እውቁ የዜማ ሊቅ የቅዱስ ያሬድ አደባባይ ሊመረቅ ነው !!
አደባባይ ሚዲያ
በኢትዮጵያዊዉ ሊቅ በቅዱስ ያሬድ ስም የተሰየመው አደባባይ ከነገ ወዲያ በአዲስ አበባ ይመረቃል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልባቸውን ጸዋትወ ዜማዎ የደረሰው ታላቁ ሊቅን የሚያዘክረውና በስሙ የተሰየመው የቅዱስ ያሬድ አደባባይ በአዲስ መልክ ተገንብቶ ለምረቃ እንደተዘጋጅ ማወቅ ተችሏል።
ዜማን ከመላእክት ተቀብሎ ለመላው ዓለም ያበረከተው እውቁ የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የደረሳቸው መጻሕፍት ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ዝማሬ እና መዋስዕት የተባሉት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ዛሬም ዋነኛ የቤተ ክርስቲያን የዕለት ተዕለት መገልገያዎች እንደሆኑ ይታወቃል።
በዚህ አስተዋጽዖውም ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ማእረግ የተሰጠው ሲሆን በመላው ኢትዮጵያ እና በውጭ አገር ጭምር በስሙ ጽላት ተቀርፆለትና ቤተ ክርስቲያን ተተክሎለት እየታሰበ ይገኛል።
አሁን ለምረቃ የተዘጋጀው የቅዱስ ያሬድ አደባባይ በአዲስ አበባ ጎተራ ማሳለጫ አካባቢ ይገኛል። ከነገ ወዲያ ለሚደረገው ምርቃትም ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገኙ ተገጿል።
ከሳምንት በፊት ለአደባባዩ ስራ ማስፈጸሚያ ገቢ ለማስገኘት ታስቦ ሊካሄድ የነበረ የእግር ጉዞ በመንግስት አካላት መከልከሉ የሚታወስ ነው።