>

የዓባይ ግድብ ተደራዳሪዎች ሊጠነቀቁት የሚገባ ነጥብ!!!  (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የዓባይ ግድብ ተደራዳሪዎች ሊጠነቀቁት የሚገባ ነጥብ!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ይሄ የስምምነት ነጥብ “ቅኝ ግዛት!” ይባል እንደሆነ ነው እንጅ “የሀገር ሉዓላዊነትን መዳፈርና ብሔራዊ ጥቅምን መነጠቅ!” የሚለው ቃል ብቻ የሚገልጸው ግፍ አይደለም!!!
ይሄ ትናንትና ዝርዝር የስምምነት ነጥቦች ይወጡለታል ተብሎ በአሜሪካ አደራዳሪነት የተለቀቀው ባለ ስድስት ነጥብ የማስማሚያ ሰነድ አለመፈረሙ በጀን እንጅ ጎል ገብተን ነበረ!!!
ከዚህ አንጻር ተደራዳሪዎቻችን ምን ልብ ማለትና ምንን መጠንቀቅ እንዳለባቸው ባጭሩ ለማመልከት እሞክራለሁ፡፡ የስምምነቱ የውል ንድፍ እንደጠቆመው ቀጣዩ ለፊርማ እየተዘጋጀ ያለው ዝርዝር የስምምነት ሰነድ የዓባይን ውኃ በልኬትና በወቅት በማስቀመጥ እንዲፈራረሙ የሚዘጋጅ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ አደገኛው ነጥብ ይሄ ነው!!!
የዓባይን ውኃ አስመልክቶ በግድቡ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት የልኬት ስምምነት በአጠቃላዩ በዓባይ ወንዝ ላይ የተደረገ ስምምነት መሆኑን ተደራዳሪዎቻችን አልተገነዘቡም!!! ስላልተገነዘቡ ነው ይሄንን ቅድመ ፊርማ የስምምነት ንድፈ ሐሳብን ተስማምተው የወጡት!!!
ምን ማለቴ መሰላቹህ ከላይ ባልኳቹህ መልኩ ማለትም በዐባይ ውኃ ላይ የውኃ ልኬትና ወቅት ተጠቅሶ ከተፈረመ ወይም ስምምነት ላይ ከተደረሰ ሀገራችን ለመቸውም ጊዜ ቢሆን የዓባይን ወንዝ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ በፈለገችው ቦታ ላይ ገድባ ለመስኖ ለመገልገል አትችልም ማለት ነው!!!
ብልጦቹና አጭበርባሪዎቹ ግብጾች እንደፈለጉ የሚያቄሉት ደንቆሮ አገኙና ሌላው ቀርቶ ዝናብ የማይኖርበት የድርቅ ጊዜ እንኳ ቢያጋጥም ብለው ሳይቀር ግድቡ ውስጥ ያለው በደኅናው ጊዜ ወይም ከድርቁ በፊት የተያዘው ውኃ የሚለቀቅበትን አስገዳጅ ውል እስከማስፈር ድረስ ነው የሔዱት፡፡ ይሄ ማለት ሌላ ምንም ሳይሆን ምን ማለት መሰላቹህ የ1959እ.ኤ.አ. የግብጽና የሱዳን የዓባይን ውኃ በብቸኝነት የመጠቀም ስምምነትን ኢትዮጵያ እንድትፈርም ማድረግ ማለት ነው ሌላ ምንም ትርጉም የለውም!!!
ይሄ የስምምነት ነጥብ “ቅኝ ግዛት!” ይባል እንደሆነ ነው እንጅ “የሀገር ሉዓላዊነትን መዳፈርና ብሔራዊ ጥቅምን መነጠቅ!” የሚለው ቃል ብቻ የሚገልጸው ግፍ አይደለም!!!
የዛሬን አያድርገውና ጠንካሮቹ ነገሥታቶቻችን ለሽዎች ዓመታት ግብጽን ለምትጠቀመው የዓባይ ውኃ በየዓመቱ 50 ሽህ የወርቅ እንክብል ያስከፍሉ እንደነበር የራሳቸው የግብጾች የታሪክ ሰነድ ሳይቀር ይናገራል፡፡ ይሄ ነው ትክክለኛው አሠራር!!!
እነሱ ነዳጃቸውን “የተፈጥሮ ሀብት ነው!” ብለው ለማንም በነጻ እንደማይሰጡ ሁሉ እኛም ፈጣሪ የሰጠንን የተፈጥሮ ሀብት ለማንም በነፃ እንድንሰጥ የሚያስገድደን አንድም ዓይነት ሕግ የለም!!! ይሄው እነሱ ይሄንኑ የዓባይ ውኃ ለመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በቱቦ አሻግረው ለመሸጥ እየሠሩ አይደለም ወይ??? ይሄንን መብት ለኛ ለውኃው ባለቤቶች የሚነፍግ የትኛው የሞራል ሕግ ነው??? በሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል አሉ!!!
ይሄንን መደፋመር ያመጣው የጉልበት መበላለጥ ነው፡፡ አቅመቢስ ደካማ መሆናችንን ዐወቁ እንደፈለጉ ይጫወቱብን ጀመር፡፡ ለዚህ ነበረ አገዛዙ የዓባይን ግድብ ሥራ እጀምራለሁ ባለጊዜ ፈጽሞ መሆን እንደሌለበትና አሁን የገባንበት ዓይነት ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ የመስጠት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ መግባት ሊመጣ እንደሚችል በመግለጥ ፈጽሞ ጊዜው እንዳልሆነና ወደፊት በሚኖሩት ኢትዮጵያዊ የሆኑና የጦር ኃይላቸውን ቢያንስ በግብጽ ደረጃ የገነቡ ጠንከር ያለ ኢኮኖሚ በሚኖራቸው መንግሥታት ቢገደብ ነው ትክክል የሚሆነው ብየ ጽፌ የነበረው!!!
እንዲያ ያለ መንግሥት በሚኖረን ጊዜ እንገድብ ብንል ግብጽ ትንፍሽ ሳትል ግድባችንን መገንባት እንችል ነበር፡፡ አሁን ግን በጦር ኃይሏና በዘመናዊ የጅምላ ጨራሽ ትጥቋ ከዓለም በዚያ ሰዓት 13ኛ የሆነችው ግብጽ 40ኛ የሆነችውን ሀገራችንን ፈጽሞ አታስገነባትምና ወይም ደግሞ ያልሆነ ውል ውስጥ ተገደን ልንገባ የምንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላልና ፈጽሞ የማይሆን ነገር መሆኑን ተናግሬ ነበር፡፡ በዚያ ጽሑፍ የግድቡ ሥራ በዚህ በወያኔ አገዛዝ ዘመን ፈጽሞ የሚታሰብ አለመሆኑን የሚያረጋግጡ ሙስናን ጨምሮ በርካታ ችግሮችንና ግድቡ በዚያ ወቅት እንገድባለን የተባለበትን ከንቱ ምክንያቶች ሁሉ ገልጨ ነበረ፡፡ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተከስተዋል!!!
ሀገራችን በታሪክ ግብጽን ሐምሳ ሽህ የወርቅ እንክብል እያስከፈለች የዓባይን ውኃ እንድትጠቀም ታደርግ የነበረው የኃይል ሚዛኑ ወደ እኛ የሚደፋ ስለነበረ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ የኃይል ሚዛኑ ወደ ግብጽ ስለደፋ ማስከፈሉ ቀርቶብን ጭራሽ ተፈጥሯዊ የሆነውን በወንዛችን የመጠቀም መብታችንን አሳልፈን ሰጥተን ለኃይል ማመንጫ እንኳ በእነሱ ፈቃድና ይሁንታ ላይ ወድቀን ባቀረቡልን ስምምነት ለመፈረም ተዘጋጅተናል!!! አያሳዝንም???
ባጭሩ ተደራዳሪዎቻችን የውኃ ልኬትና የጊዜ ገደብ እየተጠቀሰ የዓባይን ውኃ የምንለቅበትና ግድቡን የምንሞላበት አንቀጽ ላይ ፈረሙ ማለት የ1959ኙን የግብጽና የሱዳን የዓባይን ውኃ በብቸኝነት የመጠቀም ስምምነትን ፈረሙ ማለት እንደሆነ ይወቁት ነው እያልኩ ያለሁት!!! ግልጽ አይደለም እንዴ???
ምክንያቱም በልኬትና በወቅት የሚጠቀስን የዓባይ ውኃ መጠን የመልቀቅ ግዴታ ውል ላይ ከፈረምን ሌላ ለመስኖ የሚያገለግል ግድብ ዓባይ ተፋሰስ ላይ ገንብተን ውኃውን ለመስኖ እንዳንጠቀም በልኬትና በወቅት የተጠቀሰው የውኃ መጠን ያስረናልና ነው!!! አሁንስ ግልጽ አይደለም???
ይሄንን ሰነድ ነው ደናቁርት ተደራዳሪዎቻችን ከሁለት ሳምንት በኋላ በዝርዝር ተገልጾ ለመፈረም ቀጠሮ የያዙት!!!
ለዚህ መድኃኒቱ ከዚህ ስምምነት በፊት በአስቸኳይ በዓባይ ውኃ ላይ ከተፋሰሱ ሀገሮች ጋር ፍትሐዊ የወንዙ ውኃ ክፍፍልን ማስቀደምና ስምምነት ላይ መድረስ ነው!!! ደንቆሮው አገዛዝ መቅደም የነበረበትን አለማስቀደሙ ነው እዚህ ችግር ላይ ልንወድቅ የቻልነው!!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! አገዛዙ ስምምነቱ ያዘለው አደጋ በዚህ ደረጃ ግልጽ በሆነበት ሁኔታ ስምምነቱን በተባለው ቀን ከፈረመ ግን ሆን ብሎ የሀገርህን ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት በማሰብ እንዳደረገው ዕወቅ!!! ተጠንቀቅ!!!
Filed in: Amharic