>
5:41 am - Friday July 1, 2022

" የትራምፕን ጭንቅላት  ቆርጦ ላመጣ 80 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ይሰጠዋል!!!" የኢራን መንግስታዊው ቴሌቭዥን (በታምሩ ገዳ)

” የትራምፕን ጭንቅላት  ቆርጦ ላመጣ 80 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ይሰጠዋል!!!”
የኢራን መንግስታዊው ቴሌቭዥን 
 
* “ትራምፕን ለመግደል 40 ሚ/ዶላር ይከፈለን!!!”
አሜሪካዊ ኮሚዲ… 
በታምሩ ገዳ
 የአሜሪካው ፕ/ት ዶናል ትራምፕን” ለገደለ የሰማኒያ ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ እንከፍላለን “የሚል ማስታወቂያ ሰሞኑን ከወደ ኢራን መውጣቱን ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ  ቀልድ ብጤ ጣል ያደረገ ታዋቂ አሜሪካዊ ኮሚዲያን   እና አክተር ለከፍተኛ  ትችት ተዳረገ።
አሜሪካ ባለፈው አርብ የኢራኑ አብዮታዊ ዘብ  ቁልፍ  ሰው እና  የወታደራዊ ዘመቻ  ቀማሪው  ሌተናል  ጄ/ል  ቃሲም ሱሉማኒን በኢራቁ ባግዳድ አይር ማረፊያ አጠገብ በሰው አልባ አውሮፕላን(ድሮን) መግደሏን ተከትሎ  በኢራን ውስጥ ታውጆ በነበረው የሶስት ቀናት የሀዘን ስነስርአት ላይ   በምስራቃዊቷ ማሻድ ከተማ ውስጥ ነዋሪዎች ለሀዘን በወጡበት ወቅት  በመንግስታዊው ቴሌቭዥን በቀጥታ በተሰራጨ ስነስርአት ላይ ” የትራምፕ ጭንቅላትን  ቆርጦ ላመጣ ሰማኒያ ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ይሰጠዋል”የሚል መፈክር እና ጨረታ የወጣ ሲሆን  ዜናውም  አለማቀፋዊ መነጋገሪያ ርእስ ሆኖ  ነበር።
ይሁንና መቼም  የእውነተኛ የኪነጥበብ  ሰው ሁሌም የሚጠብቀው  ጭብጨባ ብቻ ሳይሆን፣ የህይወት ዋጋም እንደሚያስከፍል ሁሉ በትውልድ ሜክሲኮአዊ በዜግነቱ አሜሪካዊ የሆነው  የሀምሳ ስምንት አመቱ ጆርጅ ሎፔዝ በሰጠው አስተያየት “አረ ሰማኒያ ሚሊዮኑ ቀርቶ እኛ  በግማሽ/በአርባ ሚሊዮን ዶላር እናደርገዋለን” ሲል  በጣም አስቂኝ፣ነገር ግን መራር ቀልዱን ጣል ያደርጋል።
የኮሚዲው ሎፔዝ ቀልድም በወግ አጥባቂዎች  እና በትራምፕ ደጋፊዎች ዘንድ  ከፍተኛ ቁጣ  ከመቀስቀሱ በተጨማሪ ኮሚዲው የተጠቀመበት ቃል ተገቢ ባለመሆኑ”ሊታሰር እና  በኤፍ ቢ አይ/FBI/ ምርመራም ሊደረግበት ይገባል”ሲሉ ጫጫታ አሰምተዋል።
 ብዙ ጊዜ የፕ/ት  የትራምፕ  አስተዳደር ቀንደኛ ተቺ የሆነው እና በሚሊዬን የሚቆጠሩ አድናቂዎች ያለው ሎፔዝ ተወካይ በአጭር ቋንቋ” ቀልድ አታውቁም እንዴ? ይሔ እኮ ለሳቅ እና  ለፈገግታ ነው”ሲሉ ወቀሳውን ለማስተባበል ሞክረዋል።
የታዋቂ ሰዎችን ውሎ የሚያነፈንፈው  ቲኤም ዚ(TMZ) ድህረ ገጽ ዘገባ የአሜሪካ የምርመራ ሰራተኞች  ታዋቂው ኮሚዲያን ሎፔዝ  ስለ ፕ/ት ትራምፕ የቀለደውን ቀልድ ከ”ግድያ ማስፈራራት” ጋር ስለ መያያዙ እና ያለመያያዙ እያጤኑት ናቸው ብሏል።
በአሜሪካ የዲሞክራት እና የሪፓብሊካን ፓርቲ  ደጋፊዎች በበኩላቸው” ኮሜዲያኑ  ሎፔዝ ቀልደኛ ቢሆንም በሰሞነኛው ቀልዱ ፕ/ት ትራምፕ ይገደሉ ብሎ ለማሳቅ መሞከሩ ግን ቀይ መስመር አልፏል፣ለአፍ ወለምታውም ሊጠይቅ እና ተገቢውን ዋጋ ሊሰጠው  ይገባል” ባይ ናቸው።
በዘር፣በማህበረሰብ ጉዳዮች በሚያቀርባቸው በርካታ ደጋፊዎችን ያተረፈው ስታንድ አይ  ኮሚዲያኑ ጆርጅ ሎፔዝ በስፓኒሽ ተናጋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ ከማግኘቱ  በተጨምሪ በርካታ  ሽልማቶችን አግኝቷል።ሎፔዝን በተመለከተ  ታዋቂው ታይምስ መጽሔት በላቲን ቋንቋ ተናጋሪ  ማህበር ውስጥ ሀያ አምስተኛው ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው  ሲል ቀደም ሲል አወድሶታል። አሜሪካ እና ኢራን ከመቼውም ጊዜ በከፋ አይን እና ናጫ በሆኑበት በሰሞኑ የውጥረት ድባብ ውስጥ የተዋቂው  አሜሪካዊ ኮሚዲያን ጆርጅ ሎፔዝ”የአርባ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ይከፈለን…” ቀልድን ምን እንበለው? ።
Filed in: Amharic