>
5:14 pm - Saturday April 20, 4497

ተማሪዎቹ የት ናቸው? (ዶቼ ቬለ - ታምራት ዲንሳ)

ተማሪዎቹ የት ናቸው?

ዶቼ ቬለ – ታምራት ዲንሳ 
* የተማሪዎቹ ወላጆች ተሰባስበው ተማሪዎቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ለመጠየቅ እና የክልሉ መንግስት ጫና ፈጥሮ ልጆቻቸውን እንዲያፈላልግላቸው የሚያደርጉት ጥረት “ጉዳዩን ለፖለቲካ ፍጆታ አውላችኋል!” የሚል ማስፈራሪያና ዛቻ ከክልሉ መንግስት እየተሰነዘረባቸው እንደሆነ ይገልጻሉ።
 
ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ታግተው የነበሩ እና መንግሥት ከዕገታ መለቀቃቸውን አስታውቆ የነበረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሁንም ድረስ ያሉበትን እንደማያውቁ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ።
የተማሪዎቹ ወላጆቹ ተሰባስበው ተማሪዎቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ለመጠየቅ እና የክልሉ መንግስት ጫና ፈጥሮ ልጆቻቸውን እንዲያፈላልግላቸው የሚያደርጉት ጥረት “ጉዳዩን ለፖለቲካ ፍጆታ አውላችኋል!” የሚል ማስፈራሪያና ዛቻ ከክልሉ መንግስትእየተሰነዘረባቸው እንደሆነ ይገልጻሉ
በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት መክንያት በማድረግ ወደየቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ማንነታቸዉ ባልታወቁ ሰዎች መታገታቸዉ ከተነገረ ከአንድ ወር በኋላ መንግስት ከዕገታ መለቀቃቸውን ይፋ ካደረገ ዛሬ 11ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ተማሪዎቹ በትክክል ያሉበት ቦታና ሁኔታ እስካሁን አለመታወቁ ግን እያነጋገረ፤ ወላጆቻቸዉን እያሰጋ ይገኛል። መንግስት ተማሪዎቹ ስለመለቀቃቸው ከማሳወቅ ያለፈ ከወላጆቻቸው እንዲገናኙ አልያም በትክክል ያሉበትን ሁኔታ ማሳወቅ አለመቻሉ ጥርጣሬ እንዳሳደረባቸው የተማሪዎቹ ወላጆች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
ልጆቻችን በትክክል ተለቀው ከሆነ መንግስት በአካል ሊያሳየን አልያም ድምጻቸውን ሊያሰማን ይገባ ነበር ሲሉም ይወቅሳሉ። ቀኑ እየረዘመ በመሄዱ የመንግስትን መግለጫ በጥርጣሬ መመልከት ስለመጀመራቸው እና ወቅታዊ መረጃ የሚሰጣቸው አካል እንደሌለም ነው ወላጆቹ የሚገልጹት።
ልጆቻችንን ለማግኘት ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው የሚሉት ወላጆቹ በሚኖሩበት የአማራ ክልል መንግስት በተደጋጋሚ አቤቱታቸውን ቢያሰሙም ተጨባጭ ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
ወላጆቹ ተሰባስበው ተማሪዎቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ለመጠየቅ እና የክልሉ መንግስት ጫና ፈጥሮ ልጆቻቸውን እንዲያፈላልግላቸው የሚያደርጉት ጥረት ጉዳዩን ለፖለቲካ ፍጆታ አውላችኋል በሚል ማስፈራሪያ እየተደረገብን ነው በማለት የክልሉን መንግስት ይወቅሳሉ።
 የመንግስት ባለስልጣናት ተማሪዎቹ ከዕገታ ተለቅቀዋል በማለት መግለጫ መስጠታቸዉ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ አለማቀፉ ኅብረተሰብ ጉዳዩን በትኩረት እንዳይከታተሉት እና ቸል እንዲባል መንገድ ከፍቷል በማለት ወላጆቹ ይናገራሉ።
 ከዕገታ ተለቀቁ የተባሉት ተማሪዎች ዛሬስ የት ናቸው?
 የፕሬስ ሴክሬታሪያቱን አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ጨምሮ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፣ የአማራ ክልል ፣ የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ስልክ በመደወል ተማሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ለመጠየቅና በዚህ ዘገባ ለማካተት ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካልን ቀርቷል።
Filed in: Amharic