>
9:49 am - Wednesday December 7, 2022

የባንዲራው አምባሻ - ዶ/ር ነጋሶ ሥጦታ ለኢትዮጵያ!!! (አሰፋ ሃይሉ)

የባንዲራው አምባሻ – ዶ/ር ነጋሶ ሥጦታ ለኢትዮጵያ!!!

አሰፋ ሃይሉ
በጥቅምት 1989 ዓመተ ምህረት ላይ የዶክተር ነጋሶን ፊርማ የያዘ አንድ አስገራሚ አዋጅ ወጣ፡፡ አዋጅ ቁጥር 48/1989 ዓ.ም. እየተባለ የሚጠራ አዋጅ ነው፡፡ ይህ አስገራሚ አዋጅ ‹‹የሰንደቅ ዓላማና ዓርማ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ›› የሚል ስም በአውጪዎቹ ተሰጥቶታል፡፡ ማሻሻያ አዋጁ የወጣው ከዚያ በፊት በተመሣሣይ የባንዲራ ጉዳይ ላይ በወጣው አዋጅ ላይ አንዲት የማሻሻያ አንቀፅን ለመጨመር ነበረ፡፡ ታዲያ የአዋጁ አስገራሚነቱስ ምን ላይ ነው? አስገራሚነቱማ – በማሻሻያ አዋጅ የተጨመረችው ያቺ አንድ አንቀፅ – ለምን ተብላ የተደነገገች ብትሆን ጥሩ ነው? በባንዲራው መሐል የምትደረገመውን ሰማያዊ አምባሻ መጠኗን ከፍ ለማድረግ!!
የወቅቱ የወያኔ/ኢህአዴግ ፓርላማ አባላት ከነበሩ እማኞች ቃል እንደተረጋገጠው – ያቺ አዋጅ የወጣችው – በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ – የራሱ የኢህአዴግ ተቋማት ቀደም ባለው የኢህአዴግ መመሪያና የባንዲራ አዋጅ መሠረት በባንዲራው መሐል እንድትገባ የተወሰነችውን ሰማያዊ አምባሻ መጠኗን እያሳነሱ ቁልፍ አሳክለው በመገኘታቸው እና ከነጭራሹ አምባሻዋን የጠሉና ልሙጡን የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ታሪካዊ ባንዲራ ማውለብለብን የመረጡ ክልሎችና የክልል ተቋማት በመበራከታቸው ነበረ፡፡ እና ለእነዚህ አምባሻዋን ለጠሉ ኢትዮጵያውያን እልህ ሲባል የወጣ አዋጅ መሆኑ ነው እንግዲህ ይህ የሰንደቅ ዓላማ ማሻሻያ አዋጅ፡፡
ይሄ የማሻሻያ አዋጅ የአምባሻዋን መጠን በማተለቅ አምባሻዋ በመሐል ቢጫው ቀለም ላይ የምታርፍ ሆና የአምባሻዋ ዙሪያ ክብ ግን ወደ ላይ የአረንጓዴውን፣ ወደ ታች የቀዩን ቀለም እስኪነካ ትልቅ ተደርጎ መቀመጥ እንዳለበት ያዛል!! እና የማልረሳው በአንድ ኮሌጅ ሕገመንግሥት ያስተምር የነበረ ጓደኛዬ አንዴ ይህንን የአምባሻዋን ማተለቂያ አዋጅ ለማስተማሪያነት ሊጠቀምበት ፈልጎ ካለኝ እንዳውሰው ሲጠይቀኝ ምን ብሎ ቢጠራው ጥሩ ነው? … ‹‹አሴ፣ ያ የፖምፑ አዋጅ አለሽ?›› ብሎኝ እርፍ፡፡ በሰዓቱ ግራ ገብቶኝ የለኝም አልኩት፡፡ ደግሞ ሲያስረዳኝ በሳቅ እየፈነዳሁ አመጣሁለት፡፡ ለካስ ኳስ ሲተነፍስ አየር የሚነፋበትን የእጅ መንፊያ ‹‹ፖምፕ›› ነበር እያለኝ ያለው፡፡ ምክንያቱስ? ይሄ ጉደኛ አዋጅ – የባንዲራውን ሰማያዊዋን አምባሻ በፖምፕ ነፍቶ ያተለቃት አዋጅ ነበራ!! (Lol!)
የዚህ የአምባሻዋ ማተለቂያ የፖምፕ አዋጅ መታወጁ ብቻ አልነበረም አስገራሚነቱ፡፡ ቀደም ብሎ የወጣውም ሆነ ይህ የባንዲራ አዋጅ የሚናገሩት መንግሥት በሚወከልበት ማናቸውም ኦፊሴላዊ ሥፍራ ሁሉ አምባሻው ያለበት ባንዲራ እንደሚውለበለብ ነው፡፡ የሐይማኖትንና የመንግሥትን መለያየት የሚደነግገው የኢህአዴግ ህገመንግሥት ራሱ እንኳ ስለ ፈጣሪ መንግሥት መቃረብ እና የፈጣሪን መንግሥት ስለመውረስ ለምዕመኖቻቸው የሚሰብኩ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት የኢህአዴግን መንግሥትን የሚወክለውን አምባሻውን የያዘ ኦፊሴላዊ አርማውን የማውለብለብ ግዴታ የሚጥልባቸው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በሐይማኖት ተቋም ውስጥ አይወከልም፣ የሚውለበለብለትም አርማ አይኖረውም፡፡ ሐይማኖትም በመንግሥት ተቋም ውስጥ አይወከልም፣ የትኛውም ሐይማኖት በመንግሥት ተቋም ውስጥ የሚውለበለብለት አርማ አይኖረውምና!!
አስገራሚውና አስቂኙ እውነታና በመሬት ላይ ያፈጠጠ ሃቅ ይሄ ሆኖ እያለ – የወያኔን መንበር በወረሱት የጊዜያችን የኦሮሞ ፅንፈኞችና ከእነሱ ጋር ባበሩት የብአዴን ሆዳሞች የሚመራው የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት – የፈጣሪንም ቃል ሳይፈራ፣ የዶክተር ነጋሶን ፊርማ የያዘውን የባንዲራ አዋጅም ሳይፈራ – በቤተክርስቲያን መንበረ ፀባኦት ጉልላት ላይ እንደ ዝንጀሮ እየተንጠላጠለ – ለቅዱስ ጥምቀቱ በዓል ቤተክርስቲያን እና ምዕመኖቿ የሰቀሉትን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ – ለምን አምባሻችንን ያልያዘ ባንዲራ ሰቀላችሁ ብሎ እየቀዳደደ ወደ መሬት የመጣል ድፍረት የተሞላበት ድርጊት – በእውነት ለሰሚውም ለተመልካቹም – እጅግ አድርጎ የሚዘገንንም፣ የሚደንቅም፣ እጅግ የሚያሳዝንም – የወቅቱን የወያኔ ወራሽ መንግሥት የድድብናና የማንአለብኝነት አቋም በአደባባይ የገለፀ ተግባር ነው፡፡
የእነዚህን የቀደሙትንና የጊዜያችንን ተረኛ ገዢዎች ዓይን ያወጣ የድፍረትና ማንአህሎኝነት ድርጊት ዝም ብዬ ሳስተውል ግን – አንድ ቀን ግን – የመረረው የኢትዮጵያ ህዝብ – ለመብቱና ለዕምነቱ ሆ ብሎ የተነሳ ዕለት – እነዚህን አረመኔ ገዢዎችና ጋሻጃግሬዎቻቸውን – እንዴት ያለ ህዝባዊ ፍትህ እንደሚሰጣቸው ሳስብ – መጪውን ጊዜ ለማየት በጣሙን እጓጓለሁ!!
ፈጣሪ እነዚህን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጭካኔ በትራቸውን የዘረጉ ፀረ ቤተክርስቲያን እና ፀረ-ኢትዮጵያ ጉግማንጉጎችን በኪነጥበቡ ይመልስልን! ዓይናችንንና ልቦናችንን ገልጠን – አረመኔነቸውን አበክረን እናስተውል ዘንድ ይርዳን!!
‹‹የባንዲራው አምባሻ – ዶ/ር ነጋሶ ሥጦታ ለኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የጀመርኩትን ፅሑፍ በዚሁ አበቃሁ፡፡
የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ከሁላችን ጋር ይሁን!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!
Filed in: Amharic