>

እኛ ያቀለልነው ሌሎች ያከበሩት ኢትዮጵያዊ የመሆን እድል!!! (ዘውደለም ታደሠ)

እኛ ያቀለልነው ሌሎች ያከበሩት ኢትዮጵያዊ የመሆን እድል!!!

 

ዘውደለም ታደሠ
ወዳጄ ኢትዮጵያዊ መሆንማ ሎተሪ ነው። ምንም አይነት ፖለቲካል ኮንሰርን ይኑርህ፣ ምንም አይነት አመለካከት ይኑርህ በፍፁም ግን ኢትዮጵያዊ የመሆንን እድል ለራስህ እንዳትነፍገው!! 
ዛሬ በጠኋት ነቃሁና ዩቲዩብ ከፍቼ Genetics DNA test ያደረጉ ጥቁር አሜሪካውያንን ስመለከት ነበር። ጄኔቲክስ ዲኤንኤ ቴስት ማለት ካንተ የሆነ ዘረመል ተወስዶ ከአምስት ወይም ከአስር ሺ አመት በፊት የነበረው ኦርጂናል ዘርህ የሚታወቅበት ዘበናይ ሳይንስ ነው። (በነገራችን ላይ ይሄ ሳይንስ ሐገርህን ወይም አህጉርህን እንጂ ብሔር አይናገርም  ) ጥቁር ሆነህ 80% ጣሊያናዊ ነህ ሊልህ ይችላል። የቆዳህ ቀለም ወይም የምትናገረው ቋንቋ ወይም አሁን የያዝከው ፓስፖርት የዘር ማንዘርህን ማንነት አይናገርም። መቶ ፐርሰንት ጉራጌ ነኝ አማራ ነኝ ኦሮሞ ነኝ ትግሬ ነኝ ብለህ ስትሄድ አንተ ጥርት ያልክ ጃፓንና ናይጄሪያዊ ነህ ልትባል ትችላለህ።
እና ምን ገረመኝ? … ብዙዎቹ ይሄን ምርመራ ያደረጉት ጥቁር አሜሪካውያን የተወሰነ ኢትዮጵያዊ ዘር አለባችሁ ሲባሉ በጣም ይደሰታሉ። ዋው ዊው ምናምን ብለው ይቀውጡታል። ለምን …? ኢትዮጵያዊነት ልዩ እንደሆነ ከኛ በላይ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ።
ወዳጄ ፅድት ያልን ደሃ መሆናችን አይጠፋኝም። ግን ድህነት እውነታውን አይቀይረውም። ኢትዮጵያ የነፃነት መስኮት ነች። ሚኒሊክን ላትወዳቸው ትችላለህ በአድዋ ታሪክ ካልኮራህ ግን አንተ ባያትህ ጣሊያናዊ ነህ ማለት ነው። አባቶችህ አድዋ ላይ ቆሎ ቆርጥመው ጣሊያንን ሲያስተነፍሱኮ ሌሎች በቀንበር ስር ያሉ ጥቁር ህዝቦች «ለካ ነጭ የሚባለው ፍጡርም ይሸነፋል» ብለው ለነፃነታቸው ተነሱ። ይህ አብዮት ተቀጣጥሎ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ጥቁሮችን ሁሉ አነቃቸው። እነማርቲን ሉተር ኪንግ በተደጋጋሚ የአድዋን ቪክትሪ እያነሱ የአሜሪካ ጥቁሮችን ይቀሰቅሱ እንደነበር ተፅፏል። እነ ማርክስ ጋርቬይ አምላካችን ኢትዮጵያዊ ነው። ነፃም ያወጣናል ብለው ግግም ያሉትኮ አንድፊትድና ለነፃነት የተፈጠርን ገናና ታሪክና ስረ መሰረት ያለን ህዝቦች መሆናችንን አይተው ነው። ለመጀመሪያ ግዜኮ ለጥቁሩ ማንዴላ የዜግነት ፓስፖርት የሰጠን እነአንጎላን ጋናን ዙምባቤን ሁሉ በትጥቅ የረዳን ህዝቦች እኮ ነን። እስቲ ግባና ሃይለስላሴ በሁለተኛው የአሜሪካ ጉብኝታቸው ነጮቹ ፊት ቆመው ስለሰው ልጅ ነፃነትና ስለጥቁሮች እኩልነት በታላቅ ግርማ ሞገስ የተናገሩትን ተመልከት። “አስፈላጊ ከሆነ ነፃ ያልወጡ የአፍሪካ ሀገራትን በመሳሪያም ጭምር እንረዳለን“ ያልን ህዝቦች እኮ ነን በደህናው ግዜ!!
ባሻዬ ኢትዮጵያ ደሃ ናት? ይርበናል? ምናምን አይደል? ግን እሱ እውነታውን አይቀይረውም። እልፍ የምንኮራበት ታሪክ አለን። ሲጀምር እኛ ባንኖር ጥቁር አፍሪካውያን ፈጣሪስ ይወቃቸው አይወቃቸው በምን ያውቃሉ?
እስቲ መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ከኢትዮጵያዊ ውጪ የተፃፈ አንድ ጥቁር ህዝብ ንገሩኝ? እግዚአብሔር ጥቁሮችን እንደሚያውቃቸው እኛ ባንኖር በምን ያውቁ ነበር?  እስቲ ቁርአን ውስጥ መስኪድ ገብቶ አዛን ያለ አንድ አፍሪካዊ ጥቁር ከኢትዮጵያዊው ቢላል ውጪ አሳየኝ? አላህና እግዜርም አድልተውልናል እኮ ነው ምልህ!!!
ጥቁር አፍሪካውያን ስርአቱን የጠበቀ የሺህ አመታት የንግስና ስርአት እንደነበራቸው አለም ያወቀው በኢትዮጵያውያን አይደል እንዴ? ጥቁሮች ለመገዛትና እንደበሬ ለመነዳት ብቻ እንዳልተፈጠሩ አለም የተገነዘበው ኢትዮጵያዊ የጣሊያንን ወታደር እንደበግ እየነዳ ሲመለከት አይደል እንዴ? ጥቁር አፍሪካዊ ሁሉ ኮባ አገልድሞ ቂጡን እያወዛወዘ ሲጨፍር ኢትዮጵያውያን የህንፃ ምህንድስና ጥበብ ዛሬም ያልደረሰበትን ላሊበላ የተባለ ውቅር ቤተመቅደስ ከላይ ወደታች ገንብተው፣ 33 ሜትር ድንጋይ ጠርበው (በምን እንዳጓጓዙት እግዜር ይወቅ) አክሱም ላይ አቁመው። እነፕሮፌሰር አስመሮም አይናቸው እስኪታመም ያጠኑትን ለእንሰሳት እንኳ መብት የሚሰጠውን የገዳ ስርአት ከሶስት ሺ አመት በፊት ዘርግተው፣ ያሳዩ ኢትዮጵያውያን ባይኖሩ አፍሪካውያን ጥቁርም ማሰብና መራቀቅ ይችላል ለማለት ምን ማስረጃ ያቀርቡ ነበር?
ወዳጄ ኢትዮጵያዊ መሆንማ ሎተሪ ነው። ምንም አይነት ፖለቲካል ኮንሰርን ይኑርህ፣ ምንም አይነት አመለካከት ይኑርህ በፍፁም ግን ኢትዮጵያዊ የመሆንን እድል ለራስህ እንዳትነፍገው!!
መልካም ቀን!
Filed in: Amharic