>

ህወሓት የውጭ መንግስታት እና ሃይሎች ከውስጥ ጉዳያችን እጃቸውን ያውጡ አለች!! (ዳንኤል በቀለ)

ህወሓት የውጭ መንግስታት እና ሃይሎች ከውስጥ ጉዳያችን እጃቸውን ያውጡ አለች!!

ዳንኤል በቀለ
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ [ህወሓት] ባለፈው ቅዳሜ እና ዕሁድ ያደረገውን አስቸኳይ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ አቋሜን ያንፀባርቃል ያለውን ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥቷል።
የሃገሪቱ እና የቀጠናው ሰላም ያሳስበኛል ያለው ሕወሓት አንዳንድ የውጭ መንግስታት እና ኃይሎች በሃገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንደሆኑ በመግለጫው ጠቅሷል። ነገር ግን የትኞቹ ኃይሎች እንደሆኑ በይፋ መግለጫው ላይ የተቀመጠ ነገር የለም።
«እነዚህ የውጭ መንግስታት እና ሃይሎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላይ እያሳደሩት ያለው አሉታዊ ጫና የሃገራችንና የአካባቢውን ጥቅም ስለሚጎዳ ከውስጥ ጉዳያችን እጃቸውን ያውጡ» ይላል መግለጫው።
ይህ ካልሆነ ደግሞ፤ የአፍሪካ ሕብረትና መንግስታት ይህንን ጣልቃ ገብነት ተረድተው የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
በቅርቡ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ተዋህደው ብልፅግና ፓርቲ መመሥረቱን የተቃወመውና ብልፅግና ፓርቲን እንደማይቀላቀል ያሳወቀው ህወሓት፤ ኢህአዴግ የፈረሰበት አካሄድ ህጋዊ ያልሆነ እና ፀረ ዲሞክራሲያዊ ነው በማለት፤ ፓርቲውን “ጥገኛ እና ህጋዊ ያልሆነ” ሲል ገልፆታል።
በትግራይ ህዝብ ትግል የተሸነፉ ኃይሎች እንደገና በመሰባሰብ በሃገሪቱ የተገነባው ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም ለማፍረስ እያደረጉት ባሉት መተናነቅ የትግራይ ህዝብና ህወሓትን ጠላት በማድረግ ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል እየሰሩ ነውም ሲል ይወቅሳል።
ህወሓት በይፋ ብልፅግና ፓርቲን እንደማይቀላቀል ባሳወቀበት ጉባኤ “ከእንደኛ ዓይነት ፌደራሊስት ኃይሎች ጋር ግንባር እና ውህደት እስከ መፍጠር የሚደርስ ትግል እና መደጋገፍ እናደርጋለን” በማለት ቀጣይ አቅጣጫውን አስቀምጧል።
ይሁን እንጂ ድርጅቱ ከየትኞቹ ፌደራሊስት ኃይሎች ጋር ጥምረት እንደሚፈጥር ያለው ነገር የለም።
ድርጅቱ በጉባኤው ለኤርትራ ህዝብም መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፤ የኤርትራ ህዝብ እና የትግራይ ህዝብ አንድ ቋንቋ፣ ተመሳሳይ ባህል ያለው እና በጋብቻ የተሳሰረ ወንድማማች ህዝብ ነው። ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ግን በሁለቱ ህዝቦች መካከል ከሰላም እና ልማት ይልቅ፣ መግባት ወደ ማይገባን ጦርነት በመግባት የማያስፈልግ ኪሳራ ከፍለናል ሲል መግለጫው ያትታል።
«ባለፈው ዓመት በሁለቱም ሃገራት መሪዎች የተጀመረው ግንኙነት ተስፋ የነበረው ቢሆንም በሂደት ግን ተስፋ የተጣለበት ግንኙነት ተቋርጣል። የተጀመረው ተስፋ የሚሰጥ ወንድማማችነት እና ዝምድና በመተጋገዝ ላይ የተመሠረተና ለሁላችንም ጠቃሚ እንዲሆን ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ የሚጠብቅባቸው ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው።»
ኢህአደግን የመሰረቱ የአራቱ ድርጅቶችን የጋራ ሀብት ህግና ስርአት በተከተለ መንገድ ድርሻውን እንደሚያስመልስም በአቋም መግለጫው አስታውቋል።
ከፌዴራል መንግስት ጋር የሚኖረው ግንኙነትም ህግና ህገ-መንግስትን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ያመለከተው መግለጫው ከዚህ ውጭ የሚኖር እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደማይኖረው አመልክቷል።
Filed in: Amharic