>
5:13 pm - Sunday April 19, 6843

ታላቅ ክብር ለጋሞ ሽማግሌዎች ይሁን!!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ታላቅ ክብር ለጋሞ ሽማግሌዎች ይሁን!!!!

ያሬድ ሀይለማርያም
ለእውነት የቆሙ ችማግሌዎች እጦት፣ በካድሬ እና በመንጋ ፖለቲከኛ ክፉኛ ለተመታችው አገሬ የጋሙ ሽማግሎች ፍትውን መድሃኒት ናቸው። እንደ ጋሙ ሽማግሌዎች አይነት ቅን አሳቢ፣ የፍቅር መምህር፣ የተግባር ሰው፣ ደፋር እና ዝቅ ብለው የከፍታን ውሃ ልክ የሚያሳዩ ሽማግሌዎች ከየማህበረሰቡ ቢገኙ ከገባንበት ቅርቃር በቀላሉ ለመውጣት እድል ይኖረን ነበረ። በሽማግሌ እና በካድሬ መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ያልቻሉ ቀሳውስት፣ ሼኾች፣ አባገዳዎች፣ ፓስተሮች፣ መንፈሳዊ አባቶች ኮሽ ባለ ቁጥር አበል እየተከፈላቸው በየሆቴሉ ሲማማሉ እና በሕዝብ ስም እነሱ ሲታረቁ ቢውሉም መሬት ላይ ጠብ ያለ ነገር የለም።
የአገራችን ችግር ቅን አሳቢ እና ለእውነት የወገነ፣ ያመነበትን በትክክል የሚናገር፣ ክፉን የሚያወግዝን እና ጥሩውን የሚያበረታታ እውነተኛ ሽማግሌ፣ ደፋር ምሁር፣ ሃቀኛ ፖለቲከኛ፣ ሚዛናዊ ጋዜጠኛ እና መሰሪ ያልሆነ የአገር መሪ ይፈልጋል። ለጋሙ ሽማግሌዎች እና ሽማግሌዎቹንም ለሚያከብሩት የጋሙ ወጣቶች ትልቅ ክብር አለኝ። ጥሩ ምሳሌም ሊሆኑ ይችላሉ።
የአማራ ሽማግሌዎች ከወዴት አላችሁ? የትግራይ ሽማግሌዎች ከወዴት አላችሁ? የኦሮሞ ሽማግሌዎች እና አባገዳዎች ከወዴት አላችሁ? እነዚህን ክልሎች በተለየ ሁኔታ የምጠራው ሦስቱም ክልል ውስጥ ያለው እሳት አገሪቱን ወደ ከፋ ሁኔታ እየገፋት ያለ ስለመሰለኝ ነው። በማህበረሰብ ውስጥ ግጭት ሲፈጠር፣ ዜጎች በጠራራ ጸሃይ ሲታረዱ፣ እናት ከነልጆቿ ከቅዮዋ ተፈናቅላ ዱር ስታድር፣ ሕጻናት በነፍሰ በላዎች ታፍነው ገሚሱ ሲገደሉ፣ የዩንቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች በወሮበላ ታጣቂዎች ታፍነው ሲወሰዱ የመንግስት ክርን ቢዝል እናንተ የአገር ሽማግሌዎች የት ገባችሁ?
የጋሙ ሽማግሌዎች መንግስት ኖረም አልኖረ በአካባቢያቸው ላይ፤ በተለይም በገዛ ልጆቻቸው የማንም ሌላ ኢትዮጵያውን ሕይወትም ሆነ ንብረት እንደማይወድም ተንበርክከው፤ ግን ደግሞ በመንፈስ ልዕልና ከፍ ብለው አሳይተውናል። ከዛም አልፈው ይህን ትልቅ የሽምግልና እና የፍቅር መንፈስ ይዘው ከአንድ አገሪቱ ጫፍ ወድ ሌላው ጫፍ ተጉዘዋል። መንፈሳችሁ በሌሎች ሽማግሌዎች ይደር!!
ክብር ለጋሙ ሽማግሌዎች ይሁን!
መልካም ጥምቀት!
(የተጓዥ ማስታወሻ አውሮፕላን ተራ ሆኜ የጫርኩት)
Filed in: Amharic