>

እነ አሕመዲን ጀበል ለመንጋቸው ከማይነግሯቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታሪካዊ እውነቶች መካከል!!! [ክፍል ፫ አቻምየለህ ታምሩ]

እነ አሕመዲን ጀበል ለመንጋቸው ከማይነግሯቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታሪካዊ እውነቶች መካከል!!!

ክፍል ፫
አቻምየለህ ታምሩ
ባለፉት ክፍሎች ባቀረብናቸው ታሪኮች  እነ አሕመዲን ጀበል ለመንጋቸው ከማይነግሯቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እውነታዎች መካከል  በመንበረ ዳዊት የተቀመጡ፣ በሃይማኖታቸው ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ የሆኑት ንጉሠ ነገሥት መስጂድ በገንዘባቸው ያሰሩ፣ ሙስሊም ዜጎቻቸው በቋንቋቸው ሃይማኖታቸውን  እንዲማሩ ቁርኣንን በገንዘባቸው  ከአረብኛ ወደ አማርኛ እንዲተረጎምና የኢትዮጵያ  ሙስሊሞች  እንደሃይማኖታቸው ሥርዓት እንዲኖሩ በማሰብ  የሸርያ ፍርድ ቤት በአዋጅ  እንዲቋቋም ማድረጋቸው ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰናል።
ዛሬ ደግሞ  በምናቀርበው ታሪክ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለሙውሊም ዜጎቻቸው ያደረጓቸውን ተጨማሪ የታሪክ እውነቶች እናነሳለን። ዛሬ የምናወሳው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለሙስሊም ዜጎቻቸው የፈጸሙት ታሪካዊ ተግባር  የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች  አረብኛ ቋንቋ  የሚማሩበትን መጽሐፍ በገንዘባቸው በነ ዶክተር ሙራድና በሌሎች አማካኝነት እንዲዘጋጅ አድርገው በየጠቅላይ ግዛቱ፣  በየአውራጃው፣ በየ ወረዳውና ምክትል ወረዳው  እንዲሰራጭ  ያደረጉበት ታሪካዊ ስራ ነው። ይህ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አረብኛ ቋንቋን ተምረው የሃይማኖታቸውን ስርዓት ይማሩ ዘንድ እንዲዘጋጅ ያደረጉት መጽሐፍ ርዕስ በአረብኛ «ቀዋዒዱ ሉገተል ዓረብያ» የሚሰኝ ሲሆን  መጽሐፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1936 ዓ.ም.  በመንግሥታዊው ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ነው። የዚህን ታሪካዊ መጽሐፍ ሽፋን ከታች አያይዤዋለሁ።
ዛሬ  የምናቀርበው ሌለኛው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለሙስሊም ዜጎቻቸው የፈጸሙት የታሪካዊ እውነት ለሙስሊም አርበኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ «ሰንደቅ ዓላማችን» የሚለው የወቅቱ ጋዜጣ በአረብኛ ቋንቋ  እንዲታተም በ1934 ዓ.ም. ያወጁት አዋጅ ነው። ይህ ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ተብሎ በአረብኛም እንዲታተም የተደረገው ጋዜጣ እስከ ንጉሡ ዘመን መጨረሻ ድረስ በመንግሥት ወጪ በአረብኛ  ቋንቋ እየታተመ ይሰራጭ ነበር።
እነ አሕመዲን ጀበል ግን ይህንን ሁሉ  እውነት በመድፋት በሃይማኖት ስም የኦነግን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ  እየደረቱ ለማጣራትና በራሱ አስቦ ምርምሩ ወደሚወስደው ድምዳሜ  ላይ ለመድረስ ፈቃደኛ ያልሆነውን  መንጋቸውን  አባቶቹ ከውጭ ጠላት ጋር ተፋልመው በጋራ  እንደገና ባቆሙት አገርና ተቋማት ላይ እንዲያምጽ  በቅጥፈትና በልብ ወለድ ሲቀሰቅሱት ይውላሉ!
ከታች ቀደም ብዬ ላቀረብኋቸው ታሪኮች  ማስረጃ  የሆኑትን ሶስት ነገሮች አትሜያለሁ። የመጀመሪያው  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አረብኛ ቋንቋ  እንዲማሩ በ1936 ዓ.ም. ያሳተሙት «ቀዋዒዱ ሉገተል ዓረብያ»  የሚለው  የአረብኛ የመማሪያ መጽሐፍ ሽፋን ነው። ሁለተኛው ሰነድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1934 ዓ.ም. ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ተብሎ በአረብኛም እንዲታተም የተደረገው «የሰንደቅ ዓላማችን ጋዜጣ» እንዲታተም ንጉሡ ያወጁበትን ቃል  የያዘ ነው። ሶስተኛው ሰነድ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት በአረብኛ ቋንቋ የተዘጋጀው «የሰንደቅ ዓላማችን ጋዜጣ» ሕትመት ምን ይመስል እንደነበር የሚያሳይ ናሙና ነው።
Filed in: Amharic