>
4:50 pm - Tuesday May 17, 2022

እናንት ‹አረመኔ› (atheist) የብአዴን፣ የወያኔ፣ እና የኦህዴድ የ60ዎቹ ባለጠብመንጃ ትውልዶች ሆይ (አሰፋ ሃይሉ)

እናንት ‹አረመኔ› (atheist) የብአዴን፣ የወያኔ፣ እና የኦህዴድ የ60ዎቹ ባለጠብመንጃ ትውልዶች ሆይ፡- 

አሰፋ ሃይሉ
ዛሬ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ላለፉት አሰርት ዓመታት ሲዘራበት የኖረው ግፍ ሁሉ ተጠያቂነቱ ተጠቃልሎ በአንድ ግለሰብ እጅ ላይ ብቻ ተደፍድፎ ያረፈ እስኪመስል ድረስ ሁሉም የግፍ ተዋናይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲዘራ የኖረውን የዓመታት ግፍ ሁሉ፣ ሁሉንም ግፍና የሀገርና የወገን ክህደት ሥራውን ሁሉ፣ በወያኔ እና በጌታቸው አሰፋ ላይ ጠቅልሎ አላክኮ፣ ሁሉም በየፊናው ከደሙ-ንፁህ መሆኑን እየመሰከረ የዲሞክራሲ ብፁዕነት ካባውን ደርቦ፣ ደርሶ የዲሞክራሲ ገንቢና ለትውልድ አሸጋጋሪ ሆኖ እየተወነ ያለበት ሀገራዊ የፖለቲካ ተውኔት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡
በዛሬው የሀገራችን ትራጀዲያዊ የፖለቲካ ተውኔት ላይ የ60ዎቹና የ70ዎቹ የብአዴንና የኦህዴድ ‹‹ታጋይ›› ትውልዶች በአደባባይ ወጥተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹እነርሱ ከሳሽ፣ ወያኔ ተከሳሽ››፣ ‹‹እነሱ ለሀገር ተቆርቋሪ፣ ወያኔ ሀገር አጥፊ››፣ ሌላ ቀርቶ ‹‹እነርሱና የሻዕቢያው ኢሳያስ የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ ወያኔዎቹ ደግሞ የኢትዮጵያ ግፍና በደል ብቸኛ ተጠያቂ!›› ሆነው ቀርበውልናል፡፡
ሁሉም ሊክደው የማይችለው እውነታ ግን … ዛሬ ዲሞክራሲን ገንቢና ሰጪ ሆነው በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት የቆሙት የብአዴን እና የኦህዴድ የ60ዎቹ ‹‹ታጋዮች ነን›› ባይ ትውልዶች፣ ከወያኔ እኩል፣ ከሻዕቢያ እኩል፣ እና ከሌሎችም የኢትዮጵያን ህዝብ ደህንነትና አንድነት ከተፈታተኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እኩል – በዚህች ሀገር ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ለጠፋው የወገኖቻችን ነፍስ፣ ለፈሰሰው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ወገኖቻችን ደም፣ በጥይታቸው በልተው በየሜዳው ደመከልብ አድርገው ያለስምና ያለታሪክ ላስቀሩት የስንትና ስንት ሺኅ ኢትዮጵያውያን ቤተሰብ ሞትና መርዶ፣ በአጠቃላይ ላለፉት አሰርት ዓመታት በሀገራችን ላይ ለወረደው ስቃይና ሀዘን ሁሉ – አንዳቸውም ከሌላኛቸው ሳይለዩ – የምንግዜም የጋራ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡
የአያት የቅድመአያቶቹን የጀግንነት መንፈስ ተከትሎ ‹‹ሀገሬን፣ አንድነቴን፣ ባንዲራዬን›› ብሎ ከየቤቱ የወጣውን ያላለፈለት ምስኪን ኢትዮጵያዊ ወገናቸውን ህይወት ለበርካታ አሰርት ዓመትት በለኮሱት የጦርነት እሳት ሲማግዱ፣ ደሙን በየበረሃው ሲያፈሱ፣ አካሉን እንደ ውሻ ሥጋ በየተራራው ለአሞሮች ሲበትኑ የኖሩት እነዚያ በገራቸውና በህዝባቸው ላይ ታላቅ ክህደትንና ጥፋትን አንግበው የተነሱ የተረገሙ የ60ዎቹ የወያኔ፣ የብአዴንና፣ የኦህዴድ ትውልዶች ናቸው – በዛሬውም ትውልድ ዘመን – በመንግሥት የሲቪልና ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ – ከፍተኛዎቹን ሥልጣኖች ተቆናጥጠው እስካሁንም ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን – ዕድሜ ልካቸውን ተተብትበውበት በቀሩት እና ደም ሲገብሩና ሲያስገብሩ በኖሩበት የተረገመ የዘረኝነት ልክፍታቸው ነክረው እያመሷት ያሉት፡፡
ያንን እንደ ወራሪ ጠላት በየሜዳው ቀንጥሰው የጣሉትን የወገናቸውን አካል እንደ ታላቅ ጀግንነት ቆጥረው ነው ዛሬ ‹‹ያልተንበረከክነው›› ትውልዶች እያሉ የሚፎክሩት፡፡ በዚያ አሳፋሪና አሳዛኝ የክህደትና የአረመኔነት ታሪካቸው የወገናቸውን ደም ሲያፈሱ ለኖሩበት፣ ወገን በወገኑ ላይ ይፈጽመዋል ተብሎ ለማይገመተው አረመኔ የጭካኔ ታሪካቸው ነው በዛሬው ትውልድ ፊት ‹‹ሰማዕታት›› ሆነው የቀረቡትና የሰማዕታት ሃውልት እየተባለ የሚገነባላቸው፡፡
አንዴ በ60ዎቹ ዘመን በተለከፉበት የዘረኝነትና ኢትዮጵያን የማውደም ልክፍት ተጠምደው በወገናቸው የደም ጎርፍ ሲዋኙ የኖሩ እነዚህ የ60ዎቹ የኢትዮጵያ የእፉኝት ልጆች – ማናቸውም ከማናቸውም ሳይለዩ – ሁሉም እና እያንዳንዳቸው – የበደሉትን፣ ከጎናቸው አሰልፈው ያስጨፈጨፉትን፣ በጠላትነት ፈርጀው የጨፈጨፉትን፣ የገደሉትንና የተጋደሉትን ኢትዮጵያዊ ወገናቸውን ሁሉ – በይፋ እና በአደባባይ በአንድ ድምፅ ይቅርታ ጠይቀው፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሜዳ ለአዲሱ ከደሙ ንፁህ ለሆነ ትውልድ አስረክበው – ቀሪውን ህይወታቸውን በየእምነታቸውና በየህሊናቸው ጓዳ ተመልሰው በንስሃ ህይወት እንዲመላለሱ – የመጨረሻው የፖለቲካ ስንብት ካልተደረገላቸው በቀር – የዚህች ሀገር ፖለቲካ እና የዚህች ሀገር የዲሞክራሲ ጉዞ – በሠላማዊና ሀገራዊ ብልፅግናን በሚያመጣ መልኩ ወደፊት አንድ ጋት ይራመዳል ብሎ ማሰብ – የከንቱ ከንቱ የሆነ – ተምኔታዊ ምኞት ነው፡፡
እናንት ‹አረመኔ› (atheist) የብአዴን፣ የወያኔ፣ እና የኦህዴድ የ60ዎቹ ፖለቲከኞችና ባለጠብመንጃ ትውልዶች ሆይ፡-
እያንዳንዳችሁ በተናጠል እና ሁላችሁም በጋራ – ላጠፋችሁት የወገናችሁ ህይወት፣ ለሞቱት እና ልባቸው ተሰብሮ ለቀረው – ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ ጫፍ እስከ ምዕራብ ላሉት፣ እና በዓለሙት ተበትነው ላሉት – ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ሁሉ ከልባችሁ ይቅርታ ጠይቁ፡፡ ለዘመናት ስታቦኩ የኖራችሁትን የሀገሪቱን ፖለቲካ ለአዲሱ ትውልድ አስረክባችሁ የክብር ስንብትን ተሰናበቱ፡፡ ላለፉት 40ና 50 ዓመታት በኢትዮጵያችን በወገንና በወገን መሐል ባስነሳችሁት የእልቂትና መከራ እሳት ለተለበለበው፣ ላለቀውና ለቆሰለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ – አንዱን ሰማዕት፣ አንዱን እርኩስ ሳትሉ – ብሔራዊ የይቅርታና የእርቀሰላም ጥሪያችሁን አቅርቡ!
… እና ወገናችሁንና ሀገራችሁን በፍቅርና ይቅርታ ጥሪያችሁ አስተሳስራችሁ ከተሰናበታችሁ በኋላ የቀራችሁን ዕድሜ በየፊናችሁ ከፈጣሪያችሁ ጋር ምከሩበት፡፡ ከፀፀት ከነጻ ንፁህ ህሊናችሁ ጋር ኑሩበት፡፡ ያደባባይ ፌዛችሁንና የእኔ እሻል የእርስ በርስ መካሰሳችሁን አቁሙ፡፡ የእስከዛሬው ሃጢያታችሁና በእጃችሁ ላይ ያለው የወገኖቻችሁ ደም ይብቃ በሉ፡፡ መጪውን ለመረዳት ፈጣሪ ልቦናችሁን ያቅናላችሁ፡፡ ለመልካም እንደ ጣራችሁበት መጠን የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳችሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
Filed in: Amharic