>
11:19 am - Wednesday December 7, 2022

የሳና ማሪና (በዓለም በእድሜ ትንሽዋ ጠቅላይ ሚኒስትር) ዜና አንድ ገጠመኝ አስታወሰኝ  (አልይ እንድሬ)

የሳና ማሪና (በዓለም በእድሜ ትንሽዋ ጠቅላይ ሚኒስትር) ዜና አንድ ገጠመኝ አስታወሰኝ  

(አልይ እንድሬ)

     ይህችን አጭር ፅሁፍ ያዘጋጀኋት ከአንድ ወር በፊት የፊን ላንድ ትራንስፖረት ሚኒስትር የነበረችው ሳና ማሪና ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በመወዳደር ላይ በነበረችበትና እንደምታሸንፍም ሰፊ ግምት የተሰጣት መሆኑ እየተገለፀ ባለበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ በዓለም የብዙሃን መገኛኛ አውታሮች የ34 ዓመቷ ሳና ማሪና በእድሜ የዓለም ትንሽዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ ነው የሚል ዜና በስፋት ይለቀቅ ነበር፡፡ ያንን ዜና ስሰማ የአንድ ማዕከል ሃላፊ ጉዳይን አስታወሰኝና ይህችን ፅሁፍ ከተብሁ፡፡ ኃላፊው በስሩ ያሉ ሰራተኞችን የስራ ብቃት የላቸውም በማለት ዘወትር ያማርራል፡፡ በአንፃሩ ግን ማዕከሉ አዲስ የተቋቋመ እንደመሆኑ ሰራተኞቹ በቂ ስልጠናዎች እንዳላገኙም ይነገራል፡፡ ታዲያ በአንድ ውይይት ላይ በባለሞያዎቹ ላይ ያለውን የእውቀትና ክህሎት የላቸውም አስተያየቱን ባቀረበበት ወቅት አንደኛው የውይይቱ ተሳታፊ ተነስቶ ሰራተኞች ስራቸውን በአግባቡ ሊሰሩና ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ያን በማያደርግ ሰራተኛ ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፤ ከዛ በፊት ግን ስልጠና ያላገኙ ሰራተኞች ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ካለ በኋላ የአንዲት ወጣት እንስት ባለሞያ ስም በመጥቀስ ለምሳሌ “እከሊት“ አንድ ጊዜ እንኳን ስልጠና ሳታገኝ ነው እየሰራች ያለችው ሌሎችም ስልጠና የሚያስፈልጋቸው ሊኖሩ ይችላሉ፤ ስለዚህ ስልጠና የሚያስፈልጋቸው ተለይተው ስልጠና እንዲወስዱ ቢደረግ ስልጠና ወስደው ተልኳቸውን እማይወጡ ካሉ ግን ህግና መመሪያን በተከተለ አግባብ የእርምት እርምጃዎች የሚወሰዱበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ነው በማለት አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ ኃላፊው ለዚህ ሃሳብ መልስ ሲሰጥ ሌሎች ስልጠና እንደወሰዱ ገልፆ ከላይ የተጠቀሰችው እንስት ግን “ስልጠና ያላኳት ሴት ስለሆነች ነው ይላል፡፡ ስልጠናው የት ነው የሚሰጠው ተብሎ ሲጠየቅ ስልጠናው የፕላንት ቲሹ ካልቸር ስልጠና በመሆኑ አዲስ አበባ በሚገኘው በኢትዮጲያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት እንደሆነ ገልፆ በሴትነቷ አዝኖ እንዳላካት ያብራራል፡፡ 

      ብዙ እንስት ወጣቶች አስቸጋሪና ፈታኝ የሆነ የአየር ንብረት ባላቸው ቦታዎች ውስጥ የተግባር ስልጠና መውሰድን በሚጠይቁ የሞያ ዘርፎች (ለምሳሌ፡ ልዩ ሀይል፣ ፖሊስ፣ወ.ዘ.ተ) ተወዳድረውና ተመልምለው በአየር ንብረታቸው አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ ከወንድ አኩል ስልጠና በመውሰድ ተልኳቸውን በብቃት በመወጣት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ወንድ ያሳካውን ሴትም ማሳካት እንደሚችል በተግባራቸው ሲያረጋግጡ አዘውትረን ታዝበናል፡፡ ታዲያ ይህ  ከላይ የተጠቀሰው ስልጠና በረሃ ወይም ጫካ መሄድን የማይጠይቅ አዲስ አበባ በኢትዮጲያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት የሚሰጥ የፕላንት ቲሹ ካልቸር ስልጠና ሆኖ ሳለ “ሴት ናት ብየ ነው ያልፈቀድኩላት“ ማለት ምን ማለት ነው? የተለየ ችግር ሊያጋጥመኝ ይችላል ብየ አሰጋለሁ እና ስልጠናው ይቅርብኝ የሚል ሀሳብ ከራሷ ከባለሞያዋ አስካልቀረበ ድረስ (አልቀረበምም) የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አጠናቃ በመንግስት ስራ ላይ ከሁለት ዓመት በላይ ያገለገለችንና በማገልገል ላይ ያለችን እንስት ባለሞያ “ሴት ናት ብየ ስልጠና አላኳትም“ ማለት ዛሬም ድረስ በሴቶች ላይ ፆታዊ አድልዎ እየተፈፀመ መሆኑን ከማሳየት ውጭ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? በተለይ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት አድልዎ “ተምረዋል ወይም ሰልጥነዋል“ በተባሉ ግለሰቦች ሲፈፀም ያሳዝናልም ያሳፍራልም፡፡ በርግጥ እንደዚህ ዓይነት በተግባር የተደገፈ አግላይ አስተሳሰብ ገቢራዊ እሚሆነው ደረቅ ሳይንስን አነብንበው ሰርቲፊኬት በመያዝ ተማርን ከሚሉና በተግባራቸው ከፆታ አድልዎና ሃይማኖታዊ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው ከምሁር ለሚጠበቅ ሚዛናዊ አሰራር ራሳቸውን ማስገዛት የሚሳናቸው ግለሰቦች በአመራር ላይ ሲቀመጡ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ግለሰቦች በአመራር ደረጃ ሲቀመጡ ውሳኔ ሰጭ ስለሚሆኑ በእነሱ ውሳኔ ስር የሚያልፉ ግለሰቦችን በፆታ ወይም በሌላ በመሳሰሉ መገለጫዎች stigmatize በማድረግ ላገራቸው ብዙ መስራትና አገራቸውን መርዳት የሚችሉትን ሁሉ በኋላ ቀር አስተሳሰባቸው ጠፍንገው ይዘው ወደኋላ ማስቀረታቸው አይቀርምና ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ጎታች አስተሳሰብ ባላቸው መሪዎች በመታሰር የኋላ ቀር አስተሳሰባቸው ሰለባ ሆና ወደኋላ ብትቀር ኖሮ እንስቷና የ34 ዓመቷ ሳና ማሪና ዛሬ በዓለም በእድሜ ትንሽዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ባልበቃች ነበር፡፡ ከፈረንጆቹ ደሴምበር 16/2019 ጀምሮ ሳና ማሪና የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆና በመስራት ላይ የምትገኝ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ዜጎች ሙሉ አቅማቸውንና ተሰጥኦአቸውን በተግባር ላይ የሚያውሉበትና ላገራቸው አስተዋፅኦ የሚያበረክቱበት እኩል እድል ያገኙ ዘንድ እንደ አድልዎ የመሳሰሉ የቀጨጩ አስተሳሰቦችንና ተግባሮችን በጋራ መታገል የሁላችንም ሃላፊነት ነው የሚለው መልዕክቴ ነው፡፡

Filed in: Amharic