>

የጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ትውስታ በስራ ባልደረቦቹ አንደበት!

የጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ትውስታ በስራ ባልደረቦቹ አንደበት!!!

በትናንትናዉ ዕለት ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ስላጣነዉ የእግርኳስ ጋዜጠኛ፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ፣ የሰብዐዊ መብት ተሟጋችና በብዙ ዘርፍ ላይ ሁለገብ እዉቀት ስለነበረዉ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ (ኢብሮ ) ጽፌ ነበር። የሙያ ባልደረቦቹ ሌሎችም ስለእሱ ምን ብለዉ ነበር እነሆ ለትውስታ፦
በፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ በስደት ከአገር
ወጥቶ መሞቱ እጅግ ልብ ይሰብራል!
ሕይወት እምሻው – ደራሲ
የኢብራሂም ሞት በጣም አስደንጋጭ ሆኖብኛል፡፡ ለስፖርት እምብዛም ነኝ፡፡ ስለስፖርት የተፃፈ ብዙ አላነብም፡፡ ኢብራሂም ከፃፈው ግን እንደወጥ የፈጠራ ፅሁፍ አነበው ነበር፡፡ አፃፃፉ ከጎል ቆጠራ እና ከውጤት መረጃዎች የዘለለ ነው፡፡ ስፖርትን በከፍተኛ የመረጃ ጥራት ይፅፋል ያወራል፡፡ ስለዚህም ስፖርት ላይ ያን ያህል የጋለ ስሜት ባይኖረኝም ግን እሱ በየጊዜው የሚፅፋቸውን ነገሮች ተከታትዬ አነብ ነበር፡፡ የሚያስተምሩ አዳዲስ መረጃዎችን የማገኝባቸው ስለነበሩ ነው፡፡
በስደት ላይ መኖሩ ሳይሰጨንቀው በአገሩ ጉዳይ ላይ ያለውን ስሜት በማህበራዊ ሚዲያዎች ይገልፅ ነበር፡፡ ወቅታዊ አጀንዳ ስለሆነ የሆነ ነገር ማለት አለብኝ ብሎ የሚፅፍ አልነበረም፡፡ ከአንጀቱ ውስጥ አውጥቶ የሚፅፈው በልቡ ያለውን ነገር ለማስረዳት ለመግለፅ እንደሚጥር ነው እረዳ የነበረው፡፡ በሚያምንበት ነገር ላይ አቋሙን ሲያንፀባርቅ የብዙ ሰዎችን ድጋፍ ባያስገኝለት እንኳን፤ ያን ሳይፈራ ለራሱ ታማኝ ሆኖ ነበር የሚፅፈው፡፡ በአጠቃላይ እሱን ማጣት እንደአገር ብክነት ሆኖ ይሰማኛል፡፡ በጣም ወጣት፤ ብዙ ነገር መስራት የሚችል ስለነበር ነው፡፡ በፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ በስደት ከአገር ወጥቶ መሞት እንደ አገር በጣም የሚያሳዝን ሆኖብኛል፡፡
ማህበራዊ ሃላፊነት የሚያንገበግበው፤ ይህንንም በተለያዩ ፅሁፎቹ የሚያንፀባርቅ ነበር፡
ኤልሳቤጥ እቁባይ
የቀድሞ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛና የሰፈሩ ልጅ
ኢብራሂምን ባለገሃርና ጨርቆስ መሃል በነበረው የድሮ ሰፈራችን ሳስታውሰው በቆመበት ሁሉ በህፃናት፤ በወጣት ተከብቦ ነው፡፡ ትልቅ ትንሽ ሳይል በእድሜ ደረጃ ሳይወሰን ከሁሉም ሰው ጋር ተግባብቶ ማውራት መጫወት ይችልበት ነበር፡፡ የሰፈሩ አድባር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከድሮ ጀምሮ የማውቀው አንባቢነቱን ነው፡፡ ቤተሰባቸው ስጋ ቤት ስለነበራቸው እዚያ ለመጠቅለለያ የሚመጣ ጋዜጣዎችን በፍቅር በሚያነብበት ዝንባሌው አስታውሰዋለሁ፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ምርጥ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ እንደነበርም ነው የማውቀው፡፡ በተለይ ለመመረቂያው የሰራው በ“ሃይድሮ ፖለቲክስ” ላይ ያተኮረ የጥናት ወረቀቱ ዛሬም ድረስ እንደ ግብዓት የሚጠቀስ መሆኑ የነበረውን እውቀት እና ጉብዝና ያመለክታል፡፡
ሁለገብ ባለሙያ ነው፡፡ የስፖርት ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም፡፡ ማህበራዊ ሃላፊነት የሚያንገበግበው፤ ይህንንም በተለያዩ ፅሁፎቹ የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡ በጥልቀት እያሰበ የሚሰራ የፖለቲካ ተንታኝም ነበር፡፡ ምክንያታዊ ሰው ነበር፡፡ በአስተሳሰቡ ጨዋታ ከሌለ ጨዋታው አይኖርም የሚል ነበር፡፡
‹‹ስለስፖርት የተፃፈ ብዙ አላነብም፡፡ ኢብራሂም ከፃፈው ግን  አነበው ነበር!!!››
መንሱር አብዱል ቀኒ
የብስራት ስፖርት አዘጋጅ በብስራት ኤፍኤም 101.1
የቀድሞው የኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ
ኢብራሂም እግር ኳስና ጋዜጠኝነት ያዋሃደ ምርጥ ባለሙያ ነበር፡፡ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር ከጋዜጠኝነቱም በፊት የነበረ ነው፡፡ ሰፈራችን ለስፖርት በተለይም ለእግር ኳስ የቀረበ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ስታድዬም በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን እውቅ ኳስ ተጨዋቾች፤ የስፖርት ጋዜጠኞች እና ስፖርት አፍቃሪዎች የሚኖሩበት ነው፡፡ እኔ የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ ኢብሮ ግን ሁሉንም ስፖርት በፍቅር የሚወድ ሁለገብ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ለስፖርትና ለሌሎች ጉዳዮች ያለው የጠለቀ ፍላጎት፤ የስራ ፍቅርና ትጋት የሚገርም ነበር፡፡ በጣም ትሁት፤ ፍፁም ታዛዥ፤ ተግባቢ ባህርይም ነበረው፡፡ ይህንን የሚያውቁት ሁሉ የሚመሰክሩት ነው፡፡ በማህበራዊ ህይወቱ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅርበት የመግባባቱን ያህል ከስፖርት ቤተሰቡም ጋር ባለው ግንኙነት የቅርብ አማካሪ የነበረ ነው፡፡ ጋዜጠኞችን፤ ተጨዋቾችን፤ አሰልጣኞችን ያማክራል፡፡ ሃሳብ እየተሟገተ መወያየት ይወዳል፡፡ ኢብሮ የሚመክረውና የሚወያየው የጠለቀ እውቀቱን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ እኔ ብቻ ነው የማውቀው የሚል አልነበረም፡፡ አማራጭ ሃሳቦችን ምክንያታዊ ሆነህ ስትነግረው የሚቀበል፤ በሃሳብ ፍጭትና ሙግት
ከኢብራሂም ጋር በኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ላይ ለ9 ዓመታት አብረን ሰርተናል፡፡ ከሚያስደንቁኝ ተሰጥኦዎቹ ዋንኛው ልዩ የማስታወስ ችሎታው ነበር፡፡ ይህን የማስታወስ ችሎታውን በአንድ ምሳሌ ማረዳት ይቻላል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች የነበረው ፍራንሲስ ኦሙላኩ በአንድ ወቅት ሁለት ስም እንደነበረው ለሁላችንም ነገረን፡፡ በፈለገው ጊዜ ሁለቱንም ስሞች ማስታወስ የሚችለው እሱ ብቻ ነበር፡፡ በጋዜጣ ስራችን ደግሞ ብዙ ሰነዶችን ማስቀመጥ ባልተለመደበት አገር የተለየ የማስታወስ ችሎታ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ታውቀዋለህ፡፡ ኢብራሂም ያለው የማስታወስ ችሎታ በጣም የላቀ ከመሆኑ የተነሳ በብዙ ሰው እንደተለመደው በማስታወሻ አጫጭር ነጥቦችን አይዝም፤ ሁሉንም ነገር በቃሉ የማስታወስ፤ ከአዕምሮው በቀጥታ አፍልቆ የመፃፍና ሃሳቡን የመግለፅ ችሎታ ነበረው፡፡
ኢብራሂም በስፖርት ጋዜጠኝነት ለረጅም ጊዜ እንደመስራቱ ለስራ ብዙ የውጭ ጉዞዎችን አላደረገም፡፡ ሁለት ዓለም ዋንጫዎችን በ2010 እኤአ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በ2014 እኤአ በብራዚል የተደረጉትን ብቻ ወደ የአገሮቹ ተጉዞ ለመታደም እና ልምድኑም በጥልቅ ትንታኔ በማጀብ ስኬታማ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
ኢብራሂም ሌት ተቀን የሚሰራ፤ ትንሽ እንቅልፍ የሚተኛ እንጅ የተለየ እረፍት የሚያደርግ ሰው አልነበረም፡፡ የጋዜጣ ስራ እንደምታውቀው በየሳምንቱ ተደጋጋሚ ስራ ውስጥ ስለሚያስገባህ ጊዜ አየለህም፡፡ በቂ የጥሞና ጊዜ አግኝተህ በመፅሃፍ መልክ አዘጋጅተህ ለማሳተም እድሉን የሚፈጥርልህ አይደለም፡፡ በስፖርቱ የሚያልፉ ታዋቂ ሰዎችን የሚዘክር ‹‹የዝና መዝገብ›› በአገራችን ስፖርት ላይ መጀመር አለበት፡፡
‹‹እግር ኳስ ላይ በጣም ብዙ አንብቧል፤ የራሱ ጥናትና ምርምርም ያደርግ ነበር!››
ጋዜጠኛ ግሩም ሠይፉ
ኢብራሂም ሻፊ አህመድ በጋዜጦችና መጽሔቶች በሚፅፋቸው፤ በራድዮና በቲቪ በሚያቀርባቸው የስፖርት ትንተናዎች ይታወቃል፡፡ በጣም ምርጥ ስብዕና ያለው ሁለገብ ሞያተኛ ነበር፡፡ በፖለቲካ ሳይንስ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነት የባችለር ዲግሪ ነበረው ፤ የሲቪክ መምህር ሆኖ ከማገልገሉም በላይ በትምህርት ቢሮ ውስጥ በአስተዳደር ሥራም ሰርቷል፡፡ በተለይ ግን ከ20 ዓመታት በላይ ባገለገለበት የስፖርት ጋዜጠኝነቱ በነበረው የላቀ ብቃት እና የመጠቀ እውነት ከፍተኛ ክብር አትርፏል፡፡ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በዋና አዘጋጅ ደረጃ፤ በቋሚ አምደኛነት እና የቅርብ አማካሪነት ያገለገለ ነበር፡፡ በስፖርት ጋዜጠኝነቱ በሳልና ጥልቀት የሞላበት ስራ ሲያከናውን ኖሯል፡፡ በህትመት፤ በብሮድካስት እንዲሁም በኦንላይን ሚዲያዎች ፈርቀዳጅ ነበር፡፡ በተለይ በኤፍ ኤም ራድዮ ጣቢያዎች ዙርያ ለተፈጠሩ ልዩ ልዩ የስፖርት ፕሮግራሞች፤ የቀጥታ ስርጭቶችና ውይይቶች ጀማሪነት ከስማቸው ከሚነሳ የስፖርት ጋዜጠኞች ትውልድ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስም ነው፡፡ ለእግር ኳስ ባለው ፍቅርና ጥልቅ ትንተናው የስፖርት ቤተሰቡን ተዓማኒነትና ከበሬታ ሊያተርፍም የቻለ ነበር፡፡ በማናቸውም ጉዳይ ላይ በቁምነገር መወያየት የሚችል ፤ በምክንያት በታጀቡ ውይይቶች የተፈለገውን ያህል ለመሟገት የማይቸገርና የማይከብድ ስብዕና ያደለው፤ አገሩን ያለገደብ የሚወድ ነበር፡፡ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ
‹‹ኢትዮጵያ አንጋፋ፤ አስተዋይና በሳል የስፖርት ጋዜጠኛ አጥታለች!!!››
ጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመ
ኢብራሂም በህትመት፤ በብሮድካስት እንዲሁም በኦንላይን ሚዲያዎች ላይ በስፖርቱ ላይ በማተኮር በሚሰራበት ወቅት ምልከታዎቹ የሚያስደንቁ ነበሩ ፡፡ በራድዮ ስሰማውና በቲቪ ስመለከተው ይመስጠኝ ነበር ግርማ ሞገስ ካለው ጎርናና ድምፁ ጋር አቀራረቡ የሚማርክ ነበር፡፡ ታታሪ ባለሙያ ስለነበር በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ለጥልቅ የስፖርት ትንተናዎች ጆሯቸውን እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ ተግባቢ፤ ጨዋታ አዋቂ፤ እንደ ወንድምና ጓደኛ የምትቀርበው በምክንያታዊነቱ የማደንቀው ሰው ነበር፡፡
ኢብራሂም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በአዲስ መልክ ሲመሰረት በስራ አስፈፃሚነት ከተመረጡት አንዱ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በላይ አብሮን ሲሰራ ማህበሩን በዘላቂነት የሚጠቅሙ ብዙ ተግባራትን አከናውኖ ነበር፡፡ የማህበሩ ስራ አስፈፃሚዎች በየወሩ በምናደርጋቸው መደበኛ ስብሰባዎችና በየጊዜው በምንገናኝባቸው መድረኮች በጣም በሳል ሃሳቦችን እያቀረበ ከልቡ የሚያገለግል ነበር፡፡ ማህበሩ ለአባላቱ ጥቅምና መብት እንዲቆም በነበረው ፅኑ ፍላጎትም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ተንቀሳቅሷል፡፡ የስፖርት ጋዜጠኞች በሚኖሯቸው የተለያዩ እድሎች አጠቃቀም ዙርያ ፍትሃዊ አሰራር እንዲዘረጋና መብቶቻቸውን ለማስከበር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በማጠናከር ወሳኝ ሚና ነበረው፡፡ የስፖርት ጋዜጠኞች ስራዎቻቸውን በትክክለኛ እና በተረጋገጡ መረጃዎች እንዲያከናውኑ በማሳሰብ፤ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በማክበር በመልካም ስነምግባር እንዲከውኑ በማነሳሳት፣ ሙያ እና ሙያ ላይ ብቻ ትኩረት እንዲኖራቸው በማበረታታት፤ የመረጃ ምንጮቻቸውን በተገቢው መንገድ በመጥቀስ የሚሰሩበትን ባህል በመፍጠር የሚተጋም ነበር፡፡
‹‹በስፖርቱ የሚያልፉ ታዋቂ ሰዎችን የሚዘክር ‹‹የዝና መዝገብ›› በአገራችን ስፖርት ላይ መጀመር አለበት!!!››
ምስጋናው ታደሰ
የስፖርት ጋዜጠኛና በኢትዮ ኤፍኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት አዘጋጅ
ኢብራሂም በጣም የምወደውና የማከብረው የሙያ አጋሬ ስለነበር በመሞቱ ከፍተኛ ሃዘን ተሰምቶኛል፡፡ በአገኘው አጋጣሚ ሰዎችን ለመርዳት የሚፈልግ ጥሩ ሰው ነበር፡፡ የሚያምንበትን በግልፅ የሚናገር፤ ለሙያው መስዕዋትነት በመክፈል ብዙ ለውጥ የፈጠረ፤ የስፖርት ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ተንታኝም የነበረ ነው፡፡ በወንድምነቱ፤ በምርጥ የስፖርት ጋዜጠኝነቱ እና ትንታኔው ሁሌም ሳስታውሰው እኖራለሁ፡፡
ኢብራሂም እግር ኳስ ላይ በጣም ብዙ አንብቧል፤ የራሱ ጥናትና ምርምርም ያደርግ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግር ምንድነው? እንዴት ሊቀረፍ ይችላል ?እንዴት ሊያድግ… ሙሉ በሙሉ ሊለወጥ ይችላል? በሚል ብዙ ጥናቶችን አድርጓል፡፡ ለስፖርቱ ማደግ ይበጃሉ የሚላቸውን ሃሳቦች በልዩ የሙያ ፍቅርና ትጋት ሲገልፅ የነበረ ነው፡፡
ኢብራሂም በእግር ኳስ የስልጠና ስራዎች ዙርያም ልዩ ፍላጎት ነበረው፡፡ በሰፈሩም ታዳጊዎችን እየሰበሰበ ያሰራ እንደነበር አስታውሳለሁ በሚኖርበት አካባቢ አሰባስቦ ከጅምሩ አሰልጥኗቸው ለክለብ ደረጃ የበቁ ልጆችም አሉ፡፡ በሰፈሩ በጣም የሚወደድ እና የሚከበር መሆኑንም ነው የማውቀው፡፡ በእድሜው ከእሱ የበለጡ ትልልቅ ሰዎችን ሲጣሉ ሽማግሌ ሆኖ የሚያስታርቅም ነበር፡፡ ኢብራሂም ለበርካታ የክለብ ተጨዋቾችም የቅርብ አማካሪ ነበር፡፡ ተጨዋቾች የስነልቦና ችግር ሲገጥማቸው፤ ጎል ማግባት ሲያቅታቸው፤ ክለባቸው በየጊዜው ውጤት ሲበላሽበት በቅርበት ሆኖ እየመከረ የራሳቸውን ጥረት እንዲያሳድጉ ይደግፋቸው ነበር፡፡
በኳስ ላይ በስታድዬምም ሆነ በቴሌቭዥን ከኢብሮ ጋር ሆነህ ጨዋታ ስትመለከት በአሰላለፍ፤ በተጨዋቾች አቀያየር፤ በዳኞች ውሳኔ በቡድኖች ታክቲክና የአጨዋወት ጥንካሬ የሚሰጣቸው አስተያየቶች በጣም የሚማርኩ ናቸው፡፡ የሚያደርጋቸው ትንታኔዎች ከባለሙያዎቹ ውሳኔዎች እና ድርጊቶች ጋር የሚስማሙ መሆናቸው ያስገርምሃል፡፡ ጨዋታዎችን በሜዳ ላይ ከሜዳ ውጭም በሚያነብብት እይታው የእግር ኳስ ሳይንሱ በደንብ ገብቶታል፡፡ በቡድኖች አሰላፍ እና ታክቲክ ስትከራከረው ሊገባባህ የሚሞክረው ወረቀት ላይ ንድፉን ሰርቶ እየተነተነ ነው፡፡ ብራዚል 20ኛውን የዓለም ዋንጫ ባዘጋጀችበት ወቅት ከመሄዱ በፊት እና ከሄደም በኋላ በዓለማችን ትልልቅ ብሄራዊ ቡድኖች ዙርያ አብረን ቁጭ ብለን ስንወያይ የሚየላቸውን ውጤታማነት በሚተነበይበት የጠለቀ እውቀቱ በጣም እደነቅበት ነበር፡፡
‹‹የሚያምንበትን ነገር ያለምንም መቆጠብ የሚናገርና የሚፅፍ ነበር፡፡ መለየቱንም በግልፅ የሚያስቀምጥ ነው!!!›
ሀና ገብረ ሥላሴ
የኦሊምፒያድ ዋና አዘጋጅ በኤፍኤም አዲስ 97.1
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት
ኢብራሂምን በምሰራበት የስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያ ተምሳሌቶቼ ከምላቸው አንዱ ነው፡፡ በመጀመርያ ያወቅኩት በኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ላይ ከእነመንሱር ጋር ሲሰራ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በአዲስ ጉዳይ መፅሄት፤ በእንዳልክና ማህደር ራድዮ ፕሮግራም… በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በትጋት ሲያገለግል በአድናቆት ስከታተለው ነበር፡፡ በተለይ በራድዮ ላይ በስፖርት ውይይት ከእነመንሱር፤ ፍስሐ ተገኝና ሌሎችም ጋር ሆኖ ሲሰራ ብዙ ፈርቀዳጅ ምዕራፎችን ሊከፍት የቻለ ነበር፡፡ የእነሱ ትውልድ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ላይ አዲስ ነገር ይዞ የመጣ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን በስፖርት ጋዜጠኝነት ውስጥ ካለነው ብዙዎቻችን በእነሱ ተፅእኖ እንደመጣንና እንደተነሳሳን ነው የማስበው፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ሊጎች አሁን የተፈጠረው ተወዳጅነት እና ትኩረት በስፖርት ጋዜጠኝነት የእነሱ ትውልድ መቆም የተፈጠረ ነው፡፡ ከዲኤስቲቪ ያልተናነነሰ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ስለ ሁሉም ክለቦች የታክቲክ፤ የስነልቦና፤ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ያገባኛል በማለት እግር ኳስን በልዩ ፍቅር የሚከተል ትውልድ እንዲፈጠር እነ ኢብራሂም ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
የሲቪክ መምህር እንደመሆኑ እግር ኳስን ከእግር ኳሳዊ ቅኝቱ ባሻገር የማየት ተሰጥኦውን ፈጥሮለታል፡፡ በተለያዩ ስፖርታዊ ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ውይይቶች የሚያቀርባቸው የማጠናከርያ ሃሳቦች ከማህበረሰባዊና ከኢኮኖሚያዊ አቅጣጫዎች አንፃር የሚቃኙ መሆናቸው ልዩ ሚናውን አጉልቶ የሚያሳይ ነበር፡፡
ከስደቱ በፊት በጋዜጣና መፅሄት ላይ ሲፅፍ፤ በራድዮ ላይ ሲያወራ የሚጠቃቅሳቸው ነጥቦች በቃሉ አስታውሶ የመናገር ችሎታ ያስደንቀኝ ነበር፡፡ ስፖርታዊ ጉዳይን ካነበበው ታሪክ፤ መረጃውን ያገኘበትን ምንጭ፤ አጋጣሚና ሁኔታ በማንኛውም ወቅት በዝርዝር አስታውሶ መተንተን ይችልበት ነበር፡፡ ትክክለኛ መረጃዎችን መጥቀስና መጠቆም ይወዳል፡፡ የመፃፍ ችሎታውም የላቀ ነው በስነፅሁፉ ማራኪነትም የሚመስጥ ነበር፡፡
ሃሳቡን በነፃነት የሚገልፅ በመሆኑ ከብዙ አካላት ያጋጨው ነበር፡፡ በአጠቃላይ የሚያምንበትን ነገር ያለምንም መቆጠብ የሚናገርና የሚፅፍ ነበር፡፡ መለየቱንም በግልፅ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ በሃሳብ ደረጃ ብዙ ልዩነቶች እንኳን ቢኖሩትም በመወያየት እና በመነጋገገር የሚያምን ነበር፡፡
‹‹በስፖርት ላይ ብቻ ያልተገደበ ሁለገብ ባለሙያም ነበር፡፡ ስፖርትን ከማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ጋር በማያያዝ ተሳክቶለታል!!!››
ቆንጂት ተሾመ
የአዲስ ዜማ አዘጋጅ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1
የቀድሞዉ የሰንደቅ ጋዜጣ የስፖርት አምድ አዘጋ
ወደስፖርት ጋዜጠኝነቱ ሳልገባ በጣም ወጣት ሆኜ በዓለም ዋንጫ፤ በአፍሪካ ዋንጫ በሌሎች የቴሌቭዥ ስርጭቶች ላይ የሚሰጣቸውን አስተያየቶች በአድናቆት እከታተል ነበር፡፡ ከዚያም በፊት በኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ላይ የሚፅፋቸውን ዘገባዎች በጣም አነብም ነበር፡፡ ወደ ስፖርት ጋዜጠኝነቱ ከገባሁ በኋላ ከኢብራሂም ጋር በቅርበት የተዋወቅኩት በ2010 ላይ ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ አብረን ተጉዘን ለአንድ ወር ያህል ባሳለፍነው ቆይታ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ ወቅት አብረን ተቀምጠን በምንመለከታቸው ጨዋታዎች ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰጣቸው ትንታኔዎች የማይረሱኝና ብዙ ያስተማሩኝ ናቸው፡፡ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በደንብ ማንበብ ይችላል፡፡ እንዲህ ቢያደርጉ ብሎ የሚሰጠው አስተያየት ከአሰልጣኞች ውሳኔ ጋር ይጣጣምለት ነበር፡፡
ኢብራሂም ሁልግዜም የሚያውቀውን ነገር ለማካፈልና ለመስጠት የማይሰስት ሰውም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በተመለሰበት ወቅት ለአስልጣኝ ሰውነት ቢሻውና ለዋልያዎቹ የቅርብ ድጋፍ በመስጠት ያበረከተውን ሚና መጥቀስ ይቻላል፡፡ በየጊዜው በሚፅፍባቸው ህትመቶች ለብሄራዊ ቡድኑ የሚጠቅሙ ሃሳቦችን በማንሳት፤ ለኢንስትራክተር ቢሻው በአሰላለፍ፤ በተቃራኒ ቡድኖች ወቅታዊ አቋም፤ በተያያዝ ጉዳዮች ላይ የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ አሻራውን እንዳሳረፈ ብዙዎቻችን እንመሰክራለን፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስልጠና ላይ አቋም ይዞ የሚሟገት፤ ከሌሎች ሃሳቦች ጋር በሚያደርጋቸው ፍጭቶች ብዙ የሚያስተምር ነበር፡፡ በስነፅሁፍ ችሎታው፤ በቋንቋ አጠቃቀሙም ተሳክቶለታል፡፡
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በአዲስ መልክ ከ6 ዓመት በፊት ሲደራጅ በስራ አስፈፃሚ አባልነት ሲያገለግል በርካታ መሰረታዊ ለውጦች እንዲፈጠሩም ምክንያት ሆኗል፡፡ የማህበሩ አባላትን አቅም በስልጠና ስለመገንባት፤ የልምምድ ልውውጥ መድረኮች እንዲፈጠሩ ፤ በማህበሩ እንቅስቃሴዎች ዙርያ አባላቱ በተለያዩ ሃሳቦች ተሟግተው የተሻለ ስራ እንዲያከናውኑ በነበረው አስተዋፅኦ የሚመሰገንም ነበር፡፡
ኢብራሂም በስፖርት ላይ ብቻ ያልተገደበ ሁለገብ ባለሙያም ነበር፡፡ ስፖርትን ከማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ጋር በማያያዝ ተሳክቶለታል፡፡ የሚፅፋቸውና የሚገልፃቸው ሃሳቦች ብዙዎችን የሚያሳምኑ በመሆናቸው ብቃት የሚያመለክት ነበር፡፡ ለአገሩ ያለው ፍቅር ልዩ ነበር፡፡ሰዎችን በሃይማኖት በፖለቲካ ወይም በዘር ሳይሆን የሚመዝነው በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ነበር፡፡
‹‹ምክንያታዊ ሰው ነበር፡፡››
Filed in: Amharic