>

የኮሜዲያን አለባቸው ተካ 15ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ  (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል)

የኮሜዲያን አለባቸው ተካ 15ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ 

 

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል
በኮሜዲ (Comedy) ስራዎቹና በበጎ ፈቃድ ተግባራቱ ታዋቂ የነበረው ኮሜዲያን አለባቸው ተካ (አለቤ) ያረፈው ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት (ጥር 7 ቀን 1997 ዓ.ም) ነበር፡፡
በ1954 ዓ.ም የተወለደው አለባቸው፣ በኢትዮጵያ የኮሜዲ ስራ እንዲዘምንና እንዲተዋወቅ አድርጓል፡፡ ከባልደረባው ልመንህ ታደሰ ጋር በመሆን ‹‹ስታንዳፕ ኮሜዲ (Standup Comedy)›› እንዲጀመር አድርገዋል፡፡ ከአገር ወስጥ በተጨማሪም ወደ ሌሎች አገራት በመሄድ ስራዎቹን አቅርቧል፡፡
 – – –
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውንና ‹‹አለቤ ሾው›› የተባለውን የቴሌቪዥን ቶክ ሾው (TV Talk Show) ያዘጋጀውና ያቀርብ የነበረው አለባቸው ተካ ነው፡፡ ይህ የቴሌቪዥን ዝግጅት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት/ተወዳጅነት የነበረው ሲሆን፤ አለቤ በዝግጅቱ ላይ የሚቀርቡ እንግዶችም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የተቸገሩ ሰዎችን እንዲያግዙ/እንዲረዱ ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደርግ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስሙ የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን አቋቁሟል፡፡
 – – –
ጥር 7 ቀን 1997 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ ሲጓዙ በተፈጠረ አደጋ ሕይወቱ አልፏል፡፡ ከአለባቸው በተጨማሪ አብሮት የነበረው የካሜራና ኤዲቲንግ ባለሙያው ይልማ ቀለመወርቅም በአደጋው ሕይወቱ አልፏል፡፡ ከሞት የተረፈው ኤፍሬም ደስታ ‹‹የደግነት ትርጉሙን የማውቀው በአለቤ ነው፤ የሰው ችግር ያመዋል፤ ‹የለኝም› ማለት አይችልም፤ ለራሱ ከመኖር ይልቅ ለሌሎች መኖርን ይመርጥ ነበር›› በማለት ስለአለባቸው ተናግሯል፡፡
 – – –
የቀብር ስርዓቱ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስቲያን በተፈፀመበት ዕለት እጅግ በርካታ ሕዝብ በቦታው ተገኝቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ታላላቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም (BBC, Associated Press …) ለአለባቸው ሞት የዜና ሽፋን ሰጥተው ነበር፡፡
 – – –
አለባቸው ከዚህ ዓለም የተለየበትን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመጋቢት 2007 ዓ.ም የአለባቸው የመድረክ አልባሳትና የግል ቁሳቁሶች (ፎቶግራፎች፣ ዋንጫዎች፣ መፅሔቶችና ሕይወቱን የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም …) ለጥናትና ምርምር ተግባራት ግብዓት እንዲሆኑ በማሰብ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም ተሰጥተዋል፡፡
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኮሜዲያን አለባቸው ተካን እንደሚወዱትና እንደሚያደንቁት ተናግረዋል፡፡
አ ለ ቤ … የድሆች አባት!
ነፍስ ይማር!
Filed in: Amharic