየፍ›› ብለውታል፤ ዜጋ ሁሉ በእኩልነት ገብቶ የሚበላበት! የዛሬው የፈረንጅ አሽከር ይህንን ሶሺያሊስት ወይም ኮሚዩኒስት ይለው ይሆናል! ወሎ አይጠየፍ! ብሎታል! በወሎዬዎቹ ቋንቋ ሁልሽም እኩል ነሽ ማለት ነው!
የፈረንጅ ቢሆን ይህን ጊዜ ስንት መጽሐፍ ተጽፎበት ስንቱ ዶክተር ተብሎበት ነበር፤ እዚህም ቢሆን በየ ዪኒቨርስቲው የሚጋደሉት ተማሪዎች ጊዜያቸውን ለጥናት ቢያውሉት  ለቀሩት የኢትዮጵያ ክፍሎች አርአያ የሚሆኑ ብዙ ነገሮች ነበሩት፤ ነጮች ጥቁሮችን ሲንቁና ሲያዋርዱ ይጠየፏቸው ነበር፤ ስለሚጠየፏቸውም በመሀከላቸው ጋብቻ ክልክል ነበር፤ ዩኒቨርሲቲን ከምዕራባውያን ተማርንና ሰው መሆንን በነሱ ጠባብነትና ዘረኛነት መነዘርነው! አዬ መማር!
Filed in: Amharic