>

ከሕወሓት ማእከላይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ..!!

ከሕወሓት ማእከላይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ..!!

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የሃሳብና የመስመር ልዩነት እየሰፋ መጥቶ አሁን ኢህአዴግ በያዘው መስመርና ከነበረው የግንባሩ አደረጃጀት ስርዓትና አሰራር ውጭ ጨርሶ እንዲፈርስ በማድረግ በይዘቱ አዲስ ፓርቲ እንዲመሰረት ተደርጓል፡፡ ህወሓት ይህ ህገ-ወጥና ፀረ-ዴሞክራሲ አካሄድ በተደጋጋሚ እንዲታረም፤ የሀገራችንን ህልውና አደጋ ውስጥ በገባበት ወቅት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊታዩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እንድናተኩር በፓርቲው ውስጥም ሆነ ለመላው የሃገራችን ህዝብ በተደጋጋሚ ስንገልፅ ቆይተናል፡፡
 ይሁን እንጂ ይህንን ሊቀበል ወይም ሊሰማ ዝግጁ ያልሆነው አመራር ኢህአዴግን በፀረ- ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈርስ እና ህዝብ ያልመረጠው አዲስ ፓርቲ ስልጣን ይዞ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ እንደ ድርጅት የነበረን ብቸኛው አማራጭ በጉዳዩ ላይ ህዝባችን በተወካዮቹ በኩል ተወያይቶ እንዲወስን፤ ይህንን ተከትሎም በመጀመሪያው አስቸኳይ ጉባኤያችን ላይ ሂደቱንና ሁኔታዎችን  በዝርዝር  እንዲወስን ማድረግ ነበር። በዚሁ መሰረት   ከተፈጠረው አዲስ ፓርቲ ጋር እንደማንወሃድ መወሰኑ ይታወቃል፡፡
በፓርቲ ደረጃ በያዝነው መስመር እንለያይ እንጂ  በህገ- መንግስታችን የተቀመጠውን የፌደራልና የክልል መንግስት ግዴታና መብት አክብረን እንደምንሄድ በግልፅ አስታውቀናል። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግን በያዘው ዓላማና ፕሮግራም  እስከ ቀጣይ ምርጫ የሰጠውን ሃላፊነት በጥብቅ ሊከበር ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ የኢህአዴግ ድርጅቶችን ነው የመረጠው። መንግስት እንዲመሰርቱም እንዲመሩም ስልጣን የተሰጣቸው እነዚህ ድርጅቶች ናቸው። ከዚህ ውጭ በማንአለብኝነት  ህዝብ ያልመረጠው ሌላ አዲስ ድርጅት ስልጣን እንዲይዝም ሆነ አገር እንዲመራም ማድረግ የህዝቡን ስልጣን መቀማትና ህገ መንግስቱን መርገጥ ነው። ሀገር እንዲመራ በጋራ ለተሰጠን ሃላፊነት በተወሰኑ ሃይሎች ፍላጎት ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ውሳኔዎች ሊወሰኑና ሊተገበሩ አይገባም።
በአሁኑ ጊዜ የህወሓት አመራሮችና አባላት በመሆናቸው ብቻ ከፌዴራል መንግስትና ከአዲስ አበባ አስተዳደር የኃላፊነት ቦታዎች እንዲነሱ እየተደረገ ነው። ይህ ተግባር በፍፁም ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም ይህ ሆነ ተብሎ እየተፈፀመ ያለው እና ከዚህ ቀደም የተፈፀመ  መረን የለቀቀ ተግባር ሊታረም ይገባል። ካልሆነ ግን ይህንን ተከትሎ ለሚፈጠር ሁኔታ ሀላፊነት  የሚወስደው ይህ ህገ-ወጥ  ተግባር እየፈፀመ ያለው አካል መሆኑን ግልፅ ሊሆን ይገባል።
የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ
መቐለ
ጥር13/ 2012 ዓ/ም
Filed in: Amharic