>
5:13 pm - Tuesday April 19, 3403

የወያኔና ኦነግ ሕገ መንግሥትም ቢሆን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሶስት ቀለማት ያሉትን ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነው የሚጠቅሰው!  (አቻምየለህ ታምሩ)

የወያኔና ኦነግ ሕገ መንግሥትም ቢሆን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሶስት ቀለማት ያሉትን ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነው የሚጠቅሰው! 

አቻምየለህ ታምሩ
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለባችሁ በኦነጋውያን እየተሰቃያችሁ ያላችሁ ወገኖቻችን  ሆይ! ይህን ጽሑፍ በጥሞና አንብቡና ሕገ መንግሥት ተብዮውን ካላከበረራችሁት ሞተን እንገኛለን የሚሉትን ኦነጋውያንን ሕገ መንግሥት ተብዮውን እንዲያከብሩ ጠይቋቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሶስት ቀለማት ናቸው። የሰንደቅ ዓላማው ሦስቱ ቀለማት እኩል ሆነው አግድም የተቀመጡ ሲሆን ምሳሌያቸውም አረንጓዴው ተስፋ፣ ልምላሜና ሀብት፤ ቢጫው ሃይማኖት፣ አበባና ፍሬ፤ ቀዩ ደግሞ ፍቅር፣ መስዕዋትናነትና ጀግንነት ነው። አንዳንድ ሲባል የሰሙትን ሳይመረምሩ የሚደግሙ ካድሬዎች ይህንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ «ልሙጡ ሰንደቅ ዓላማ» ወይም «የድሮው ሰንደቅ ዓላማ» እያሉ ይጠሩታል። ይህ ግን የደጋሚዎቹን አጥልቆ ያለማሰብ ችሎታና አለማንበባቸውን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማን ትናንትና ዛሬ የሚያሳይ አይደለም።
ሕገ መንግሥት  ተብዮው አንቀጽ ሶስት ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚከተለውን ደንግጓል፤ 
አንቀጽ ፫ 
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ
1. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል። ሦስቱም ቀለማት አኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ።
2. ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢ ትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች አና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።
3. የፌዴራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል። ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ።
አማርኛ ለሚችል ማንኛውም ሰው የሕገ መንግሥት  ተብዮው አንቀጽ ሶስት ንዑስ አንቀጽ አንድ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም የተቀመጡ እንደሆነ ከደነገገ በኋላ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ስለሚጨመረውና ለጊዜው ግልጽ ስላልተደረገው አርማ ያትታል። የሕገ መንግሥት ተብዮው  አንቀጽ ሶስት ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ስለሚቀመጠው ብሔራዊ አርማ ይዘት ያብራራል። ይህ የሚያሳየው ሰንደቅ ዓላማውና በሰንደቅ ዓላማው መሐል ላይ የሚቀመጠው አርማው ሁለት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ነው። «የፌዴራሉ አባል ክልሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና አርማ ሊኖራቸው ይችላል» የሚለው የሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ ሶስት ንዑስ አንቀጽ ሦስት ደግሞ የበለጠ ግልጽ በማድረግ ሰንደቅ ዓላማና አርማ ሁለት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ያሳያል።
በመሆኑም  ኦነጋውያን ካላከበራችሁት በሚሉን ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሶስት መሰረት እንኳን ብንሄድ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ያሉት ሲሆን የአንቀጹ ሶስቱም ንዑስ አንቀጾች በተለይ ንዑስ አንቀጽ ሁለትና ሶስት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማውና ሰንደቅ ዓላማው መሐል ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ አርማው የተለያዩና ለየቅል  መሆናቸውን ያሳዩናል። ለዚህም ነው በፋሽስት ወያኔ ዘመን ሕገ መንግሥት ተብዮው ከጸደቀ በኋላ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ሳይቀር  በየ አደባባዩ ይውለበለብ የነበረው የኢትዮጵያ  ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሶስት ቀለማት  ያሉት  የኢትዮጵያ ሕዝብ  ሰንደቅ ዓላማ የነበረው።
ከምርጫ 1997 በኋላ የፋሽስት ወያኔ አገዛዝ ሕጋዊ ያደረገውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ የአርበኛ ልጆችን «የድሮው ሰንደቅ ዓላማ» አውለበለባችሁ እያለ ሲያስርና ሲያሳድድ የኖረው ራሱ የጻፈው ሕገ መንግሥት ምን እንደሚል እንኳ ሳያውቅ የራሱን ሕገ መንግሥት በመጣስ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ወያኔ  «ብሔራዊ አርማ» የሌለበትን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ሲያሳድድ የኖረው በ1988 ዓ.ም. ሰለ ሰንደቅ ዓላማ ያወጣውን  «የሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ ቁጥር 16/1988»  አዋጅ  ጥርስ በማርገፍ ነው። ይህ አዋጅ የሰንደ ዓላማውንና የዓርማውን ቀለማት ትርጉም በተናጠል አቅርቧል።
ባጭሩ በሕገ መንግሥት  ተብዮው አንቀጽ ሶስት መሰረት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም የተቀመጡበት ብቻ ነው። ሕገ መንግሥት  ተብዮው አንቀጽ ሶስት የሚያወራው ስለ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ አርማ ነው። የሕገ መንግሥት  ተብዮው አርቃቂ  ኮሚቴ የሕገ መንግሥት ተብዮውን አንቀጽ ሶስት ሲጽፍ የአርማና የሰንደቅ ዓላማ ልዩነት ተነስቶ ውይይት እንደተደረገበት፤  የኦሕዴዱ ግርማ ብሩ አርማና ሰንደቅ ዓላማ መካከል ስላለው ልዩነት ጠይቆ ልዩነት እንዳላቸው ከኮሚቴው አባላት መልስ እንደተሰጠው የሕገ መንግሥት ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ነጋሶ ጊዳዳ «ዳንዲ የነጋሶ መንገድ» በሚለው መጽሐፉ ነግሮናል።
 ስለሆነም «ብሔራዊ አርማው» እና ሰንደ ዓላማቅ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው። 
ስለዚህ የዛሬዎቹ ባለጊዜዎችም አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ አውለበለብህ ብለው ሊያስሩህ ወይም ሲቀሙህ ሲመጡ ካላከበርነውና ካላስከበርነው ሞተን እንገኛለን የምትሉትን ሕገ መንግሥት አክብሩ በላቸው። ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 106 «የሕገ መንግሥቱ የአማርኛ ቅጂ የመጨረሻው ሕጋዊ እውቅና ያለው ሰነድ ነው» በሚል የደነገገውን ጠቅሰህ በአማርኛ ቋንቋ አርማና ሰንደቅ አላማ የተለያዩ መሆናቸው በማሳት በሕገ መንግሥታችሁ አንቀጽ ሶስት ሕጋዊ የተደረገው ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ መሆኑን፤ ሰንደቅ ዓላማውን እንጂ የርዕዮተ ዓለም አርማቸውን የመሸከም ግዴታ እንደሌለብህ በማሳወቅ ሕገ መንግሥት ተብዮውን ሌላውን አክብሩ ከማለታቸው በፊት ራሳቸው በቅድሚያ ያከብሩት ዘንድ አስተምራቸው።
ከላይ የታተሙት ገጾች  በ1988 ዓ.ም. የወጣው  የሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ልዩነት የሚደነግገው   «የሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ ቁጥር 16/1988» ነው።
Filed in: Amharic