>

እገታው የሽብርተኞች የምርጫ ቅስቀሳ ዘይቤ ይሆን እንዴ ? (ሳምሶን አስፋው - ቋጠሮ)

እገታው የሽብርተኞች የምርጫ ቅስቀሳ ዘይቤ ይሆን እንዴ ?

 

ሳምሶን አስፋው – ቋጠሮ

 

የመንግስት ባለስልጣናት አሰራር ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በመከልከል ከዜጎች ደህንነትና ከህዝብ መብት ይልቅ ለመንግስት መልካም ገጽታ ሲጠነቀቁ እያየን ነው፡፡

ከታጋቾች ህይወት ይልቅ እገታው በመጪው ምርጫ ውጤት ላይ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ አንድምታ ያሳሰባቸው ይመስላል (ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ተደብቀው እንጂ አልታገቱም እስከማለት መድረሳቸውን ልብ ይሏል)፡፡

በለጋ ወጣቶች ህይወት የፖለቲካ ቁማር መጫወት ይዘገንናል!!! ሊፈጸም የማይችል ግን አይደለም፡፡ እገታው ገዥው መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ማስጠበቅ አይችልም! የሚል አጀንዳ የተሸከመ የአክራሪ ብሄርተኞች የእጅ አዙር የምርጫ ቅስቀሳ ቢሆንስ? ብሎ መጠርጠር ይቻላል፡፡በሌላ አገላለጽ “አፈና” የሽብርተኞች የምርጫ ቅስቀሳ ዘይቤ ይሆን እንዴ ብሎ መጠየቅም ይቻላል፡፡ወፍ እንዳገሩ  . . ይባል የለ ፡፡

በተለይ የአክራሪ ብሄርተኞች የእጅ አዙር የምርጫ ቅስቀሳ ቢሆንስ? የሚለውን ጥርጣሬ የሚያጭረው አጋቾቹ እስካሁን ምንም ጥያቄ አለማቅረባቸው ነው፡፡ አጋቾቹ የራሳቸው ጥያቄ ከሌላቸው ፤ ምናልባት መንግስትን (ገዥውን ፓርቲ) በማሳጣት የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ያሰበ 3ኛ አካል ቀጥሯቸው ሊሆን ይችላል የሚለው ጥርጣሬ ጎላ ብሎ ይከተላል (የእጅ አዙር መባሉም  ለዚሁ ነው)፡፤

ይህ ደግም እገታው የፖለቲካ ቁማር ሊሆን ይችላል የሚለውን የመንግስት ባለስልጣናትን ጥርጣሬ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ማድረግ እንደማይቻል ያመላክታል፡፡ይሁንና መንግስት እንደ መንግስት በመረጃ ላይ እንጂ በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ማድረግ አይጠበቅበትም ፡፡

የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ መረዳት የቻልኩት ስለ እገታው በቂ መረጃ እንደሌላቸው ነው፡፡ እገታው ይፋ ከሆነበት ቀን አንስቶ ህዝብ መንግስትን “ እጅ ከምን ?” በሚል ጥያቄ ጠዋት ማታ ያጣድፍ ጀመር፡፤  የመረጃ እጦቱ ግራ ያጋባቸው ባለስልጣናት እለታዊ ፋታ ለማግኘት ሲሉ 21 ታጋቾችን አስለቅቀናል በማለት ዋሹ !  ውሎ አድሮ ግን ነገሩ ሁሉ አለባብሰው ቢያርሱ . . . ሆነባቸው፡፡ መረጃ ጉልበት እንደሆነ ሁሉ ! የመረጃ እጥረትም አቅመ ቢስ ያደርጋልና አቅመ ቢስ አደረጋቸው.!

መረጃ አልባ ወንበር ለሃይለማሪያም ደሳለኝም አልበጀ

በተለይ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ከጭንቀታቸው መረዳት አይከብድም፡፡ ቢቸግራቸው “የታገቱት ልጆቻችን ይፈቱልን” የሚል መፈክር ባይዙም ፤ በባህርዳሩ ሰልፍ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ያሳዝናሉም! ያናድዳሉም፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውና ጭንቀታቸው ያሳዝናል! ድንዛዜያቸው ደግሞ ያናድዳል፡፡ መረጃ የሌለው ወንበር ለሃይለማሪያምም እንዳልበጀ ከትናንት ሊማሩ ይገባ ነበር፡፡ አልተማሩም! ወንበራቸውንም ሆነ የወከላቸውን ህዝብ በአግባቡ አላስከበሩም፡፡

በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ አንዳዶቹ የበለጠ እኩል ናቸው

ከብልጽግና ፓርቲ አባላት ውስጥ የበለጠ እኩል የሆኑት የጆርጅ ኦርዌል “አንዳንዶች” በአማራው ክልል ባለስልጣናት ላይ ጥላቸውን ያጠሉባቸው ይመስላል፡፡

በዚህ ጉዳይ ከታጋች ወላጆች ባላነሰ እንቅልፍ አጥተው የሰነበቱት አቶ ንጉሱ ይመስሉኛል ። የመንግስት አፍ መሆን ከባድ ሃላፊነት ነው፡፡ የመንግስት አፍ ሆነህ መልካም ሥራውን ስታበስር የሚመሰገነው መንግስት ነው፡፡በዛው ሃላፊነትህ የመንግስት ውሸት ስታስተላልፍ ግን የምት ሰደበው አንተ ነህ፡፡ በአቶ ንጉሱ ላይ ሰሞኑን የደረሰውም ይሄው ነው፡፡ 21 ታጋቾችን አስፈታን ብለው ሲናገሩ እሰይ አበጀህ የተባለው መንግስት ነው፡፡ መግለጫው ውሸት ሆኖ ሲገኝ ግን ቀጣፊ የተባሉት ተናጋሪው ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ አቶ ንጉሱ ሰሞኑን ከሰጡት አወዛጋቢ መግለጫ የተረዳሁት ነገር “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም!” እንዲሉ ለ27 አመታት ያሰለቸን የወያኔ _ ኢህአዴግ መንግስታዊ ውሸት በብልጽግና ዘመንም እንደቀጠለ መሆኑን ነው፡፡ ውሸት ከህዝብ ልብ ያራርቃል፡፡ ህዝብ መንግስትን ለማመን እየተቸገረ ነው፡፡

ወደ እገታው ስንመለስ፤፟ እገታው ገዥውን ፓርቲ ከህዝብ ለማጣላት ታስቦ የተፈጸመ ፖለቲካዊ ደባ ከሆነ በከፊልም ቢሆን አላማው እየተሳካ ነው ማለት ይቻላል ፡፡ ይሁንና ለስኬቱ ዋና ምክንያት አጋቾቹ ሳይሆኑ መንግስት እራሱ ነው፡፡ እንዴት? ማለት ጥሩ!

ጉዳዩ በተድበሰበሰ መጠን ጥያቄው እየጠነከረ ፤ ውጥረቱም እየከረረ መጣ፡፡ ባለስልጣናቱ  ደግሞ ውጥረቱን የሚያረግብ በቂ መልስ ወይም መረጃ አልነበራቸውም፡፤ በሳቢያውም የመረጃ እጦታቸውን በውሸት ለመሸፈን መሞከራቸው ህዝብን አሳዘነ፡፡

ለመንግስትም ሆነ ለታጋቾችና ቤተሰባቸው የሚጠቅመው እውነቱን አውቆ መፍትሄውን በጋራ መሻት ነው፡፤ ለውጡን የሚደግፈው ህዝብ ይህን መሰል ሽብርና ትርምስ ለምንና በማን ሊፈጸም እንደሚችል በቂ ግንዛቤ አለው፡፡ ለዚህም ነው የጉዳዩ ይፋ መሆን ሊያሳስባቸው የሚገባው ሽብርተኞችን ሆኖ ሳለ መንግስት ጉዳዩን ለማድበስበስ መሞከሩ ግራ የሚያጋባው፡፤ መንግስት አንዳንዴ ህዝብን ለማረጋጋት ሲል ይፋ የማያደርጋቸው ነገሮች ቢኖሩም መዋሸትን ግን አይጨምርም፡፡

የሚፈለጉ መረጃዎች . . .

እገታው መቼና የት ተፈጸመ፡? አጋቾቹ እነማን ናቸው? ታጋቾቹስ ? የትና በምን ሁኔታ ይገኛሉ ? የአጋቾች ጥያቄ ምንድነው? የሚሉት ተጨባጭ የሆነ መልስ የሚፈልጉ ዋና ዋና የመረጃ መሰብሰቢያ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ወደ መፍትሄ የሚደረገው ጉዞ የሚታቀደውም ከነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ በመነሳት ነው፡፡

የመንግስት ሃላፊነትም ይኽው ነው!  ትክክለኛ መረጃ መሰብሰብ! ከመረጃው በመነሳት ! የህዝብን ደህንነትና የሃገር ህልውናን ማስጠበቅን አላማው ያደረገ መፍትሄ መሻት!

አበቃሁ!

ቸሩ እግዚአብሄር ታጋቾቹን በሰላም ከቤተሰባቸው ጋር ይቀላቅላቸው!

Filed in: Amharic