>

ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱኳን ሚደቅሳ ግልጽ ደብዳቤ

ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱኳን ሚደቅሳ ግልጽ ደብዳቤ

ዮሐንስ  መኮንን 
ጉዳዩ፦ ኦርቶዶክስ አማኞችን ለጥቃት የሚያጋልጥ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እርምት እንዲሰጥበት ስለመጠየቅ!
በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ ፓርቲ ሰሞኑን ሰሜን ሸዋ ሰላሌ ገብረ ጉራቻ ላይ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂዷል።
ማንኛውም ፓርቲ ሠላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ እስከተከተለ ድረስ ከደጋፊዎቹ ጋር የመሰብሰብ ዓላማውንም የማስተዋወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው እረዳለሁ።
ይሁን እንጂ ኦፌኮ ገብረ ጉራቻ ላይ በጠራው የምርጫ ቅስቀሳ ራሱን “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት” ብሎ በሚጠራው ኮሚቴ አባል በዲያቆን ኃይለሚካኤል ታደሰ አማካይነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማኞች እና አገልጋዮቿ ካህናት ላይ እጅግ አደገኛ እና ለጥቃት የሚያጋልጥ ቅስቀሳ ሲያደረግ ውሏል። የቤተክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ክብሯን አኮስሷል። የምእመኖቿንም ህሊና አማስኗል
እርስዎ የየሚመሩት የምርጫ ቦርድ በምርጫ ህጉ መሠረት የፓለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው የድርጊት መርሐግብር ከተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ውጪ ምንም ዓይነት የምርጫ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ በቅርቡ ማዘዙ ይታወቃል።
በተጨማሪም በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በምርጫ ቦርድ መካከል በተደረገ ውይይት ሠረት የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ ከአመጽ የፀዳ እንዲሆን ማሳሰቢያ የተሰጠ ሲሆን የፓለቲካ ፓርቲዎች ይህንን ሳያደርጉ ቢገኙ ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ እንደነበርም እናስታውሳለን።
ይሁን እንጂ ኦፌኮ የምርጫ ቦርድን ትእዛዝ እና መመሪያ በመጣስ በጠራው የምርጫ ቅስቀሳ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆንን ዜጎችን ሕገመንግሥታዊ የአምልኮ መብት የሚጥስ እና አማኞቹን ሰቀቀን ውስጥ የሚከት ለጥቃትም የሚያጋልጥ ጠብ አጫሪ ቅስቀሳ አድርጎብናል።
ከምርጫ ሕጉ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ “በህዝብ ደህንነት ሰላምና ተረጋግቶ መኖር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች’በሚለው ክፍል ሥር በአንቀጽ 492 “የተፈቀደውን የሃይማኖት ሥርዓት ማወክ፣ ማስተሃቀር የሚያስቀጣ ወንጀል ነው!” የሚለውን ድንጋጌ በአደባባይ ጥሷል።
ስለዚህም እርስዎ በኃላፊነት የሚመሩት የምርጫ ቦርድ ኦፌኮ ዜጎችን አላስፈላጊ ፍጥጫ ውስጥ ከሚከት እና ኦርቶዶክስ አማኞችን ለጥቃት ከሚያጋልጥ ጠብ ጫሪ ቅስቀሳው እንዲታቀብ እና ገርበጉራቻ ላይ አድርጎት ለነበረው ጥፋትም በይፋ  የእርምት እርምጃ እንዲወስድ እንዲያደርግ እንደ አንድ የቤተክርስቲያኒቱ አባል እና ኢትዮጵያዊ ግብር ከፋይ ዜጋ እጠይቃለሁ።
አመሠግናለሁ።
Cc;
– Office of The Prime Minister
– The Federal Supreme Court
– Federal Attorney General
– Ethiopian Human Rights Commission
– የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
Filed in: Amharic