>

ወገኖቻችንን ባስቸኳይ እንታደግ! (ከይኄይስ እውነቱ)

ወገኖቻችንን ባስቸኳይ እንታደግ!

ከይኄይስ እውነቱ

 

ከክርስቶስ በዓለ ልደት ጋር በተያያዘ በዕለቱ ‹‹በእውነት ክርስቶስ ተወልዶልናል?›› በሚል ርእስ አንድ አጠር ያለ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በጊዜአችን በእምነት ሽፋን የተነሱ ሐሳውያን ቊጥራቸው ቀላል የማይባሉ ወገኖቻችንን ሕይወት እየጎዱና ቤተሰብ እንዲለያይ ምክንያት መሆናቸውን ችግሩ የደረሰባቸውን አዛውንቶች ዋቢ አድርጌ መግለጼ የሚታወስ ነው፡፡ በቡሃ ላይ ቈረቈር እንዲሉ ዘረኞችና የሥልጣን ጥመኞች አገራችንና ሕዝቧን የሚያምሱት ሳያንስ ቁጭ በሉዎችና ‹ጠንቋዮች› ምድራዊ ተስፋ ያጡትን ብቻ ሳይሆን ሥጋዊ ሕይወቴን አሻሽላለሁ ብለው በብዙ እንግልት ባህር ማዶ የተሻገሩ ወገኖቻችንን ሳይቀር ትዳር እያፈረሱና ቤተሰብ እየበተኑ ይገኛሉ፡፡ 

የዛሬው ትኩረቴ ራሷን ‹እህተ ማርያም› በሚል የምትጠራ አጭበርባሪ አንዴ እመቤቴ መልእክት ሰጥታ ልካኛለች፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ በቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገቡትን ቀዳሚትና ክርስቲያን ሰንበት (እሑድን) ሽራ በገዛ ሥልጣኗ ሰኞና ማክሰኞን ሰንበታት አድርጋለች፤ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙና ጆሮ የሰጧት ወገኖቻችንን ወደ ሀገር ቤት ካልተመለሳችሁ ከፍተኛ ጥፋት ይገጥማችኋል በሚል ማስፈራሪያ ቤተሰብ በትነው እንዲመለሱ ያደረገቻቸው አሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ንግሥተ ነገሥታት ኢትዮጵያ እንደምሆን ተነግሮኛል፣ ቤተመንግሥት ልገባ ነው እያለች ጥቂት የማይባሉ ወገኖችን እያነኆለለች ትገኛለች፡፡ 

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በዚህች ቊጭ በሉ የተጭበረበሩ ወገኖቻችን ጥፋት እንዳለ ሆኖ፣ አሁን የሚገኙበት ሁናቴ ማንም ሰው በጤነኛነት የሚያደርገው ባለመሆኑ ባስቸኳይ እንድንታደጋቸው ለኢኦተቤክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሚመለከተው መምሪያ እና በቤተክርስቲያኒቱ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ለሚንቀሳቀሰው ለማኅበረ ቅዱሳን ይህ መልእክት እንዲደርስና ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስዱ ለማሳሰብ ነው፡፡

በስም የተጠቀሰችው ጉድ ኮልፌ ዐጠና ተራ አካባቢ እንደምትገኝና ሰለባዎቿን በምታስተዳድረው ‹ድርጅት› (ሠራተኞችን ቀጥራ) ሰብስባ ኪራይ እያስከፈለች ማስቀመጧንና ከሷ ፈቃድ ውጭ ማንም ‹ተከታይ› ውልፍት እንደማይል ችግሩ ደርሶበት ከአሜሪካ የመጣ አንድ የጓደኛዬ ጓደኛ በአካል አግኝቼው በመረበሽና በማዘን ነግሮኛል፡፡ የዚህ ወንድማችን ባለቤት የተጠቀሰችዋን ቀጣፊ ንግግር በማኅበራዊ ሚዲያ ከሰማች በኋላ (ቢመክር ቢያስመክር እምቢኝ አሻፈረኝ ብላ) ጓዟን ጠቅላላ ሁለት ሕፃናት ልጆቻቸውን /ከትምህርታቸው አስተጓጉላ/ ይዛ ኮልፌ ዐጠና ተራ ከተባለችው አጭበርባሪ ቤት ገብታለች፡፡ ጉድ በል ሸዋ የሚያሰኝ ጉዳይ እየገጠመን ነው እኮ ወገኖቼ!!! እኔ የችግሩ ሰለባ ከሆነ ወንድማችን ሰምቼ እንጂ እንዲህ ዓይነቱን የቊጭ በሉዎች ተግባር በማኅበራዊው ብዙኀን መገናኛ (በተለይም የፈስ ቡክ ተጠቃሚም ባለመሆኔ) አልከታተልም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ይህንን መልእክት የምታነቡ ወገኖቼ ስለዚህች አጭበርባሪ ሴት ጉዳይ እንግዳ እንደማይሆንባችሁ በማመን ኮልፌ ዐጠና ተራ አለ የተባለውንና ወገኖቻችን የ‹ታገቱበትን› ቤት አድራሻ በመለየት ጸጥታ የሚያስከብር ፖሊስ ካለ ለፖሊስ በማሳወቅ እንዲሁም ከላይ ለጠቀስኳቸው ለቤተክህነቱና ለማኅበረ ቅዱሳን በፍጥነት ታሳውቁ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡

Filed in: Amharic