>
5:13 pm - Thursday April 19, 8068

ሀይማኖትን ለርካሽ የፓለቲካ አላማ መጠቀም- አህመዲን ጀበልን እንደ ማሳያ!!! (አንተነህ ሙሉጌታ)

ሀይማኖትን ለርካሽ የፓለቲካ አላማ መጠቀም- አህመዲን ጀበልን እንደ ማሳያ!!!

አንተነህ ሙሉጌታ
 
* “ለህዝበ ሙስሊሙ ያላቸውን የመረረ ጥላቻ በህገ መንግስታቸው ሳይቀር አንጸባርቀዋል…” ተብለው በአህመዲን ጀበል የፈጠራ ክስ የቀረበባቸው ንጉሰ ነገስት ከታዋቂ ኡስታዞችና ሼሆች ጋር የተነሱት ታሪካዊ ፎቶ ተካቷል
አህመዲን ጀበል የተባለው ጽንፈኛ የኦሮሚያ ብሄርተኛ ሰሞኑን LTV የተባለ የኦነግ ልሳን ለሆነ ቴሌብዥን በሰጠው ቃለመጠይቅ የ1923ቱ የአጼ ሐይለስላሴ ሕገ_መንግስት “ኢትዮጵያ በእስላሞችና በአረማዊያን የተከበበች እና አደጋ ውስጥ የወደቀች አገር ናት” ብሎ  በመግቢያው ያትታል። ይህ ደግሞ ሕገመንግስቱ ሙስሊሞችን በኢትዮጵያዊነት አያቅፍም።” የሚል ፕሮፓጋንዳ አሰራጭቶ ነበር።
 
የእሱን ኢንተርቢው ተከትሎ በእዉኑ የ1923ቱ የአጼ ሐይለስላሴ ሕገ_መንግስት “ኢትዮጵያ በእስላሞችና በአረማዊያን የተከበበች እና አደጋ ውስጥ የወደቀች አገር ናት” ብሎ  በመግቢያው ላይ አስፍሯልን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነበር።
 
 በኢትዮጵያዊነትና በአማራ ሕዝብ ላይ የሚሰራጩ የተለመዱ የሀሰት ውንጀላዎችን በማስረጃ እያስደገፈ በማጋለጥ የሚያከሽፈው አቻምየለህ ታምሩ የተባለው ሊቅ ሁሌም እንደሚያደርገው የአሁኑንም የአህመዲን ጀበልን የተለመደ የሀሰት ውንጀላ በማስረጃ አስደግፎ ውድቅ አድርጎታል።
 
አህመዲን ጀበል ሀይማኖትን ሆነ ብለው ለርካሽ የፓለቲካ ጥቅም ከሚጠቀሙ ጽንፈኛ ብሄርተኞች አንዱ ነው።
አህመዲን ጀበል ሙስሊሞች  በኢትዮጵያ ውስጥ በሀይማኖታቸው ምክንያት በደል እንደደረሰባቸው አድርጎ የውሸት ውንጀላ ሲያሰራጭ በዚህ ሳምንት ሁለተኛው ነው።
 
በእነዚህ ሁለት የለውጥ አመታት ውስጥ የተፈጸሙ የሀይማኖት ጥቃቶችን በዝርዝር ካየን በሀይማኖት ጥቃት መጮህ  ካለባት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን እንጅ እስልምና ሊሆን አይችልም። በእነዚህ ሁለት የለውጥ አመታት በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ላይ በደረሰ ጥቃት 158 ካህናትና ምዕመናን ሲገደሉ ከ20 የማያንሱ ቤተክርስትያናት በእሳት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። ከዚህ አንጻር በእስልምና ላይ የተፈፀመ ጥቃትን ካየን በሀይማኖት ጥቃት ምክንያት የአንድም ሙስሊም ህይዎት አላለፈም። የተቃጠለው የመስጊድ ቁጥርም ከተቃጠለው የቤተክርስትያን ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው።
 
 ይሁን እንጅ በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በኩል የሀይማኖት ጥቃቱን ተከትሎ በጅምላ አንድን ብሄር ወይም ሕዝበ ሙስሊሙን በጅምላ የወነጀለ የለም። በተቃራኒው እነ አህመዲን ጀበል; ጃዋር መሀሙድ የመሳሰሉት ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች እምነትን ሽፋን አድርገው በአማራ ሕዝብ ላይና በኢትዮጵያዊነት ላይ ጦርነት ከፍተዋል። ጥቂት ደንቆሮዎች በሰሩት ጥፋት የአማራን ሕዝብ በሞላ መወንጀል ወይም የመላው አማራ ሕዝበ-ክርስትያን በሙስሊሙ ላይ የሰራው በደል አስመስለው ይወነጅላሉ። እነዚህ ጽንፈኞች ይኸንን ድርጊት የሚጠቀሙት እያንዳንዷን ጥቃቅን ክስተት አማራነትንና ኢትዮጵያዊነትን ለመወንጀል መጠቀሚያ ስለሚፈልጉ ነው።
 
 አህመዲን ጀበልና የመሳሰሉት ጽንፈኞች የሞጣውን የመስጊድ ቃጠሎ የብሄርና የሀይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ እየተጠቀሙበት ነው። ዋና አላማቸውም ሀይማኖትን ሽፋን አድርገው ግጭት መቀስቀስና የአገሪቱን ሰላም በማናጋት የተጀመረውን የዲሞክራሲ ለውጥ በማጨናገፍ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ በብሄር የተከፋፈለ አስተዳደር ውስጥ ተዘፍቃ እንድትቀር ማድረግ ነው።
 
 አህመዲን ጀበል ለዚህ አላማውም ወቅታዊ ክስተቶችን ከመጠቀም አልፎ የሌለ ያልተፈጸመ ታሪክን በመፍጠር ወይም እውነተኛውን ታሪክ አጣሞ በማቅረብ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ከኢትዮጵያዊነት አመለካከት ጋር ማጣላት;  እንደዚሁም አማራ ሙስሊሞችን ከአማራ ክርስትያኖች ጋር በማጋጨት የአማራን ሕዝብ በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ በመክተት ጠላቶቹን እንዳይቋቋም ማዳከም ነው። አህመዲን ጀበል ለዚህ እኩይ ተግባሩ  የ1923ቱን የአጼ ሐይለስላሴን ሕገመንግስት ኢትዮጵያዊ  ሙስሊሞችን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጎች አይቆጥርም ብሎ በሕገመንግስቱ ላይ የሌለ ያልተጻፈ ታሪክ ጠቅሶ የዘባረቀው።  
 
 እርግጥ ነው በታሪካችን የተፈጸመ መጥፎ የታሪካችን አካል ካለ መካድ የለብንም። ጥሩው ብቻ ሳይሆን መጥፎውም ታሪካችን ነው። ጥሩውም ሆነ መጥፎው የሁላችንም የጋራ ታሪካችን ነው። 
 
  የማይካደው እውነታ እስከ 1966 ዓብዮት ድረስ በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት ስርዓት ውስጥ ኦርቶዶክስ ክርስትና መንግስታዊ ሀይማኖት የሆነና የቅርብ ድጋፍ ያገኝ የነበረ መሆኑን መካድ አይቻልም። ለምሳሌ የክርስትያኑ ሀይማኖት በዓላት እነ ገና/ ልደት; ፋሲካ የመሳሰሉት ብሄራዊ በዓላት ሲሆኑ የሙስሊሙ ሀይማኖታዊ በዓላት በብሄራዊ በዓልነት እውቅና አልነበራቸውም። ሀሰቱን የምንቃወመውን ያክል እውነታውን ደግሞ ጥሩም ሆነ መጥፎ መቀበል ያስፈልጋል። 
 
 የሙስሊም እምነት በዓላት ብሄራዊ በዓል ሁነው መከበር የጀመሩት ከ1966ዱ አብዮት በኋላ ነው። አንድ ሰው ይኸን ንጹህ ታሪክ ለሌላ ጥቅም ሽፋን ሳያደርገው ታሪክን በታሪክነቱ ቢያስተምረው የሚቃወም ሰው ያለ አይመስለኝም። ጥሩውም መጥፎውም ታሪካችን ነውና።
 
ነገር ግን እንደ አህመዲን አይነት ሰዎች አላማቸው ለእስልምና መቆርቆር ሳይሆን ወይም ታሪክን በታሪክነቱ ማስተማር ሳይሆን አላማቸው እስልምናን ለአክራሪ ጸረ-ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት መጠቀሚያ ማድረግ ነው። ሰውየው የሚያስቀድመው እስላምነቱን ሳይሆን አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነቱን ነው።
 
 ለዚያም ነው በአማራ ክልል የተከሰተችዋን ትንኝ የምታክል ስህተት ዝሆን አሳክሎ በማቅረብ ችግሩን የፈጠሩት መላው የአማራ ሕዝብ እንደሆነ አድርጎ የሚወነጅለው። አህመዲን ጀበል  ብሄራቸው አማራ የሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮች ኦሮሚያ ክልል ብዙ ግፍ ሲፈጸምባቸው አንዳች ነገር ትንፍሽ አይልም።  ለምሳሌ የአማራ ብሄር ተወላጅ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከኦሮሚያ ክልል በግፍ ሲባረሩ ይህ በእምነታችን የተከለከለ ነው; አቁሙ ብሎ አይገስጽም።
 
 በተቃራኒው አማራ ክልል ከመላው የአማራ ሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የቆሙ ጥቂት ደንቆሮ ጋጠወጦች የሰሩትን ስህተት ግን የመላው አማራ ሕዝበ-ክርስትያን በሙስሊሙ ላይ የሰራው በደል አስመስሎ ያቀርበዋል።
 
 የ1923ቱን የአጼ ሀይለ ስላሴ ሕገመንግስትንም ኢትዮጵያዊነትን ከእስላሞች ልብ ለመፋቅ ብሎ የሌለ ነገር ፈጥሮ ሕገመንግስቱ ላይ ያልተባለ/ ያልተጻፈ ነገር አምጥቶ የተለመደውን የውሸት የኦነግ ፕሮፖጋንዳውን ዘባረቀ።
 
 አቻምየለህ ታምሩ ሕገመንግስቱን አቅርቦ የዘባረቅከው ነገር ሕገመንግስቱ ውስጥ የታለ? የምትለው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሕገመንግስቱ ላይ የለም ብሎ ሲሞግተው የመልስ መልስ ብሎ ባሰራጨው ጽሁፍ  ከ10 አመት በፊት የህዎሃት ካድሬዎች ካሰራጩት ህትመት ላይ በማስታወሻየ ላይ የያዝኩት ነው ብሎ መልስ ሰጠ። እሱ ከ10 አመት በፊት የተሰራጨው ሕትመት ብሎ የገለጸው የህዎሃት ወያኔ ካድሬዎች እነ ዶ/ር እንድርያስ እሸቴ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ብለው ባቋቋሙት የህዎሃት ድርጅት በኩል የተሰራጨ ህትመትን ነው በማስረጃ የጠቀሰው።
 
 ቆይ በምን ሂሳብ ነው የአህመዲን ጀበል ማስታወሻ የኢትዮጵያ ሕገመንግስት መግቢያ የሆነው? አህመዲን ጀበል ሀሰተኛ የሀሰት አባት ስለሆነ እንጅ የሕገመንግስቱ ኮፒ በየላይበራሪው ሞልቷል። አንዱ ላይበራሪ ገብቶ ሕገመንግስቱን አውጥቶ ገጽ አንድ ላይ መግቢያውን አንብቦ እሱ የሚለው ነገር እውነት መሆኑን ወይም አለመሆኑን ማጣራት ይችል ነበር እኮ። ችግሩ እውነተኛውን የሕገ መንግስት ኮፒ ቢያነበው እሱ የሚሰብከውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እንደሚያከሽፍበት ያውቃል። ኢንተርቢው ሲሰጥ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት:  ጸረ-ክርስትና እና ጸረ-አማራ መልዕክት ያስተላልፍልኛል ያለውን በሀሰት ከዘበዘበ በኋላ; እንደ አቻምየለህ ታምሩ ያሉ የታሪክ አዋቂዎችና ተመራማሪዎች እሱ የጠቀሰውን ሕመንግስት አቅርበው የምትለው ጽሁፍ በሕገመንግስቱ መግቢያ ላይ የለም። የሕገመንግስቱ ቅጅ ይኸውልህ። አንተ የምትለው ጽሁፍ ግን በዚህ ሕመ-መንግስት ላይ የለም ብለው ሲሞግቱት የወያኔ/ ህዎሃት ካድሬዎች ከ10 አመት በፊት ካወጡት ህትመት ላይ በማስታወሻየ ላይ ያሰፈርኩት ነው ብሎ እንደተለመደው ዘባረቀ። ያውም እኮ የወያኔ/ህዎሃት ካድሬዎች ከ10 አመት በፊት አወጡት ያለውን ህትመት ኮፒ እንኳ አላቀረበም። ማስረጃየ ብሎ ያቀረበው ያንን የህዎሃት/ ወያኔ ካድሬዎች ያወጡትን ህትመት ከ10 አመት በፊት አንብቤ በማስታወሻየ ላይ የከተብኩት ነው ብሎ የሚለው። እንግዲህ ይታያችሁ አህመዲን ጀበል ለውሸት ፕሮፓጋንዳው የሚጠቀመው ማስረጃ የራሱን ማስታወሻ እንደ ሕገመንግስቱ መግቢያ አድርጎ ነው።
 
 በአጠቃላይ እስልምና የአማራ ሕዝብም እምነት ነው።  ለእነ አህመዲን ጀበል ግን የጸረ-ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት መቀስቀሻ መንገድ ነው። አንድ ሙስሊም አማራ ኦሮሚያ ክልል በሙስሊም ኦሮሞዎች ድብደባ ቢደርስበት ለአህመዲን ጀበል ጉዳዩ አይደለም።  የእሱ ነጥቡ እምነቱ ሳይሆን አክራሪ ብሄርተኝነቱ ነው። እስልምናን የሚጠቀምበት ጸረኢትዮጵያዊ ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት እንደ ሽፋን ነው።
 
የአገሬ ሕዝበ ሙስሊም ሆይ; እነ አህመዲን ጀበል: እነ ጃዋር መሃመድ ወዘተ ያሉት ጽንፈኛ ብሄርተኞች ሀይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚንቀሳቀሱት ለርካሽ የፓለቲካ አላማ ነው። በዚህ ዘመን በአማራ ክልል ሙስሊሞች ላይ ሆን ተብሎ ጭቆና እየተደረገባቸው እንደሆነ በማስመሰል የሚራገበው ፍጹም ውሸት ነው። የአማራ ክልልን የሚመራው ድርጅት (አዴፓ; – በአዲሱ ስሙ የአማራ ብልጽግና) ሊቀመንበር ደመቀ መኮነን እኮ ሙስሊም ነው። አገሪቱን እየመሩ ካሉት ከ8ቱ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራርች 6ቱ ሙስሊም ሲሆኑ 2ቱ ፕሮቴስታንት ናቸው። አንድም ኦርቶዶክስ ክርስትያን በሊቀመንበርነት ቦታ ላይ የለም። እውነታው ይኼ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ ሁለት የለውጥ አመታት በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ላይ በደረሰ ጥቃት 158 ካህናትና ምዕመናን ሲገደሉ በሀይማኖት ጥቃት ምክንያት የአንድም ሙስሊም ህይዎት አላለፈም።  ከ20 የማያንሱ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያናትና ወደ 10 የሚጠጉ  የፕሮቴስታንት ቤተ እምነትች በእሳት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ የተቃጠለው የመስጊድ ቁጥር ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።  ተበደልሁ: ተገፋሁ ብላ መጮህ ካለባት ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እንጅ እስልምና  ሊሆን አይችልም።
 
 የአገሬ ሕዝበ ሙስሊም ሆይ እውነታው ይኸ መሆኑን አውቀህ በጽንፈኛ ጸረ-ኢትዮጵያዊ ብሄርተኞች የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ተጠልፈህ አገርህን ወደሚያፈርስ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከመግባት ትጠነቀቅ ዘንድ እመክርሀለሁ።
Filed in: Amharic