>
5:13 pm - Wednesday April 20, 6788

የማይተማመኑ መሪ እና ተመሪ (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

የማይተማመኑ መሪ እና ተመሪ

በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ ወንጀለኞችን አድኖ ለፍርድ ሊያቀርብ ወዘተ… ስንቴ ምሎ፣ ስንቴ ተገዘቷል? ያው ግን አድሮ ቃሪያ ነው። የሰዎች አእምሮ ግን ሁሉንም ይመዘግባል። የመንግሥት ቃል ኪዳኖች አፋዊ መደለያ መሆናቸውን እየተረዳ መምጣቱ አይቀሬ ነው። በስተመጨረሻ እምነቱ ተሸርሽሮ ያልቃል። አሁን ተሸርሽሮ የት እንደደረሰ እንጃለት!
——
ካፒታሊስቶቹ አገራት “ክሬዲት ሂስትሪ” (የብድር ታሪክ) የሚሉት ነገር አላቸው። አንድ ሰው ከባንኩ በብድር ገንዘብ የተለያዩ ነገሮችን መሸመት ይፈቀድለታል። የሚያገኘው የሸመታ ብድር መጠን የሚወሰነው ግን ከዚህ ቀደም የብድር አከፋፈሉ ሁኔታ እየታየ ነው። ብድር ሳያዛባ የሚከፍል ከሆነ የተለያዩ የብድር ዕድሎች ተጨማምረው ይመቻቹለታል፤ አለበለዚያ ግን የቀድሞው የመበደር አቅሙን የሚያክልም ላያገኝ ይችላል። እምነት የሚገነባው እንዲህ ነው።
ብዙ ነጋዴዎች አሉ። መሥራት የማይችሉትን ቃል የሚገቡ፣ ማድረስ በማይችሉት ቀን ሊያደርሱ ምለው ተገዝተው ሥራ የሚረከቡ። ሥራው ሲበላሽባቸው ወይም በጊዜው አልደርስ ሲላቸው ደግሞ ይሰወራሉ፤ ስልክ እንኳን አያነሱም። ሥራውን ከማበላሸታቸው በላይ ድክመታቸውን አለማመናቸው እና እውነታቸውን መጋፈጥ አለመቻላቸው ደግሞ የባሰ ያበሽቃል። ለወደፊቱ ምን ይደረግ ለሚለው እንኳን አብረው ለመምከር አይመቹም። እነዚህ ሰዎች የአሠሪያቸውን እምነት ደግመው አያገኟትም! የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራም እንዲህ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ ወንጀለኞችን አድኖ ለፍርድ ሊያቀርብ ወዘተ… ስንቴ ምሎ፣ ስንቴ ተገዘቷል? ያው ግን አድሮ ቃሪያ ነው። የሰዎች አእምሮ ግን ሁሉንም ይመዘግባል። የመንግሥት ቃል ኪዳኖች አፋዊ መደለያ መሆናቸውን እየተረዳ መምጣቱ አይቀሬ ነው። በስተመጨረሻ እምነቱ ተሸርሽሮ ያልቃል። አሁን ተሸርሽሮ የት እንደደረሰ እንጃለት!
የሚያሳዝነው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደነዚያ አባይ ነጋዴዎች መሆኑ ነው። ስህተት በስህተት ላይ እየሠራ ዜጎች “ኡኡ…” ብለው ሲጣሩ ይሰወራል። ድምፁን አጥፍቶ እንዳላየ፣ እንዳልሰማ ይሆናል። ትንሽዬ ስኬት ሲኖር ካላመሰገናችሁኝ የሚል አካል፥ ጉልህ ጥፋቱን ለማስተካከል ቀርቶ ለማመን እንኳን ድፍረቱ የለውም። በዚህ እምነት ያጡ ዜጎች አማራጭ መፈለጋቸው አይቀርም። መንግሥት ሥራውን በአግባቡ ለመወጣት አለመቻል እምነት ማጣት ተጎጂዎች እና ጥበቃ የሚፈልጉ ወገኖችን ሌሎች አማራጭ የደኅንነት መጠበቂያ መንገድ ሲፈልጉ፣ በዚህ የልብ ልብ የሚሰማቸው እኩይ ወገኖች ደግሞ አጋጣሚውን ተገን አድርገው ወንጀላቸውን ያጠናክራሉ። የመንግሥት ድብብቆሽ ችግሩን ያከፋዋል እንጂ አያቀለውም።
ሰሞኑን የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ የቁጥር ጉዳይ ብቻ አይደለም። ለቁጥር ለቁጥር የትራፊክ አደጋ በየቀኑ ብዙ እጥፍ ሰዎችን ይገድላል። ነገር ግን የትራፊክ አደጋ እንዲህ ታቅዶ የሚሠራ ወንጀል አይደለም። ገጪውም ተገጪውም ሳይፈልጉ የሚወድቁበት መከራ ነው። እንዲያም ሆኖ የትራፊክ አደጋንም ቢሆን የሚቀንሱ ሥራዎችን እንዲሠራ መንግሥት ኀላፊነት አለበት። የተደራጁ ወንጀለኞች ከሚፈፅሙት ወንጀል ሰዎችን መጠበቅ የማይችል መንግሥት ግን ጭራሽ የመንግሥትነት ማዕረግ አይገባውም።
Filed in: Amharic