>
10:23 am - Thursday August 18, 2022

የኦነጋውያን ታክቲኮች፤ ኦሮማራ፣ ኦሮትግሬ፣ ብልጽግና (መስፍን አረጋ)

የኦነጋውያን ታክቲኮች፤ ኦሮማራ፣ ኦሮትግሬ፣ ብልጽግና 

መስፍን አረጋ

በርከት ያሉ አገር ወዳድ ጦቢያዊ የፖለቲካ ሰዓሊወች (ለመሳል የሚፈልጉትን ስለሚስሉ ብቻ) ኦቦ ዐብይ አህመድን የጦቢያ መቅሰፍት ከሆኑ ኦነጋውያን ጋር የሞት ሽረት ግብግብ የገጠመ የጦቢያ መድሕን አስመስለው ይስሉታል፡፡  

ዐምባገነን በሚያስብል ደረጃ መከላከያንና ደሕንነትን ጨምሮ ሁሉን በጁ በደጁ ያደረገው፣ ያሻውን ሹሞ ያሻውን የሚሽረው፣ በእስክንድር ነጋ ላይ ግልጽ ጦርነት ያወጀው፣ ክርስቲያን ታደለን በጨለማ እስርቤት የሚያሰቃየው፣ ያማራ ብሔርተኝነት ያሰጋኛል በማለት ዐብንን ያሽመደመደው፣ ያማራን ቆፍጣና አመራሮች ጨፍጭፎና አስጨፍጭፎ የራሱን ስልቦች ባማራ ሕዝብ ላይ የጫነው ዐብይ አህመድ፣ ለኦነጋውያን ሲሆን ግን የተመኙትን እንዲዘርፉ፣ ያሻቸውን እንዲደሰኩሩ፣ የፈለጉትን እንዲያፈናቅሉ፣ እንዲያግቱና እንዲገድሉ ሙሉ ነጻነት ለምን ሰጣቸው ተብለው ሲጠየቁ ግን ማጣፊያው ያጥራቸውና ውሃ የማይቋጥሩ ተልካሻ ምክኒያቶችን ይደረድራሉ፡፡   

እውነታው ግን ኦቦ ዐብይ አህመድ የጦቢያ መድሕን ሳይሆን የጦቢያ መቅሰፍት መሆኑ ነው፡፡  ኦቦ ዐብይ አህመድ የጦቢያ መቅሰፍት መሆኑን ለመረዳት ደግሞ የፖለቲካ ተንታኝ መሆን ሳያስፈልግ ማንን እየተንከባከበ ማንን እንደሚያዋክብ መታዘብ ብቻ ይበቃል፡፡  በርግጥም ኦቦ ዐብይ አህመድ ጦቢያን ሊገድላት ቆርጦ የተነሳ ቀንደኛ ኦነጋዊ ነው፡፡  በትሕነግ ጊዜ የኦነግ ህቡዕ ሰላይ የነበረው ዐብይ አህመድ፣ ‹‹ከለውጡ›› በኋላ ደግሞ የኦነግ ህቡዕ መሪ ሁኗል፡፡

ዐብይ አህመድና ጃዋር ሙሐመድ በዘዴ እንጅ በግብ አንድ አካል አንድ አምሳል ናቸው፡፡  ግባቸው ደግሞ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮምያን አጼጌ (empire) መገንባት ነው፡፡  ይህ ከሆነ ታዲያ ዐብይ አህመድና ጃዋር ሙሐመድ በጀርባ እየተላላሱ በግንባር የሚቧቀሱ ለመምሰል የሚጣጣሩት ለምንድን ነው? 

ለታክቲክ ነዋ!

ኦሮማራ በብአዴን ጫንቃ ስልጣን መጨበጫ ታክቲክ ነበር፡፡  ኦሮትግሬ በወያኔ ጫንቃ አማራን እንዲሁም ትግሬን ባጠቃላይ ደግሞ ሐበሻን ማዳከሚያ ታክቲክ ነው፡፡  ብልጽግና ደግሞ በአልኦሮሞ (ኦሮሞ ባልሆኑ) አገር ወዳድ ጦቢያዊያን ጫንቃ ጦቢያን ወደ ኦሮምያ የመቀየር መቋጫ ታክቲክ ነው፡፡ 

  1. የኦነግን ገሀድ ክንፍ የሚመራው ጃዋር ሙሐመድና ፊታውራሪወቹ (በቀለ ገርባ፣ መራራ ጉዲና፣ ከማል ገልቹ፣ ሽመልስ አብዲሳ፣ ወዘተ. ) ይበልጥና ይበልጥ ሲጸንፉ (ጽንፈኛ ሲሆኑ)፣ የጽንፈኝነት ሰለባወች እንደ አሸን በፈሉበት ኦሮምያ በተሰኘው ክልል ውስጥ በስፋት ይደገፋሉ፡፡  በተጨማሪ ደግሞ በፀራማራ ትርክታቸው የትግራይ ወየንቲወችን ከጎናቸው ያቆማሉ፡፡  
  2. በተቃራኒ ደግሞ ጃዋር ሙሐመድና ፊታውራሪወቹ የኦነግን ህቡዕ ክንፍ የሚመራውን ዐብይ አህመድን ለይምሰል ያህል በአሃዳዊነት አምርረው ሲከሱትና ሲወቅሱት፣ ግለሰቡ በአልኦሮሞወች (ኦሮሞ ባልሆኑ አገር ወዳድ ጦቢያውያን) ዘንድ በይበልጥ እንዲታመንና በስፋት እንዲደገፍ ያደርጉታል፡፡  ለምሳሌ ያህል ለማ መገርሳ ከዐብይ አህመድ ጋር ሳይጣላ የተጣላ የሚያስመስለው የተንኮታኮተውን የዐብይ አህመድን አልኦሮሟዊ ድጋፍ (non-oromo support) መልሶ ለመካብ በማሰብ ሲሆን፣ ሐሳቡ ደግሞ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተሳክቶለታል፡፡  ለማ መገርሳ በሚያስወራው ደረጃ ከዐብይ አህመድ ጋር በእውነት ተጣልቶ ቢሆን ኖሮ፣ ዐብይ አህመድን በቀላሉ መገልበጥ በሚችልበት በቁልፍ ስልጣኑ ላይ ላንድ ሰዓት እንኳን ባልቆየ ነበር፡፡      

በዚህ ዓይነት ክሌካቻ (ባለ ሁለት ክራንቻ፣ two-pronged) ታክቲክ፣ ኦነግ ጃዋራዊ እጁን በኦሮምያና በትግራይ ላይ፣ ዐብያዊ እጁን ደግሞ በቀረው ጦቢያ ላይ በመጫን ጦቢያን በሁለት እጆቹ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ፀረጦቢያ እቅዱን በቀላሉ ማስፈጸም ይችላል፡፡ 

የኦነግ ጥንካሬ ከራስ የመነጨ ውስጣዊ ጥንካሬ ሳይሆን በሌላው ድክመት ላይ የተመረኮዘ ውጫዊ ጥንካሬ በመሆኑ፣ ለጦቢያ አስጊ የሚሆነው አገር ወዳድ ጦቢያውያን እስከተዳከሙ ድረስ ብቻና ብቻ ነው፡፡  አገር ወዳድ ጦቢያውያንን እያዳከመ ያለው ደግሞ መሠሪው ኦነጋዊ ኦቦ ዐብይ አህመድ ነው፡፡   በመሆኑም የኦነግ እቅድ ተሳክቶ ጦቢያ እንዳትፈርስብን የምንጨነቅ ጦቢያውያን ሁሉ ሙሉ ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን በገሃዱ ኦነጋዊ በጃዋር ሙሐመድ ላይ ሳይሆን በሕቡዑ ኦነጋዊ ባብይ አህመድ ላይ ብቻና ብቻ መሆን አለበት፡፡

ባንወደውም ልናደንቀው የሚገባንን የኦነግን ክሌካቻ ታክቲክ በተመለከተ ደግሞ የሚከተለውን መሠረታዊ ጥያቄ መጠየቅ የግድ ነው፡፡  ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በመንደር ተለያይቶ ይገዳደል የነበረው፣ ስለ ታክቲክ ምንም ፍንጭ ያልነበረው ኦነግ፣ አሁን በድንገት ተነስቶ የወጣለት ታክቲከኛ ለመሆን እንዴት ቻለ?  

ይህን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ የጦቢያ መሠረታዊ ጠላቶች ወደሆኑት ኸርማን ኮኸንን (Herman Cohen) ወደመሳሰሉት የዐረቡና የምዕራቡ ዓለም ፓሮቻዝከኛወች (ማለትም የሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochazka) ሐሳብ አቀንቃኞች) ዓይኖቻችንን መወርወር ግድ ይሆንብናል፡፡    

    መስፍን አረጋ 

   mesfin.arega@gmail.com  

Filed in: Amharic