>
5:43 pm - Tuesday May 17, 2022

የአክራሪ ኦሮሞዎች የለዬለት ዕብደት በአዲስ አበባ (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

የአክራሪ ኦሮሞዎች የለዬለት ዕብደት በአዲስ አበባ

 

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ 

 

ይህ ጽሑፍ ንዴትን ለመግለጽ ተጻፈ እንጂ አስተማሪነትም ሆነ ገምቢነት የለውም፡፡ ስለዚህ አክራሪዎች እንዲያነቡት አልመከርም፡፡ አንዳንዴ የሚሰማንን ነገር እንዳለ ማውጣቱ ተሸፋፍኖ መተማማትን ያስወግዳልና ጥሩ ነው፡፡  

ለማንኛውም ጤነኛ ክርስቲያኖች እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስስ የልደት በዓል አደረሳችሁ – “በሰላም” የምትለዋን ቅጥያ የተውኳት ሆነ ብዬ ነው፡፡

ከደቂቃዎች በፊት ከመካኒሳ ወደ ሜክሲኮ እየመጣሁ ነበር፡፡ ከፊት ለፊቴ ታርጋው አራት ቁጥር የሆነ የመንግሥት መኪና አየሁ፡፡ አንድ ቁጥር ታክሲ፣ ሁለት ቁጥር የቤት መኪና፣ ሦስት ቁጥር የንግድ፣ አራት ቁጥር የመንግሥት ሆኖ “ኢት.” ይል ነበር የእስካሁኑ የታርጋ አሰጣጥ ደምብ፡፡ አሁን ደግሞ ያ ያየሁት የመስክ ላንድ ክሩዘር የኮድ ቁጥሩ አራት ሆኖ ኮዱ “ኦሮ.“ ይላል – ኦሮሚያ ለማለት፡፡ እንደዚህ ያለ ታርጋ አሰጣጥ አይቼም ሆነ ሰምቼ ስለማላውቅ አጠገቤ የነበረን ባለመኪና ጠየቅሁ፡፡ እርሱም  እንደኔው ግራ የተጋባ ዜጋ ኖሮ “በዚህ ትደነቃለህ ወንድሜ፣ ሁሉም ነገር እኮ ተምታትቶብናል!” አለኝና እንደኤሊ ይንፏቀቅ የነበረው ጭንቅንቅ መንፏቀቅ ስለጀመረ ተለያየን፡፡ አዲስ አበባም ሆነች ኢትዮጵያ ወሬኛና ብሔርን ከብሔር ጋር በማጋጨት እንጀራውን የሚጋግር ቱልቱላ እንጂ የተግባር ሰው አልፈጠሩምና በተለይ አዱ ገነት ልትፈነዳ ደርሳለች፡፡ የሰው ብዛት አይነሣ፡፡ መንገዶች በበቂ ሁኔታ ስለሌሉን ምንም እንኳን በመኪና ብዛት እጅግ አነስተኛ የመኪና ቁጥር ካላቸው ሀገራት ውስጥ ብንካተትም ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ በመኪና ከመንቀሳቀስ በእግር መጓዝ የሚሻልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ይታይህ እንግዲህ – እሳት ቢነሳ፣ በሽተኛ በአምቡላንስ ቢጫን፣ አንድን አካባቢ የከተማ ሽፍታና ወምበዴ ቢወርና ባንክ ቢዘርፍ፣ ጠብና ሁከት ቢነሳ ወዘተ. እንዴትና በምን ተሄዶ ችግርን በወቅቱ መፍታት እንደሚቻል አስበው፡፡ የተሳሰረና የተመሰቃቀለ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ ኢትዮጵያ ታስፈራለች፡፡ በጣም ታስፈራለች፡፡ ዕረፍት በማይሰጥ ማኅበረሰብኣዊና ፖለቲካዊ ወጀብ የምትናጥን ሀገር መምራት ደግሞ በእጅጉ ያሳፍራል፤ የቦሌን መንገድና ሕንጻ አይተህ ኢትዮጵያን እንዳደገችና እንደበለጸገች ብትቆጥር የጅሎች ጅል ነህ፡፡ ቁርስ እንደምንም ቀምሰው ምሣና እራት ለማግኘት ገደል የሚሆንባቸውን በርካታ ሚሊዮን ዜጎች ከዘነጋሃቸው አሁንም የሞኞች ሞኝ ነህ፡፡ እኔኑ በጠራራ ፀሐይ እየዘረፉ በአንድ አዳር የሚከብሩ የጥቂት ሞልቃቃ ሀብታሞችን ኑሮ አይተህ እኔንም እንደነሱ ካሰብከኝ ሳይረፍድብህ ወደሚቀርብህ የአእምሮ ህክምና ማዕከል ሂድና ተመርመር፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2020 የኅልውና ችግር ከሚገጥማቸው አገሮች ተርታ ኢትዮጵያን ሦስተኛ አደረጓት እንጂ አንደኛነትን የሚቀማት ሊኖር አይችልም፡፡ የመንና ሦርያ ወይም አፍጋኒስታንማ የለየላቸው ስለሆኑ በዚህ ጥናት ከመነሻው ሊካተቱ ባልተገባ፡፡

የተለመዱ ጥያቄዎችን ልጠይቅ፡፡ ምን እየሆነ ነው ያለው? ወዴት እየሄድን ነው ያለነው? ፌዴራል መንግሥት ተብዬው  የት አለ? ዶክተር አቢይ የት ነው ያለው? ምን ውስጥ ገብቶ ይሆን ሀገሪቱ እንዲህ የመደዴዎች መጫወቻ ስትሆን አጮልቆ እያዬ አስችሎት ዝም ብሎ የተቀመጠው? ለመሆኑ ኢትዮጵያ መንግሥት አላት ማለት ይቻላል አሁን? የሕዝብን እሮሮ ሳያዳምጡ አራት ኪሎ ተደብቆ ሀገርን መምራት ይቻላል ወይ? ኢትዮጵያ ያለችው እኮ በአርትስ ቲቪና በአንዳንድ የዋሃን ኤፍ ኤም ራዲዮኖች እንጂ በተግባር እንዳለች መቁጠር አንችልም፡፡ ኑሯችን የነሲብ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱን ተውት፡፡ የሽሮ ጥሬ ራሱ ብር 70 እንደገባ ሰምቻለሁ፡፡ በዚህ የኦህዲድ/ኦነግ ዘመን የምንይዘው ቀፎ  አንድ መቶ ብር ያለው ዋጋ ከወያኔ አሥር ብር፣ ከደርግ ሁለት ብርና ከአፄዎቹ ዘመን ስሙኒ በእጅጉ ያንሳል፡፡ በወር የ600 እና 700 ብር ደሞዝተኛ መኖሩን ደግሞ አትርሣ፡፡ መራራ ቀልድ የሚቀለድባት ሀገር ሆናለች ኢትዮጵያ፡፡ መንግሥትም ሆነ የግል ቀጣሪ ድርጅቶች በሀገሪቷና በሕዝቡ ላይ ጭፍግ ተውኔት ደርሰው እየተወኑ ናቸው፡፡ ለነገሩ ይበሉን፡፡ ለማንኛውም እርግጫ የምንመች ጌኛዎች ስለሆንን ማንም ደንቆሮና ማይም እየመጣ በንፍጥ ጭንቅላቱ ይጫወትብናል – እኛ ደግሞ መርዙ እስኪዋሃደንና እስኪያፈዝዘን ድረስ በጭብጭባ እጃችንን እያጋልን እንደግፋለን፤ ጭብጨባ ሰውን የሚያነሆልልባትና ሞትንና እርጅናን ሳይቀር የሚያስረሳባት በውጤቱም ከሃዲዎችና ዘረኞች፣ ሙሰኞችና ሆዳሞች እንደ አሸን እየፈሉ የሚሄዱባት ሀገር ስላለችን እባካችሁን ለራሳችን አንዴ እናጨብጭብ፤ ኮራም እንበል! ለማንኛውም መጪውን ጊዜ ከኦህዲድ ጋር ጥሩ የጭብጨባና የኩራት ጊዜ ያድርግልን፡፡ “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ” ነው ተረቱም፡፡ 

አንድ ከተማ የሁለት ሀገር ዋና ከተማ ሊሆን ፈጽሞውን አይችልም፡፡ አዲስ አበባ አንዱን መምረጥ አለባት፡፡ አንድም የኢትዮጵያ አለዚያም የኦሮሚያ፡፡ ለሁለት ጌቶች መገዛት እንደማይቻል መጽሐፉ የሚገልጸው ለዚህ ነው፡፡ አንዱ ሲስብ ሌላው ይጎትታል፡፡ አንዱ ሲከለክል ሌላው ይፈቅዳል፡፡ አንዱ ኑ ሲል ሌላው ሂዱ ይላል፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ እንኳንስ ተቃራኒ ኃይሎችና ተመሳሳይ ኃይሎችም በሁለት ጎራ ከፍለው ወይም በአንድ ጊዜ ወይም በየተራ ሊገዟት አይችሉም፡፡

በአዲስ አበባ ውስጥ ኦሮ የሚል ታክሲ በፈለገው ቀለምና በፈለገው ሞዴል የትም እንደልቡ ይንቀሳቀሳል – በኩራት እየተጀነነና ትራፊኮችን እያስፈራራ ሳይቀር፤ ማን ነክቶት! ብር 20 ሽህና ከዚያም በላይ ለባለሥልጣናት ጉቦ እየተከፈለ በቀላሉ ፈቃድ በማውጣት በአዲስ አበባ መርመስመስ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ መስተዳድር በጥብቅ ህግና ትዛዙ ሌሎችን ቀፍድዶ ስለሚይዝ ዜጎች ክፉኛ ተቸግረዋል፡፡ኢትዮጵያውያን በገዛ ሀገራቸው የእንጀራ ልጅና የእውነት ልጅ ሆነው በሁለት አገዛዝ በአንድ ከተማ ውስጥ ሊኖሩ ተገደዋል – አንድኛቸው በፍርሀት እየተንቀጠቀጡ ሌላኛቸው ሌሎችን እያሽቆጠቆጡ፡፡ የታሪክ ፍርድ ለካንስ እንደዚህ ብሽቅ ነው እናንተዬ! 

ሰሞኑን ደግሞ ቤት እንደሚፈርስ ተገልጾኣል፡፡ የማን ወይም የነማን ቤት ሊፈርስ እንደሚችል ለማወቅ ተኝቶ ማለምን አይጠይቅም፡፡ በጣም ግልጽ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዙሪያ በዚያን ሰሞን እነእንትና በፌዴራሉና በኦሮሚያ ፖሊስ ታጅበው የነማንን ቤት እንዳፈረሱ ግልጥ ነው፤ እነማን የነማንን ኮንዶምንየም እንደዘረፉ ግልጥ ነው፤ እነማን የአዲስ አበባን መሬት እየተቀራመቱ ባወጣ እየቸበቸቡት እንዳሉ ለመሬታውያን ብቻ ሳይሆን ለሰማያውያንም ግልጥ ነው – ግን ወዮ ለነዚህ ደናቁርት ማጣፊያው በሚያጥራቸው ቀን፡፡ አጋሰሱ ኦነግ ኢትዮጵያን ለብቻ የመቆጣጠር ቅዠቱን በተግባር እያሳዬ ነው፡፡ ኦህዲድን ያሽመደመዱትና በዘረኝነት ልክፍት ያሰነካከሉት እንጃዋር እግዜር ይይላቸውና ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያ ለይቶላት ፈራርሳለች፡፡ መፍረስ ሁሉ በዐዋጅ እንዲደግፍ መጠበቅ ደግሞ የዋህነት ነው፡፡ የሚሠራውን ሁሉ ስታዩት ያስበረግጋችኋል፡፡ እናም ከዚህ በላይ መፍረስ ካለ የቃሉን ትርጉም አላወቅነውም ማለት ነው፡፡ ኦህዲድና ውኃ ሲወስዱ እያሳሳቁ ነው፡፡ ስንገርም ግን!

ይሄ ሁሉ ኦነጋዊ ብልግና ከዚህ የከፋ ሀገራዊ ትርምስና ዕልቂት እንዳያስከትል እፈራለሁ፡፡ የዱባን ጥጋብ የምናውቅ አንጋፋ ዜጎች የኦነግን ጰራቅሊጦሳዊ የጉሽ ጠላ ስካር እየታዘብን መዳረሻችንን ሳይሆን የአካሄዳችንን የጎንዮሽ ውጤት ብንፈራ አይፈረድብንም፡፡ ኦነግን ለዚህ ያበቃው የወያኔ ጥጋብና ዕብሪት መሆኑን የምናስታውስ ደግሞ የኦነግን ማብቂያ መተንበይ በጣም ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን አንድ የዕብሪት ጎማ እስኪተነፍስ ስቃይ አለ፤ ልጅ ያለ ምጥ ሞትም ያለ ጣዕር አይመጡም፡፡ ደስታ ያለ ሀዘን፣ ብርሃንም ያለ ጨለማ ዋጋ ሊተመንላቸው አይችልምና ለማንኛውም መልካም ነገር የሚፈጸም ክፍያ አለው፡፡ አሁን ወዳለው ደረጃ ለማድረስም ቢሆን የወያኔን ጥጋብ ለማስተንፈስ የተደረገውን ርብርብና መስዋዕትነት አንርሣ፡፡ ያለ መስዋዕትነት የሚጠገን መኪናም ሆነ የሚተነፍስ ጎማ የለምና አሁንም እንደምንጊዜውም ሁሉ የምለው በንጹሕ ልቦና ወደ ፈጣሪ እንጸልይ ነው፡፡ ከፈጣሪ በራቅን ቁጥር የምንጠጋው ተቃራኒው ወደሆነው ሰይጣን ነውና ከፈጣሪያችን ጋር ብዙም ሳይረፈድብን እንታረቅ፡፡ የአንድ ሰው ጸሎት ቀላል አይደለምና በሚታዩት ሶዶም ወገሞራዊ ድርጊቶች ሳንደናገጥ የየበኩላችንን ጸሎትና ምህላ እናድርስ፡፡ ማን ያውቃል የራሔልን ዕንባ ያበሰ ጌታ የኛንም ያብስልናል፡፡ እነአናንያን፣ አዛሪያንና ሚሳኤልን ከእሳት ላንቃ ያወጣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ዳንኤልን ከአንበሣ ትናጋ ያወጣ አምላከ ኢትዮጵያ፣ አፎምያን ከደራጎን ነበልባላዊ ላንቃ ያላቀቀ የጌቶች ጌታ የእሳካሁኑ በቃችሁ ብሎ በአመክሮ ከገባንበት አዘቅት ሊያወጣን ይችላል፡፡

 

EMAIL: ma74085@gmail.com)

Filed in: Amharic