>
1:33 am - Saturday December 10, 2022

የደራሲ አዳም ረታ አዲሱ መፅሀፍ "አፍ" በእኔ እይታ!!! (ሌሊሳ ግርማ)

የደራሲ አዳም ረታ አዲሱ መፅሀፍ “አፍ” በእኔ እይታ!!!

ሌሊሳ ግርማ
~
‹‹ … የመፅሐፉን አርዕስት ‹አፍ› ባይለው ጥሩ ነበር …?›› ሰሞኑን  ያለኝ ማን ነበር? ማን እንደነበር ማስታወስ አስፈላጊ ስላይደለ አላስታውሰውም፡፡ አስተያየቱን የሰጠው በ ‹አፍ› እንደነበር ግን ትዝ ይለኛል፡፡
     አርእስቱ ምን ቢባል ይሻል ነበር? ብዬ ገፋ አድርጌ አልጠየቅሁትም እንጂ… ብጠይቀው ያቀርብልኝ የነበሩት አማራጮች እርግጠኛ ነኝ ከሚከተሉት አያልፍም፡፡ …አንድም፦ አይን፣
 ሁለትም፡- ነብስ ..፣ ካልሆነም፡- አእምሮ … አልያም፡- እጅ … ከእነዚህ አይወጣም፡፡
    ‹‹አእምሮ›› ወይንም ‹‹እጅ›› ከ አፍ የበለጠ የሚከበሩት ያለ አግባብ እንደሆነ እንዳስብ ያደረገኝ ይሄ ድርሰት ነው፡፡ በተለይ የእኛን ማህበረሰብ በተመለከተ ‹‹አፍ›› ከአይንም ሆነ እጅ በበለጠ የሰለጠንንበት ነው፡፡ እንዲያውም ደራሲው ‹‹እኛን›› ጥሩ አድርጎ የሚገልፅ ብልት (Organ) ያገኘ መስሎኛል፡፡ ንግግር ወይንም ቋንቋ የተባለው የሰውነት ልዩ ስጦታ ከአእምሮ ባልተናነሰ የአፍ መሰረት ያለው ነው፡፡ አፍ በዝግመተ ለውጥ አጋጣሚ ንግግርን ማድረግ እንዲችል ሆኖ ባይመች ኖሮ ..ባህልም ሆነ ቋንቋ በቀላሉ ባልተስፋፋ … ሀሳብንም እያሸጋገረ ባላሰፋ ነበር፡፡ በአፍ ያልተነገረ ቃል በአእምሮ የሚደመር የሀሳብ ወይንም የእምነት መዋቅር አይመሰረትም፡፡ …በባቢሎን ሲገነባ የነበረው ግንብ አእምሮ ወይንም እጅ ሳይሆን አፍ ለማግባባት በመለገሙ ነው ኢንዱስትሪው የፈረሰው፡፡
            ‹‹ኦ ሆ ሆ  ስራ  ነው – ስራ ነው – ስራ ነው
            ‹‹ሰውን ሰው ያደረገው – ስራ ነው››
   … የምትል በአፍ የምትዜም … ግን ባለ እጅን ከባለ አፍ በላይ ለማንገስ የምትሞክር በግራ ርእዮተ አለም የሰከረች ዜማ ስትዜም ድሮ ትዝ ይለኛል፡፡ …ዜማዋም ዜማ ሆና ቀረች፡፡ በአፍ መሰረት በተገነባ ሀገር ላይ የእጅ( ተግባር ) ቋንቋን በቀላሉ ማስፈን አይቻልም፡፡ አፎቻችን፤  ተረቶቻችን፣ ስብከቶቻችን፣ ቅኔዎቻችን …ከተግባር የበለጡ ማንነቶቻችን ናቸው፡፡ አፍ የሚያስፈልገንን ያህል አይናችን የህልውናችን ምንጭ አይደለም- በዚህች ሀገር፡፡ ምፅዋት ጠይቆ የሰውን ልብ አራርቶ ለመኖር ራሱ ከተዘጋ አንደበት የተሰወረ ዐይን የተሻለ በህይወት የመቆያ ዋስትና ይሰጣል፡፡
    በዚህ የአዳም ረታ አዲስ መፅሀፍ ውስጥ የሚገኝ ‹‹ኮላሴ›› የተሰኘ ገፀ-ባህርይ አለ፡፡ የጌርሳሞት ወላጅ አባት ነው፡፡ በጨቅላነቱ ዝንጀሮ አሳድጎታል፡፡ ወደ ሰዎች አለም መጥቶ መኖር የቻለው ግን የሰውን ቋንቋ አንደበቱን ገርቶ ከተማረ በኋላ ነው፡፡ ዝንጀሮ ያሳደገው ሰው መሆንና ዝንጀሮ መሆን የሚለያዩት አንደኛው የሰው ቋንቋ ከተማረ ይለምዳል …ዝንጀሮ ግን የፈለገ ቢጥርም አፉ  ንግግር ለማድረግ በተፈጥሮ አልታደለም፡፡
ጨዋታው
 የድርሰቱ ቅርፅ የጠጠር ቅብብሎሽ በመሰለ አኳሁዋን የተቀረፀ ነው፡፡ አምስት ጠጠሮች አሉ፡፡ አንዷ ጠጠር አጫዋቿ ናት፡፡ ወይንም መቅለቢያዋ፡፡ ጌርሳሞት ትባላለች፡፡ አራቱ ተቀላቢዎች ወንዶች ናቸው፡፡ ራሚሱ፣ ገለታ፣ ዘሪሁን እና በካፋ፡፡ ጨዋታ ሁሉ የደርሶ መልስ ሂደት አለው፡፡ ገፀ ባህሪዎቹ መጀመሪያ ይመደባሉ፡፡ በአጭር ገለፃ ባህሪያቸው ይነገረናል፡፡
  ግን በጨዋታው ሂደት (በደርሶ መልሶ) እርስ በራስ እና በሚኖሩበት አለም በሚያጋጥማቸው ተሞክሮ የይዘት ባይሆንም የስነልቦና ለውጥ ያደርጋሉ፡፡ ጥበብነቱም ይሄ ነው፡፡ ተራ የሚመስሉት ጠጠሮች ከጨዋታው ሂደት እኛን አንባቢዎቹን መስለው ይገኛሉ፡፡ ምትሃቱም ይሄ ነው፡፡
‹‹የግሪኩ የአፈ ታሪክ ፍርደኛ፣ ቆሮንጦሳዊው ንጉስ ሲሲፈስ ያንን ትልቅ አለት ወደ ኮረብታው ጫፍ አንከባሎ ሲያወጣ አንከባሎ ያወጣው መልሶ ሲወድቅበት …መልሶ አለቱን ሲገፋ…›› እያሉ ሲነግሩን የነበረውን ተረት ጆሮ ወይ ቀልባችንን ሰጥተን እናደምጥ የነበረው በድንጋዩ እና ሲሲፈስ መሃል ያለው የደርሶ መልስ ጨዋታ እኛንም ስለሚመለከተን ነው፡፡ ድንጋዩ ጌርሳሞት እጅ ሲደርስ ቅልልቦሽ ጨዋታን ተመስሎ በአዳም ረታ አማካኝነት አገኘነው፡፡ …ምናልባት ጌርሳሞት ሴት በመሆኗ ምክንያት ሊሆን ይችላል ደራሲው ለገፀ ባህሪዋ እንዲምቻት የሲሲፈስን ድንጋይ ለቅልልቦሽ የደርሶ መልስ ጨዋታ ቅርፅ ያመቻቸላት፡፡ …ቀላቢዋ ጌርሳሞት በመሆን ፋንታ ወንዶቹ ቢሆኑ ጠጠሮቹ ወደ ብይ፣ የጨዋታው ግብ ደግሞ መቅለብ ሳይሆን አሽኳሎ ጉድጓድ ማስገባት ሊሆን ይችል ነበር… ስል አስባለሁኝ፡፡ …ወይንም አንድ ሴት አራት ወንዶችን(ጠጠሮችን) በመቅለብ ፋንታ አራት ወንዶች ጌርሳሞትን እንደ ኳስ አታለው ወደ ግብ መረብ ማስገባት ሊሆን ይችል ነበር የጨዋታው ትልም፡፡ …ይሄ የኔ ተቀጥላ ሀሳብ ነው፡፡ በመፅሀፉ ውስጥ ሌላ ጨዋታ ለመፍጠር በምናቤ አማካኝነት የማደርገው ሙከራ ብላችሁ እይታዬን እለፉት፡፡
ጌርሳሞት ብቻ ሳትሆን ሁሉም ከራሳቸው ጋር የሚያሳልፉት ምዕራፍ አላቸው፡፡ እርስ በራሳቸው እና ራሳቸው በራሳቸው …ወይንም ራሳቸው በሌላቸው አንፃር በሚያደርጉት መስተጋብር እና ገለፃ ፕሎቱ ሳይሆን ድርሰቱ ከህይወት የበለጠ  ጣእም እና ‹‹ቴክስቸር›› እያበጀ ይመጣል፡፡ …ከጨዋታው ትልም፣ ገፀ ባህሪዋቹ በተናጠል ካላቸው ግብ ፣ ከሰፈሩ እና የድርሰቱ ዳራ ከሚፈጥሩት አቅም በበለጠ ጥቅሉ ሬሰፒ የህይወትን ሁለንተናዊ ትርታ የሚዘምር ይመስለናል፡፡ መስሎኛል፡፡ ‘’The whole is more than the sum of its parts’’  እንዲሉ ከበፊቱም የነቁት አሳቢዎች፡፡
…ጨዋታም ከጨዋታ በላይ፥ በቃላት የሚቀናበር አስማትም ከተራ ቃላት በላይ፣ ድርሰትም ከህይወት እና ለተራ ጉዳያችን ደርሰን ከምንመለስበት (ከምንመላለስበት) መንገድ በላይ የሚሆነው እንዲህ – እንዲህ እያለ ነው፡፡
‹‹ይወስዳል መንገድ … ያመጣል መንገድ›› …ወስዶ የሚመለሰው ግን የሄደውን አንባቢ አይደለም፡፡ ራሱን ተሸክሞ ነው የሚመለሰው፡፡ ደራሲ ፤ የአንባቢውን መጠን የለሽ የህይወት ተሞክሮ ቀላል በሚመስል የቃላት ጨዋታ ማሸከም ነው ስራው፡፡ ደራሲው አዳም ረታ ነው፡፡ ደራሲው እሱን እንድንሸከመው አይሻም፡፡ ራሳችንን ደጋግሞ በማሸከም ግን ወደር አልተገኘለትም፡፡
  ~
መፅሐፉ ላይ የትኛውንም ገፅ ድንገት ከፍታችሁ ብታነቡ እንደ ዋና ጉዳይ ወይ እንደ ማያያዣ ሆኖ የምታገኙት አፍን ነው፡፡ አፍ በብዙ ግብር አንፃር እና ንዑስ ክፍል የተጠቃለለ አብስትራክት ቃል ነው፡፡ ከንፈር፣ መንጋጋ፣ ምላስ፣ ጥርስ …ወዘተ፡፡
  ‹‹ገለታ ደህና አደርክ? ወደ የት ነህ?›› አለችው፡፡ ብቻውን ሲሆን ትደፍረዋለች፡፡
…ጉንጭ ለጉንጭ ተሳሳሙ፡፡ በልታ እንደወጣችው የእንቁላል ፍርኖ ትሸታለች፡፡››
     ( ወደ ገፅ 56 ስገልጥ እንዳጋጣሚ ያገኘሁት)
በተፈጥሮአችን ሁለት ነገሮች ላይ በአንድ ቅፅበት
 (ማለትም የታሪኩ ሂደት እና ታሪኩን ማካሄጃ ንጥረ ነገሮች ላይ) ማተኮር አንችልም እንጂ ሆነ ብለን እናስተውል ካልን መፅሀፉ በአጠቃላይ ስለ ሰው ልጆች አፍ ነው፡፡
‹‹ገለታ ወዴት ነህ?›› አለችው (ያለችው በአፏ ነው)
‹‹ጉነጭ ለጉንጭ ተሳሳሙ›› (ዝምድናን ለመግለፅ የሚፈልጉ አፎች የሚሳሳሙበት ስፍራ ነው ጉንጭ)
‹‹በልታ እንደወጣችው የእንቁላል ፉርኖ ትሸታለች›› (አፍ በበላው እንቁላል የሽታ የስሜት ህዋስ ትርጓሜ ሲያገኝ)… ወዘተ
ቀጥሎ በታሪኩ ሂደት በጥቅሉ መሰረታዊ ገፀ ባህሪዎቹ የተቀረፁትም አፍን መሰረት ባደረጉ ምልክቶች ሆነው እናገኛለን፡፡
ጌርሳሞት በአጠቃላይ አፍ ወይንም ከንፈር ናት፡፡ የእሷ ግልፅ ነው፡፡ …አራቱ ገፀ ባህሪያትን ስንመለከት
…ለምሳሌ፡-   ገለታ ዝምተኛ ነው (ዝምተኛነት እና ለፍላፊነት የአፍ አጠቃቀም ከንግግር አንፃር ሲመዘን ነው፡፡)
        …ገለታ ዝምተኛ እና ጉንጩ ላይ ዲምፕል ያለው ወጣት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሀርሞኒካ ይጫወታል፡፡
        በካፋ- ‹‹ከቃሚ ጓደኞቹ ጋር በርጫ ሲቀመጥ ጎኑ የሚጎልተው ኮዳና የስጋ ሳንቡሳ ነው›› (በአጭሩ
        የአፉ መገለጫ ሆዱ ነው እንደማለት ነው)
        አቡ(ራሚሱ) ፡- ተሳዳቢ እና ቃሚ ነው (ያው የአፍ ስራ ናቸው)
        ዘሪሁን፡- ወሬኛ እና ውብ ፉጨት ማፏጨት የሚችል ነው (ውበት እና ርካሽነት በ አንድ አፍ ላይ ሲዳበሉ)
በዚህ አተያይ ከዋናዎቹ ገፀ ባህሪዎች ባሻገር ያሉትንም ብናስተውል ደራሲው መስራት ለፈለገው ህፅን አፍ ዋናው ማያያዣ ማድረጉን በቀላሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡ በቅልልቦሽ ቅርፅ የተወጠነው ጨዋታም በእጅ ሳይሆን በአፍ እንደሆነ  ወርውሮ ለመቅለብ የሚሞክረው እንገምታለን፡፡ ነገር ግን ቀላቢዋ ጌርሳሞት ከአራቱ የጠጠር ከረሜላዎች አንዱንም መቅለብ ሳይሳካለት የድርሰቱ የጨዋታ ሂደት ይጠናቀቃል፡፡ ገለታ ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ከነ ሃርሞኒካው ይሞታል፡፡ ጌርሳሞት ጥርሷ ላይ መወጠሪያ ሽቦ ታሳስራለች…ወ.ዘ.ተ
    ‹‹ የአንድን ሴት ከንፈር እናይና ቆንጆ ወይንም አስቀያሚ ወይንም ሌላ የመሰለንን ስያሜ እንሰጣለን …ለመሆኑ
      አንድ ከንፈር ውብ የሚባለው መቼ ነው? ለምን ውብ ተባለ? አንድ ነገር ውብ ከተባለ በኋላ ውብ አለመባል
      የሚጀምረው መቼ ነው? ከንፈሮች የማይለወጥ ዘላለማዊ የሆነ የውበት ባህርይ (ኤሰንስ) አላቸው?››  ብሎ
    ደራሲው በአንዱ የግርጌ ማስታወሻው ይጠይቅና በሥነ ውበት የ‹‹Golden Proportion›› ተብሎ የሚጠራውን ቀመር ተጠቅሞ ለጌርሳሞት ከፊቷ ርዝመት አንፃር ይህ የውበት ልክ ከንፈሯ ላይ እንደሚያርፍ በመጠይቅ  እና ጥቆማ መልክ ያቀርባል፡፡
ከአምስቱ የፍልስፍና ፈርጆች አንዱን (ስነ ውበትን) ከከንፈር ጋር እንዳገናኘው …ተግተን ብንፈልግ የተቀሩት አራቱ ዘርፎችም (ማለትም ሜታፊዚክስ፣ ፖለቲክስ፣ ሀይማኖት፣ ሞራል) …እንደዚሁም ተብራርተውም ባይሆን ተጠቁመው መገኘታቸው አይቀርም፡፡
   ‹‹ሁሉ ያልተወራላቸው ሀሚና ናቸው፡፡ እነዛ ልባም ነን የሚሉ አፈኞች፡ እንደ አበው የሚሰራቸው የስነቃል ጭቃ ሹሞች፣ ነጋዴ ሀይማኖተኞች፣ የመድፍ ምስል ምላሳቸው ቀይ ጀርባ ላይ የተነቀሱ ፖለቲከኞች፡፡›› እንዲል የወ/ሮ መቅረዝ ልጅ ራሚሱ (ገፅ 156)
… ጊዜ አይበቃ እንደሆን እንጂ… የፍልስፍና ዘርፎቹ የሚጠይቁትን ጥያቄ በአፍ አማካኝነት የሚመልሱ ብዙ አንቀፆችን ዋቢ ማድረግ ይቻላል
 ~
የጥበብ መሰረታዊ ግብ አንድን ነጥብ መርጦ ማጉላት ነው፡፡  ከዛም…ያንን ነጥብ ለጥቅሉ እውነታ ማስተሳሰሪያነት  ወኪል አድርጎ አቅልሎ ማቅረብ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደራሲው ‹‹አፍ”ን እንደ ዋና ትዕምርት (Motif) ማጉላቱ ተዋጥቶለታል እላለሁ፡፡
ከዚህ በፊት ደራሲው መርጦ ያተኮረባቸው እንጀራው፣ ወጡ፣ ፍርፍሩ እና መረቁ ያለመመገቢያ አፍ… ግዑዝ መስለው ተነጥለው ነበር  እንዴ ?እንድል አድርጎኛል፡፡
ጉርሻ ያለ መጉረሻው የተጠናቀቀ የደርሶ መልስ ጉዞ አይሰጥም፡፡
ትእምርቶችም ተዋረድ አላቸው፡፡ በእንጀራ …በወጥ እና በመረቅ አማካኝነት የድርሰት ካርታውን የነደፈ ደራሲ የሰው አካል ላይ ሲደርስ ‹‹አእምሮ›› ወይ ‹‹ነፍስ›› ቢለኝ ኖሮ ምክንያታዊነቱ በተፋለሰብኝ ነበር፡፡
ደራሲው አሁንም እንደ ቀድሞው በአቦ ሰጡኝ እንደማይሰራ ‹‹አፍ›› የሚለው ድርሰት ድጋሚ ማሳያ ነው፡፡ ጥሩ ጥበብ ሆን ተብሎ የሚከወን (Deliberate) ነው ….ይላሉ፡፡ “አቦ ጥበብን አይሰጡም” ማለታቸው ነው፡፡
በአዳም  ውስጥ እኔ የሚታየኝ… ንድፍን የተከተሉ ሰንሰለታማ የድርሰት ስራዎቹ ብቻ አይደሉም ..ከድርሰቶቹ ጀርባ በፈጠራ ሂደቱ ላይ  በእቅድ እና ጥንቃቄ የድርሰት ‹‹ሬሰፒውን›› ለመቀመም የሚጨነቅ ባለ መርህ ደራሲም ጭምር ነው፡፡
Filed in: Amharic