>
11:20 pm - Wednesday November 30, 2022

የግጭት ነጋዴዎች፣ የግጭቶች አረዳዳችን እና የመንግስት ዳተኝነት!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የግጭት ነጋዴዎች፣ የግጭቶች አረዳዳችን እና የመንግስት ዳተኝነት!!!

 

ያሬድ ሀይለማርያም

መንጋ እና ብልጽግና!!!

 
በየሰፈሩ ያሉ የግጭት ነጋዴዎች የሕዝብን ተስፋ ሊነጥቁና ሕዝቡንም ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊከቱ ስልት ነድፈው፣ በጀት በጅተው፣ የሰው ኃይል መድበው፣ የጦር መሳሪያ አከፋፍለው ይሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ መሆኑን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ በደንብ ይናገራል። ለእያንዳንዱ ክስተት እንግዳ እየሆንን ነው እንጂ ሂደቱን በጥሞና ለተከታተለ እና የግጭቶቹን ባህሪ ላጤነ ሰው ባለፉት ሁለት አመታት አገሪቱ ያስተናገደቻቸው ሁከቶች፣ ብጥብጦች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ የሰው ህይወት የቀጠፉ እና ንብረት ያወደሙ ጥቃቶች ሁሉ ምንጫቸው አንድ ወይም ሁለት ነገር ቢሆን ነው። ከአብዛኛዎቹ ግጭቶች ጀርባም ጥቂት አቀናባሪዎች እና ደጋፊዎች ይመስሉኛል ያሉት።
ይህ የጥፋት ኃይል እና በሕዝብ ግጭት ለማትረፍ ስልት ነድፎ የሚንቀሳቀሰው ቡድን አንድ መገለጫ ብቻ ያለው አይደለም። ፖለቲከኞ፣ ጋዜጠኛ፣ ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ አክቲቪስት፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ፣ ወላይታ፣ ሌሎች የብሄር መሰረቶች፣ ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ ምሁር፤ ሁሉንም ያቀፈና ያሳተፈ ነው።  የግጭቱ ሰለባዎች ደግሞ እንዲሁ ሁሉም ብሔር፣ ኃይማኖት፣ ጽዖታ እና እድሜ ላይ ያነጣጠረ ነው። አንድ ቡድን ላይ ወይም አንድ ኃይማኖት ላይ ወይም አንድ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም። ለዚህም እስኪ ዋና ዋና የሆኑትን ክስተቶች ዘርዝራችው እዩ እና ማን አጥቂ፤ ማን ተጠቂ እንደነበር አጥኑ።
ከፍተኛ ውጥረት እና ጉዳት ያስከተሉትን የጥቃት ክስተቶች ብቻ እንኳ ብናይ፤ ጅጅጋ፣ ቡራዩ፣ ጌድዮ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አዋሳ፣ መተማ፣ ጎንደር – ቅማንት፣ ወልዲያ፣ ከሚሴ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ሞጣ እና ሌሎች ሥፍራዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን ማየት ይቻላል። አንዱ ጋር ሙስሊሙ ሲጎዳ ሌላው ጋር ክርስቲያኑ ይጠቃል። አንዱ ጋር ኦሮሞው ጥቃት ሲፈጸምበት፤ ሌላው ጋር አማራው ይጠቃል። አንዱ ጋር ወላይታው ሲገደል፤ አንዱ ሥፍራ ቅማንቱ ይገደላል። የግጭት ነጋዴዎች ያላንኳኩት ቤት የለም።
ኦሮሞ እናት፣ ሙስሊም እናት፣ ክርስቲያን እናት፣ አማራ እናት፣ ትግሬ እናት፣ ወላይታ እናት፣ ሲዳማ እናት፣ ቅማንት እናት፣ ሱማሌ እናት፣ ጋሞ እናት፣ አፋር እናት፣ የኢትዮጵያ እናቶች አንብተዋል። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ጠአት መጠነቋቆል አይቻልም። ሁሉም ተጠቂ ሆኗል። ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንኳ በእስልምና እምነት እና በኦርቶዶክስ እምነት ላይ ያነጣጠሩት ጥቃቶች የግጭቱን ባህሪ እና ከጀርባ ያሉትን ኃይሎች ፍላጎት በደንብ ያሳያል።
ስለዚህ ችግሩ በአገር የመጣ፣ ሕዝብን እርስ በርሱ ለማጫረስ የተለመ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የተፈጠሩ ክፍተቶችን በደንብ ታሳቢ ተደርጎ የተቀናጀ እንደሆነ መረዳት የግድ ይላል። በየሳምንቱ በአዳዲስ የግጭት ክስተቶች ተሞልተው ያሳለፍናቸው ግጭቶች ዝም ብሎ ድንገት እንደ ሰደድ እሳት የተነሱ አይደሉም። ለእኔ ትላንት በቡራዩ በተፈጸመው ሰቆቃ እና ቅማንት ላይ በተፈጸመው አስነዋሪ ተግባር መካከል፣ ሲዳማ ውስጥ በተፈጸመው ሌላ ሰቆቃ እና ሞጣ ላይ በደረሰው አስነዋሪ ተግባር፣ ከሚሴ ላይ በደረሰው ጥቃት እና ሐረር ላይ በተከሰተው ግጭት፣ ጎንደር ላይ በተፈጸመው የሕጻናት ጠለፋ እና ግድያ እና ደንቢዶሎ በተፈጸመው የሴት ተማሪዎች ጠለፋ፣ በኦሮሚያ ክልል 86 ሰዎች በሞቱበት የቅርቡ ክስተት እና ድሬዳዋ ላይ በተፈጸሙ አስነዋሪ ተግባራት መካከል ግልጽ ዝምድና እና ትስስር ይታየኛል።
ሁላችንም የየራሳችንን በደል ብቻ ስለምናይ፣ ለሌሎች ጥቃት ትኩረት እና ተቆርቋሪነት ስለማናሳይ፣ የራሳችንን እያጋነንን የሌሎችን በደል ችላ ስለምንል ነው እንጂ ጥቃቱም ሆነ አጥቂዎቹ ኢላማ ያደረጉት አንድን ሰው፣ አንድን ብሔር፣ አንድ ኃይማኖት፣ አንድን የህብረተሰብ ክፍል ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደ አገር እና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ አንድ ማህበረሰብ ለማወክ እና ለማተራመስ የታለሙ ናቸው።
የመንግስት ሕግ በማስከበር እረገድ እያሳየ ያለው ለዘብተኝነት ወይም ዳተኝነት በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው እነዚህ የግጭት አትራፊዎች እራሱ መንግስት ጉያ ውስጥም እንዳሉ የክስተቶቹ ሁኔታና ባህሪይ፣ ክስተቶቹን ተከትሎ የመንግስት አካላት የሚያሳዩት ዳተኝነት፣ ክስተቶቹን ለማስቆም የሚደረጉ መንግስታዊ ጥረቶች አለመታየታቸው በመንግስት ውስጥ ሆነው እነዚህ ግጭቶችን ከሚያቀነባብሩ ሰዎች ጋር የሚሰሩ ወይም የሚተባበሩ ወይም ውጤቱን የሚጋሩ ሰዎች መኖራቸውን ነው የሚያመላክተው።
.
መንጋ እና ብልጽግና!!!
ኢትዮጵያ ውስጥ ፎቅ የምትሰሩ ሰዎች ይህን ልብ በሉ። በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ አሜኬላዎች፣ ጋጠወጦች፣ መንጋዎች አንድም በቅጣት አለያም በረዥም ጊዜ ትምህርት ከዚህ የወንጀለኝነት አስተሳሰባቸው እስኪጸዱ ድረስ ወይም ሕግ የሚያስከብር መንግስት እስኪመጣ ድረስ የሕንጻችውን ፊትለፊቱን ከላይ እስከታች በኮንክሪት ግጥም ብታደርጉት ይሻላችኋል። ለከተማ ውበት በኋላ ይታሰብበታል። በውጭ ምንዛሪ እና በከፍተኛ ገንዘብ የተገነባን ሃብት እንዲህ በደቂቃዎች ውስጥ ዶግ አመድ ሲያደርጉግ ማየት ያማል፤ ጉዳቱም የባለሃብቱ ብቻ ሳይሆን የአገር ነው። ለነገሩ መስጊድ እና ቤተክርስቲያ በእሳት ለኩሶ የሚጨፍር መንጋ ባለበት አገር ሕንጻ ቢወድም ምን ይደንቃል። መንጋ እና ብልጽግና፤ ሁለት የማይጣጣሙና አብረው የማይሄዱ ነገሮችን ይዘን የት ልንደርስ ይሆን ያስብላል። የጉድ አገር፤
መፍትሔው
+ መንግስት የሕግ የበላይነትን ያስከብር፣
+ በምርጫ ሰበብ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮችን በሚያደርጉ ፖለቲከኞች ላይ በአደባባይ ስም ተጠርቶ ተግሳጽ እና እንደ አስፈላጊነቱም ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ፣
+ የቆዩ እና የመረቀጹ ቁስሎችን አለባብሶ መሄድ ተገቢ ስለማይሆን እና አገሪቱንም ብዙ ዋጋ ሊያስከፍላት ስለሚችል ሳይውል ሳያድር አገራዊ የመግባቢያ እና የእርቅ መድረክ ሊኖር ይገባል።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic