>

የአድዋው አርበኛና የወልወሉ ጀግና — ፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የአድዋው አርበኛና የወልወሉ ጀግና — ፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ !!!

አቻምየለህ ታምሩ
የበአመቱ የአድዋ  ድል ክብረ በዓል በተዘከሩ ቁጥር ከማይታወሱት የአድዋ ድል ቀዳሚ ጀግኖች መካከል በራስ መኮንን እየተመራ ከሐረር የዘመተው የአድዋ ጦርነት ግንባር ቀደም ዘማችና አምባላጌ ላይ ወራሪውን የጥሊያን ጦር ዶግ አመድ ያደረገው የጎንደሬ ጦር ነው። ከዚህ በፊት ባቀረብሁት ዝክረ ታሪክ  ማንነታቸው ስላልተናገረላቸውና ጀግንነታቸው ስላልተጻፈላቸው በራስ መኮንን እየተመሩ ከሐረር ተነስተው ወደ አድዋ ስለዘመቱት የጎንደሬ ጦር የአድዋ ድል ግንባር ቀደም ጀግኖች ታሪክና ማንነት ጽፌያለሁ።
የአድዋ ድል ግንባር ቀደም ዘማቾች ጦር የሆነው የጎንደሬ ጦር ከሚታወቁ ዝነኛ መሪዎቹ አንዱ ግራዝማች ጎሹ ነበሩ። ግራዝማች ጎሹ  የሐረር ሠራዊት ቀዳሚ የሆነውን  የጎንደሬ ጦር እየመሩ ወደ አድዋ የዘመቱት አርበኛውን ልጃቸውን ፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹን አስከትለው ነበር። በአድዋ ጦርነት ወጣት የነበሩት ፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ በአድዋ ጦርነት መጨረሻ ቆስለው በሕይወት ቢተርፉም በሁለተኛው ዙር በምስራቅ በኩል በመጣው የጥሊያን ወረራ ግን ወልወል ላይ  ከፋሽስት ጋር ተጋድለው ለአገራቸው በመውደቅ  ቀዳሚው ነበሩ።
የፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ አባት ግራዝማች ጎሹ የዐፄ ቴዎድሮስ ወታደር የነበሩ ሲሆን ዐፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ሲወድቁና ጦራቸው ሲበተን ወደ ሸዋ ተሻግረው ዳግማዊ ምኒልክ ያደራጁት ጎንደሬ የሚባለው የዐፄ ቴዎድሮስ ወታደሮች ሻለቃ መሪ ነበሩ። ዳግማዊ ምኒልክ ከሚወዱትና ከሚመኩበት ታማኝ ጦራቸው መካከል «ጎንደሬ» በሚል ያደራጁት የተበተነው የዐፄ ቴዎድሮስ  ወታደር የነበሩ ተዋጊዎች ሻለቃ ግንባር ቀደሙ ነበር። ከሐረር ወደ አድዋ የዘመተው የአድዋ ድል ግንባር ቀደም ዘማቾች ጦር  የጎንደሬ ሻለቃ መሪ  የነበሩት የግራዝማች ጎሹ የትውልድ ስፍራ የአንበሶች ምድር ቋራ ነው።
በልጅነታቸው አባታቸውን ተከትለው  ከሐረር ወደ አድዋ የዘመቱት አርበኛው  ፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ በኢትዮጵያ ላይ  በድጋሜ የተቃጣውን  የጠላት ወረራ ሲጋፈጡ የወደቁበት ቦታ ወልወል ይባላል። ፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ የወደቁበት የወልወል ግጭት ፋሽስት ኢትዮጵያን ለመውረር ሰበብ የሆነው ወይም አውሮፓውያኑ immediate cause የሚሉት አይነት ነው።  ወልወል በቀድሞው ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በኦጋዴን አውራጃ ውስጥ የሚገኝ የኢትዮጵያ መሬት ሲሆን እያንዳንዳቸው 50 ሜትር ርዝመት ያላቸው 359 የውሃ ጉድጓዶች ያሉበት ስፍራ ነው።  በኦጋዴኖቹ ትውፊት መሰረት እነዚህን ጉድጓዶች ያስቆፈሩት ኢትዮጵያን ከ1426 – 1460 ዓ.ም. ያስተዳደሩት  ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ናቸው።
ኅዳር 26 ቀን  1927 ዓ.ም. ረቡዕ ልክ ከቀኑ 9 ሰዓት ተኩል ሲሆን የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሶማሌ ላንድን  መንግሥት ወሰን  ተካላዮች ኮሚሽን ጠባቂ በነበረው የኢትዮጵያ ድንበር ጠባቂ ጦር ላይ ፋሽስት  አደጋ ጥሎ  የተቀሰቀሰው የወልወል ግጭት ወዲያው በሰማይ አውሮፕላኖች፤ በምድር ታንኮች ደርሰው በጣሊያኖቹ መድፍና ቦምብ ለጦርነት ባልተዘጋጀው የኢትዮጵያ ጦር ላይ ዘመቱበት።
በዋናው ኮሚሽነር በፊታውራሪ ታፈሰ ሀብተ ሚካኤልና በምክትሉ ዶክተር ሎሬንሶ ታዕዛዝ የሚመራው የኢትዮጵያ የድንበር ተካላዮች ኮሚሽን አባል የነበሩት የዐይን ምስክሩ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ «የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሶማሌላንድ የወሰን መካለል ታሪክ» በሚል ባዘጋጁት  በሰነድ የዋጀ መጽሐፋቸው ውስጥ  የአድዋው ጀግና ፊታውራሪ አለማየሁ  ጎሹ  በወልወሉ ግጭት እንዴት እንደወደቁ  ሲያስረዱ
«ፊታውራሪ አለማየሁ የመጀመሪያው [የፋሽስት] ተኩስ ሲሰሙ ካረፉበት ዘለው ተነስተው መሳሪያቸውን ያዙ። ወዲያው እሮምታው ተኩስ ስለቀጠለ ፎክረው ከምሽጋቸው ወጥተው መተኮስና  ጠላትን መጣል እንደጀመሩ በጠላት በኩል በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ»  በማለት ጽፈዋል።
በግጭቱ መሪውን ያጣው የፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ ጦር ቀኑን ሙሉ  ለዳር ድንበሩ ሲዋጋ  ውሎ ማታ ጨለማው ለዐይን ሲይዝ  በኢትዮጵያ ሠራዊት ደንብ  መሰረት  የወደቁትን መሪውን የፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹን አስከሬን አንስቶ በወሰን ተካላዮቹ በእነ ብላታ መርስዔ ኀዘን መኪና አስጭኖ ወደ አድውና ከዚያም ወደ ጅግጅጋ ተወስዶ  በጅግጅጋ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲቀበር አድርጓል።
ከወልወል ግጭት በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም.  የዳግማዊ ምኒልክን መታሰቢያ ሐውልት መርቀው ሲከፍቱ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግራቸው መደምዳሚያ ላይ «ወደፊትም ለነገሥታት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ትልልቅ ሥራ የሚሰሩና የሠሩ አርበኞች ለሥራቸውና ለስማቸው መታሰቢያ የሚሆን ሐውልት እየተከታተልን እናቆማለን» ባሉት መሰረት ወልወል ላይ ለወደቁት ጀግኖች ለነፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ  በወደቁበት ምድር  በወቅቱ የመታሰቢያ ሐውልት አቁመውላቸው ነበር። ይህን ንጉሡ ያቆሙትን የነፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹን  የመታሰቢያ ሐውልት ግን  የኢትዮጵያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪል የሆነው ፋሽስት ወያኔ አፈረሰው።
ፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ  በስማቸው የሚጠራ ኮሎኔል አለማየሁ አስፋው የሚባል የልጅ ልጅ ነበራቸው። ኮሎኔል አለማየሁ አስፋው  በደርግ ዘመን ጀኔራል ጌታቸው ናደው የኤርትራ አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት የኤርትራ ምክትል አስተዳዳሪ ነበሩ። ኋላ ላይ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚባል ጨካኝ አውሬ ኮሎኔሉንና ጀኔራል ጌታቸው ናደውን ሊገድል ሲነሳ ጀኔራሉ  አልሸሽም ብለው  በግፍ ሲገደሉ ኮሎኔል አለማየሁ ግን አብረዋቸው የነበሩትን  ወታደሮች  አስከትለው በመሸሽ ወደ ኢሕአፓ ኮብልለው ሸምቀዋል።
ኮሎኔል አለማየሁ ወደ ኢሕአፓ የገቡት ወዶገብ  እንደሆኑ  የጻፉ ቢኖሩም ኮሎኔሉን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ግን ወደ ኮሎኔል አለማየሁ አስፋው ወደ ኢሕአፓ የገቡት መንግሥቱን ባላዋ ሽሽትና  ለጊዜው መሆኑን፤ ይህን በማድረጋቸውም እንደ ጀኔራል ጌታቸው ናደው እንዳይገደሉ የወሰዱት የመጨረሻ አማራጭ እንደሆነ ያስረዳሉ። ኮሎኔሉ ከኢሕአፓ ጋር ትንሽ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ አሜሪካን አገር  በማቅናት «የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት»  የሚል ፓርቲ  ከባልደረቦቻቸው ጋር መስርተው ክፍሌ ወዳጆ የሚባል የወያኔ አጋሰስ  እስኪያፈርሰው ድረስ ደርግን እንደታገሉ  ከሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ በኋላ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አዛዥ የነበሩት ኮሞዶር ጣሰው ደስታ «የኢትዮጵያ አንድነት ትዝታና ትግል» በሚል በ1990 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ አውስተዋል።
በወልወልን  ግጭት  ሰበብ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ድል አድርጋ መውረሯ፥  ከአገራቸው  በፊት ቀድመው የወደቁትን  የፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ  ጀግንነት ሊቀማው አይችልም! ፊታውራሪ አለማየሁ  በወደቁበት ምድር በወልወል  የቆመው የጀግናው አርበኛ  የፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ ሐውልት በፋሽስት ወያኔ ቢፈርስም   ምድርን ከነታሪኳ የሚያጠፋ መአት እስካልመጣ ድረስ፥ የፊታውራሪ አለማየሁ ጀግንነትና ስም  ከወልወል ጉድጓዶች ጋር ለሁልጊዜ ይኖራሉ።
Filed in: Amharic