>
6:26 am - Tuesday July 5, 2022

ከተበዳይ ወገን መሪ ይፈልቃል ብሎ የጠበቀም አልነበረም!!! (ምስጋናው ብርሃኔ)

ከተበዳይ ወገን መሪ ይፈልቃል ብሎ የጠበቀም አልነበረም!!!

ምስጋናው ብርሃኔ
ባሕር ዳር፡- ጥር 14/2012ዓ.ም (አብመድ) ሕዝቡ ታሪክን ለማስታወሻነት አስቀምጦ ትውልድ እንዲማርበት በማድረግ ሀገር መገንባቱን፣ ጥላቻ ሳይሆን ፍቅርን ማስተማሩን ቀጥሏል፡፡
የዘረኝነት መንፈስ ድንገት እንደ ደራሽ ነፋስ ሽው ማለት ይዟል፡፡ ጉዳዩን አብዛኛው ሰው የተገነዘበው አይመስልም፤ እርስ በእርስ ተጋብተው እና ተዋልደው ለዘመናት የኖሩት ሁለት ብሄሮች እርስ በእርስ በጥርጣሬ መተያየት ጀምረዋል፡፡ ይህ ሲሆን የከፋ ጉዳት ያደርሳል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ በጥቂቶች የተጀመረው የዘረኝነት መንፈስ  ቀስ በቀስ ወደ ሕዝብ እና ወደ መንግስት መዋቅር መግባት ጀምሯል፡፡ ይህን ጊዜ ታዲያ የመንግስት መዋቅር በመሰንጠቁ በሁለት ጎራ ተከፍለው እርስ በዕርስ አንዱ አንዱን መወንጀሉ ቀጥሏል፡፡
በዚያች ሀገር ላይ ዓለምን የሚያሳዝን ተግባር ይፈጸማል ብሎ የገመተ ዓለማቀፍ ተቋም ግን አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ እንደ መንግስታቱ ድርጅት ያሉ ዓለማቀፍ ተቋማት ጉዳዩ ሪፖርት ቢደረግላቸውም ትኩረት አልሰጡትም፡፡ ዘረኝነቱ በሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር ተራገበ፤ አካባቢው በጥላቻ ተመርዞ አንዱ አንዱን ለማጥፋት ይፈላለጉ ጀመር፡፡በሀገሪቱ አብላጫውን ቁጥር የሚሸፍኑት ሁቱዎቹ  የቱትሲ ብሔርን እና በዘር የተጋመደውን ሕዝብ ለማጥፋት ይቀዳደሙ ጀመር፡፡ ይህን ሂደት በመንግስት የስልጣን ወንበር ላይ ያሉት ሁቱዎቹ ማስተባበራቸው ጉዳዩን አስቸጋሪ አደረገው፡፡
ዘመኑ በ1994 (እ.አ.አ) ነው፤ የመጠፋፋት ፊሽካው ተነፍቷል፡፡ አሁን ሁሉም ያገኘውን ያጠፋልኛል ያለውን መሳሪያ ሁሉ ይዞ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ መንግስትም ከማስቆም ይልቅ ጉዳዩን ማራገቡንና እገዛ ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ ዛቻው እና ቅራኔው ወደ ተግባር ተለውጦ ሁቱዎቹ ለ100 ቀናት ባካሄዱት የዘር ማጥፋት ዘመቻ 800 ሽህ ሰዎችን እስከወዲያኛው እንዲያሸለቡ አደረጉ፡፡ ይህን ያደረጉት ሁቱዎቹ ከጥፋት ዘመቻው መልስ ያገኙት ትርፍ ጸጸት ብቻ ሆነ፡፡ ስለ ጉዳዩ ቀድመው መረጃ ያላቸው ሰዎችም ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው እስከዛሬ ድረስ በጸጸት ይንገበገባሉ፡፡
ያን ዓለምንም ይሁን ሀገሪቱን ያሳዘነ ክስተት የሚያስረሳ መሪ ግን ማን ሊሆን ይችላል የሚለው ሌላው የራስ ምታት ነበር፡፡ ከተበዳይ ወገን መሪ ይፈልቃል፤ ሕዝቡንም በእርቀ ሳላም ወደ ሰላም እና አንድነት ይመልሳል ብሎ የጠበቀ ግን አልነበረም፡፡ የተበዳይ ወገን ግን በደሉን ሁሉ ረስቶ ሀገርን በማቆም ላይ የተመሠረተ ሀሳብ ይዞ ብቅ አለ፤ በፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ በኩል፡፡ ፖል ካጋሜ ከቱትሲ ብሔር ነው የተወለዱት፡፡ የፖል ካጋሜ ቤተሰቦች ወደ ዩጋንዳ በመሰደዳቸው አብዛኛውንም ጊዜ በዚያው በማሳለፋቸው ከእልቂት አምልጠዋል፡፡
ፖል ካጋሜ እንደ አውሮፓውያኖቹ አቆጣጠር 2000 ላይ ፕሬዘዳንት ሆነው ሲመጡ ሀገርን እንዴት አርጋግተው ልማትን ሊያመጡ ይችላሉ የሚለው ጥያቄ የብዙዎች የሀገሪቱ ዜጎች እና የምዕራባውያን ጥያቄ ነበር፡፡ የቀድሞው ወታደራዊ መሪ፣ የሀገሪቱ አራተኛው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ግን ያልተጠበቀ የሰላም እና የዕድገት ፍኖትን ተከተሉ፡፡ ፖል ካጋሜ የተከተሉት ፖሊሲ ሀገርን አረጋግቶ ወደ እድገት ጎዳና የምትንደረደር ሀገር ለመፍጠር አስችሏቸዋል፡፡ ሕዝቡ ታሪክን ለማስታወሻነት አስቀምጦ ትውልድ እንዲማርበት በማድረግ ሀገር መገንባቱን፣ ጥላቻ ሳይሆን ፍቅርን ማስተማሩን ቀጥሏል፡፡
አሁን ላይ በሩዋንዳ የትኛውም ዜጋ ሩዋንዳዊ እንደሆነ ከመናገር በቀር የቱትሲ አለያም የሁቱ ብሔር ነኝ ከማለት ሲቆጠብ ይስተዋላል፡፡ ዘር ቆጠራ እና ዘረኝነት አስከፊ እንደሆነ ኖረውት፣ ዋጋም ከፍለውበት አልፈውታልና፡፡ ታሪካቸውንም ለዓለም ማስተማሪያነት አድርገውታል፡፡ ሩዋንዳውያን ያላቸውን የቡና እና የሻይ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ኢኮኖሚያቸውን ይደግፋሉ፡፡ ከረሃብ እና ከችግርም ለመውጣት ወደፊት እየተስፈነጠሩ ነው፡፡
 “ብልህ ከሞኝ፣ ሞኝ ከራሱ ይማራል” እንዲሉ አበው ኢትዮጵያችንስ ከዚህ ተምራ ወደፊት ትስፈነጠር ይሆን?
ሰላም፣እድገት እና የሕዝቦቿ አንድነት ለኢትዮጵያ!
የመረጃ ምንጭ:- የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገጽ
Filed in: Amharic