ፈተናዎቹ ወደ መፍትሔው እያቻኮሉን ነው!!!
ቀሲስ አባይነህ
* ክርስቲያኖችን ገድለው አካል የሚቆራርጡ ጠቋር አውሬዎች እንዴት ለመንግስት የምቾቱ መገለጫዎች ኾኑ? ወንጀለኞቹንስ በሕግ ለመጠየቅ እንዴት አፈረ????
***
፩. መስከረም ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋ እና በሐረር እኛ ኦርቶዶክሳውያን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተከለከልን።
፪. በደመራ በዓል በእነዚሁ አካባቢዎች ሰንደቅ ዓላማ መያዝም ኾነ ማውለብለብ አይቻልም ተባለ። በልብስ፣ በጌጣጌጥ፣ በጥልፍ እና የጥበብ አልባሳት ሁሉ ላይ ሰንደቅ ዓላማይቱን ለምን ዐይተናት አሉ። የለበሱ ሁሉ ተገፈፉ። እኛስ ባለዕዳ ነን፤ በሰንደቅ ዓላማይቱ የተዋቡባት የውጭ ሀገር ሰዎች ሁሉ ሳይቀሩ በየመንገዱ ኃላፊነት በጎደላቸው ተንገላቱ።
፫. የደመራ በዓል በደብረ ዘይት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይከበር ዋለ። ወንድሞቻችን በሰከረ ፖለቲካ ባለጊዜ ነን ባዮች መንገላታት ደረሰባቸው። ጥርስም ተነከሰባቸው።
፬. በጅማ ከተማ ለሰልፉ ዝግጅት ደፋ ቀና ሲሉ ከነበሩ ኦርቶዶክሳውያን ሕይወታቸውን የገበሩ ለከፋ አደጋ የተዳረጉ አሉ። ዛሬም በስጋት ያሉ በርካቶች ናቸው።
፭. ጥምቀተ ባሕር የከተማው አስተዳደር በመከልከሉ ምክንያት በሆሳዕና ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይከበር ሊውል ነው።
፮. በዓለ ጥምቀትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዐርማዋ እንዳታሸበርቅ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ጅኒ ተነሥቶበታል። እኛ እንተክላለን እነርሱ ይነቅላሉ። ነገ ግን ከፍ አድርገን መልሰን እንተክለዋለን።
፯. ሰላማዊ ሰልፍ የተጠራው ለበዓሉ ድምቀት እንደሚሉት ለማድረግ አልነበረም። በሰሜን በደቡብ በምዕራብ በምሥራቅ እና በመኻል ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየደረሰባት ያለው የተደራረበ ግፍ አንገፍግፏት ነው። ግን በግልጽ ቋንቋ የጽንፈኞችን ጫና የሚፈራው በከፊልም ደጋፊያቸው የኾነው መንግሥት ነገሩ አስፈራውም ወዲህም አልተመቸውም።
ሊመቸው የማይገባው ይመቸዋል፤ ሊመቸው የሚገባው ይጎረብጠዋል።
* ክርስቲያን ገድለው አካል የሚቆራርጡ ጠቋር አውሬዎች እንዴት የምቾቱ መገለጫዎች ኾኑ? ወንጀለኞቹን በሕግ ለመጠየቅ እንዴት አፈረ?
* የገደሉትን አናስቀብርም ብለው አስከሬን በማንሣት ላይ የነበሩትን አረጋዊ እዚያው ሲደርቧቸው አዎ መንግሥት ተመችቶታል።
* አራስ እናትን ከልጇ ነጥለው በሰይፍ ሲያርዱ ለመንግሥት የሳቁ ምንጭ ኾኖለታል።
* በጠራራ ፀሐይ በተደረገ ስብሰባ ኦርቶዶክሳውያንን ጠራርገን ከከተማችን እና ከአካባቢያችን እናስወጣለን ሲሉ መንግሥት ፖሊሲውን እያስፈጸሙለት በመኾኑ ተረጋግቶ በአድናቆት ይመለከታቸዋል።
* በገርበ ጉራቻ – በኩዩ ቅዳሜ ጥር ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. ደብረ ሊባኖስን የመውረስ ሊቃውንትን የማፍለስ ሥርዓተ ገዳሙን የማፍረስ ድንፋታ ሲጮህ ውሏል።
ይህ በራሱ የቅስፈት መጀመሪያ መኾኑ ነው። አምላከ ተክለ ሃይማኖት ሥራውን ይጀምረዋል። አላርፍ ያለች ጣት. . .
ለአብነት ጠቃቀስን እንጅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በበርካታ የፈተና እሳት ታጥራለች። ፈተናን አቆራርጦ ማለፍ የባሕርይዋ ነውና አለምንም ጥርጥር ታልፈዋለች። ስለዚህ እኛ ልጆቿ በደረሰባት ሁሉ በመቆዘም ጊዜ አናባክንም።
ወየሓውሩ እም ኃይል ውስተ ኃይል – ከኃይል ወደ ኃይል ይሔዳሉ እንዲል መጽሐፍ ከአንዱ ፈተና ወደ ሌላው በላይ በላዩ መሸጋገራችን መልእክት አለው። በቶሎ በቶሎ ፈተና በአናት በአናቱ በመደራረቡ ልባችን አይሸበር። ልንሠራው የጀመርነው ይፈጸም ዘንድ ፈተናዎቹ ወደ መፍትሔው እያስቸኮሉን ነው። ወደ ድሉ ሊያቀርበን ነውና አንገት እንዳንደፋ። እናም ሥራችንን አንተው!
ሆሳዕና ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!