>

"ጎበዝ ኢትዮጵያን ያህል ሃገር እንዴት በአንድ ሰው እጅና ላይ እንተዋለን፤ ምንስ እስኪሆን እንጠብቃለን?!? " (ያሬድ ጥበቡ)

“ጎበዝ ኢትዮጵያን ያህል ሃገር እንዴት በአንድ ሰው እጅና ላይ እንተዋለን፤ ምንስ እስኪሆን እንጠብቃለን?!? “

ያሬድ ጥበቡ
 
* የኦነግ ሠራዊት የምእራብ እዝ ኮማንደር የሆነውን ጃልመሮን በአማርኛ አደመጥኩት፣ እናም ተደመምኩ። “ተማሪዎቹን አላገትንም፣ ባንኮች አልዘረፍንም፣ የመንግስት ባለሥልጣናትን በአልሞ ተኳሾች አልገደልንም፣ ሁሉም ቀሽም መንግስታዊ ድራማዎች ናቸው” ይላል። አድምጡት! አማርኛ ሳይሆን ቅኔ ነው የሚናገረው!
—-
መንግስት ባለበት ሃገር ባንክ መዝረፍ ጨዋታ አይደለም። ብዙ ዝግጅት፣ እቅድ፣ ቅንጅት ይጠይቃል። በደርግ የመጀመሪያ ሁለት የሽግግር አመታት ወያኔ የአክሱም ባንክን ለመዝረፍ ሲሳካለት፣ ኢህአፓ የወልድያ ባንክን ለመዝረፍ ሲከሽፍበት፣ የቁጭራን ባንክ ለመዝረፍ ችሏል። ከዚያ ወዲያ ከደርግ ጋር በተደረጉ የ15 ዓመታት የትጥቅ ትግሎች አንድም ባንክ መዝረፍ የተቻለ አይመስለኝም። ለታጋዮች ባንክ መዝረፍ ትልቅ ክንዋኔ ስለሆነ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን የሚያኮራ ክንዋኔ በመሆኑ እንኳንስ ሊክዱት፣ ተሽቀዳድመው መግለጫ የሚያወጡበት ገድል ነው። ባህሉም ይህ በመሆኑ፣ ጃል መሮ እኛ አላደረግነውም ሲል ለመቀበል እንገደዳለን። ታዲያ ማን አደረገው? ኦሮሚያን የሚያስተዳድሩት አካላት ወይስ …?
በነዚህ የ”ሽግግሩ” 20 ወራት ብዙ ቀሽም ድራማዎች የተተወኑ ይመስላል። በቡራዩ በአንድ አነስተኛ ማህበረሰብ አባላት፣ በጋሞዎች ላይ የተካሄደውን ፍጅት ስናይ፣ ገና አዲስአበባ ከገባ አንድ ቀን ባልሞላው የኦነግ ጦር ሊካሄድ ይችላል ብለን የጠረጠርን ከነበርን ተሳስተናል። በዚያን ሰአት ኦነግ ቡራዩ የሚባል አዲስ የከተማ እድገትና ጋሞ የሚባል ህዝብ መኖሩንም አያውቅም ነበር። ስለሆነም ከግድያው በስተጀርባ ያለው ኦነግ የመሆን እድሉ እጅግ ጠባብ ነበር። በፖሊስ አልተጣራም፣ ወንጀለኞች አልተያዙም፣ ግልፅ የሆነ ተአማኒ የፍርድ ሂደት አልተካሄደም። ለምን? ፍጅቱን ማነረ ነበር ያካሄደው? ወይስ ኢትዮጵያችን ውስጥ የተፈጠረውን የደህንንት ክፍተት ተጠቅሞ የሚንቀሳቀስ የባእድ ሃይል አለ? መንግስት መልስ ሊሰጠን ይገባል።
ከቡራዩ አስቀድሞ የኢንጂነር ስመኝ ግድያ ነበር። ራሳቸውን ነው ያጠፉት ብለው መግለጨ  የሰጡን የፖሊስ አዛዣ ከመቅፅበት ከሥልጣናቸው ተነሱ። ወይስ እድገት ነው የተሰጣቸው? ግን ለምን? መልሱን ስለፈራነው አልጠየቅንም።
ከቡራዩ ቀጥሎ 20 የሚያህሉ ባንኮች በኦሮሚያ ክልል ተዘረፉ። የኦሮሚያ ክልል የደህንነት ሃላፊ የነበሩት ጄኔራል ከማል ገልቹ፣ የኦዲፒና የክልሉ ባለሥልጣናት እጅ እንዳለበት ቢነግሩንም ነገሩን ማካረር አልመረጥንም። ሽግግሩን እንዳይጎዳው በማለት ዝምታን መረጥን። የሚገርመው ግን ፌዴራል መንግስቱም ዝርፊያዎቹን ለማጣራት ኮሚሽን ማቋቋም አልመረጠም። ምንም ያልተደረገ ይመስል ዝምታን መረጠ። “ይሄ ነገር በኦነግ እየተመካኝ ባለሥልጣኖችን እያበለፀገ ነው እንዴ?” ብለን ብንጠረጥርም ቁስላችንን እየላስን መተኛቱን መረጥን።
ከባንኮቹ ቀጥሎ የሰኔ 15ቱ አሳዛኝ ክስተት ተፈፀመ። የአማራ ክልል መሪዎች በባህርዳር ተገደሉ፣ የጦርሀይሎቹ ጠቅላይ ኤታማዦር በቤታቸው ተረሸኑ። መንግስት ራሱ የሚያወጣቸው መግለጫዎች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መሆን ብዙ ጥያቄዎችን እንድናነሳ አስገደደን። በአደባባይ ጠየቅን። ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ሆነ ነገር አለሙ። ነፃ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ጠየቅን። ማን ሰምቶ! ሰው እንዴት የራሱን ተጠርጣሪነት ለማፅዳት ሲል እንኳ በሪሞት የሚቆጣጠረው የአጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም አይፈቅድም? ይባስ ብሎ ሰላማዊ ጋዜጠኞችን፣ የባልደራስ አባላትን፣ የአብን መሪዎችን አሰረ። ብዙዎቹን ለ48 ቀናት በጨለማ ክፍሎች አቆይቶ ቢለቅም እስካሁንም ያልተፈቱ አሉ። የፍርድ ሂደቱም የታዘብነው ነው። የታለ ነፃ ሚዲያዎቹ የሰአረ ገዳይ ነው የተባለውን ወጣት ቤተሰብ አነጋግረው የዘገቡልን? በ1953 በህዝብ አደባባይ የመፈንቅለ መንግስት የፍርድ ሂደት ያካሄደች ኢትዮጵያ ከ60 ዓመት በኋላ በ2012 የዚያን ተወዳዳሪ ግልፅነት ቢያቅታት፣ እንዴት ግማሹን ማድረግ እንኳ አይፈቀድላትም? ይሄ ብቻ እንኳ የተያያዝነው ፍትህ ሳይሆን ሸፍጥ መሆኑን በብቃት አያሳይምን? በወያኔ ጥላቻ ነው ዐይናችን የታወረው፣ ወይስ በቤተመንግስት ግብሮች ነው ዐይናችን የተጋረደው? ወይስ በጃል መሮ መጣብህ ቆፈን ተጨማደን ነው፣ ዜግነታችንን አሳልፈን የሰጠነው?
ዜግነት አልባ፣ እንዲህ እንዲህ እያልን ሶስት ወራት ወደተሸጋገረው ሃገራዊ ምርጫ እያመራን ነው። በተቀናቃኝ ተብዬ ፓርቲዎች መሪዎች ሳይቀር “ለሃገሪቱ ህልውና ወሳኝ ነው!” ተብሎ ወደሚፈከርለት ምርጫ እያዘገምን ነው። እውን ከዚህ ሃገራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊነትና እንደሃገር መቀጠል የሚወስን ምርጫ ማካሄድ ይቻላልን? ያውም በነሃሴ ዶፍ፣ አርሶአደሩ በአረም በተያዘበት ወር፣ ተዋህዶ ክርስትያኑ በፆም ፀሎት በተጠመደበት ሰአት እውን ነፃ ተአማኒና ኢትዮጵያን የሚያድን ምርጫን ማካሄድ ይቻለናልን? አይመስለኝም።
ምርጫ ግን አለን። ጃል መሮን ስሰማው ኢትዮጵያን የሚጠላ ሰው አልሰማሁም። ጃል መሮን ስሰማ በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ አማሮችን በጥላቻ የሚያይ አንደበት አልሰማሁም። ጃል መሮን ስሰማ ያዳመጥኩት፣ ትወናው ቆሞ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ ለኢትዮጵያ የሚል ጥሪ ነው። ከጃል መሮ የሰማሁት፣ የኢህአዴግ ሥልጣን ተገርስሶ፣ ነፃ፣ ፍትሀዊና ርቱእ ምርጫ ማካሄድ የሚችል ሁላችንንም ያካተተ ተአማኒነት ያለው ከትወና የራቀ የሽግግር መንግስት እናቁምና እኛም መሳሪያችንን አውርደን እንሳተፍበት የሚል ጥሪ ነው። “እሳት ነው የጨበጥነው፣ እንድንጠቀምበት አታስገድዱን!” የሚል የሰቆቃ ጥሪ ነው ከጃል መሮ አንደበት የሰማሁት። እስቲ እናድምጠው። እንዴት አንድ ሰው እንዳይቀይም ብለን ሃገርን ያህል ነገር ያልሆነ እሳት ውስጥ እንከታለን? ኢትዮጵያን ያህል ሃገር፣ እንዴት በአንድ ሰው እጅና በአንድ የጎልማሳ አእምሮ ላይ እንተዋለን? ጎበዝ ምን አይነት ቆፈን ነው ያጨማደደን? ጭንቀቴ ለምን እንደማይሰማችሁ እስቲ ንገሩኝ። ለምን? ለምን?
Filed in: Amharic