>

"ችግሩን በደረት በኩል መግጠም!!!" (ዳንኤል ክብረት)

“ችግሩን በደረት በኩል መግጠም!!!”

 ዳንኤል ክብረት
*  “የሚያዋጣው ችግሩን በደረት በኩል መጋፈጥ ነው፡፡ የሚከፈለውን መሥዋዕትነት ከፍሎ የሰይጣን ክንፉን መንቀል ይገባል፡፡ ማስታመም የተሳሳተ ወንድምን እንጂ የተሳሳተ መንገድን አያስተካክልም!!!

ራሱን ‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት› ብሎ የሚጠራው ቡድን ዓላማው ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማው ደግሞ አራት አካላትን ይጠቀማል፡፡ ክልላዊ መዋቅሮችን፣ ፖለቲካዊ ኃይላትን፣ ቤተ ክህነታዊ ኃይላትንና ባለ ሀብቶችን፡፡
መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት› ዓላማ ሦስት ናቸው፡፡
“1. የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያ መነጠል
2. የብሔረሰብ ቤተ ክህነቶችን በሌሎች አካባቢዎች በማስፋፋት ኩላዊቷን ቤተ ክርስቲያን ብሔረሰባዊት አድርጎ መበታተን
3. በእነዚህ በሁለቱ በመጠቀም ጥንታዊቷን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ክፍልፋይ (Denominations) አውርዶ ማጥፋት፡፡
ተልዕኮው ዛሬ የሚያቀነቅኑት ሰዎች አይደለም፡፡ ሰዎቹ የቫይረሱ መነሻዎች ሳይሆኑ ተሸካሚዎች ናቸው፡፡ እነርሱም የመጀመሪያዎቹ አይደሉም፤ የመጨረሻዎቹም አይሆኑም፡፡ የኢትዮጵያን ዓምዶች ማፍረስ የሚፈልጉ አካላት ከውጭና ከውስጥ ሲሸርቡት የኖሩት ሤራ ተከታይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የጥይቱ ዒላማ የሆነችው የኢትዮጵያ አንድነት ታሪካዊና ትውፊታዊ ዓምድ ስለሆነች ነው፡፡
ችግሩ እዚህ ደረጃ መድረስ አስተዋጽዖ ያደረጉ ነገሮች አሉ፡፡
1. የቤተ ክህነት የማስፈጻምና የተሰሚነት ዐቅም እየተዳከመ መምጣት
2. ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲካ እየጦዘ መምጣት
3. ሳይፈቱ የተንከባለሉ ሐዋርያዊ ጥያቄዎች
መፍትሔዎቹ
1. የቤተ ክህነቱን ቁመና ለዘመኑ ጥያቄ መልስ በሚሰጥ ሁኔታ ማስተካከል
2. ለኦሮሞ ኦርቶዶክስ ሕዝብ መንፈሳዊ ጥያቄ ቤተ ክርስቲያናዊ ምላሽ መስጠትና ያንንም በተግባር ማሳየት
3. ቅዱስ ሲኖዶስ ባለው ሥልጣን ችግር ፈጣሪዎችን ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ካህናትና ዲያቆናት በይፋ መክሮ፣ ገሥጾ፤ ካልተመለሱ አውግዞ መለየት፤
4. ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ከሊቃውንት፣ ከምእመናንና ከወጣቶችና የተውጣጣ ኮሚቴ ማቋቋም፤ ኮሚቴውም ችግሩን እያጠና አስፈላጊውን ሁሉ የትምህርት፣ የተቋም፣ የሚዲያ፣ የሕግ፣ የሰው ኃይልና ሌሎች ተግባራትን ነገር እንዲያከናዉን ሥልጣንና ኃላፊነት በሕግ መስጠት
5. የቤተ ክርስቲያንንና የቤተ ክህነትን ስምና መብት ለማስከበር በሕግ ክስ መመሥረት
6. ፌዴራላዊና ክልላዊ አካላት በቤተ ክርስቲያን ቦታ ላይ ‹የኦሮምያን ቤተ ክህነት› እየተኩ የሚሠሩትን ሥራ እንዲያቆሙ በአደባባይ መጠየቅ፤ ካልሆነ በአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በኩል ድምፅን ማሰማት
7. በአዲስ አበባ ከተማ ከሁሉም የሀገሪቱ ወረዳዎች የሚሳተፉበት የምእመናን ጉባኤ በማድረግ በችግሩ ዙሪያ መነጋገርና አቋም መያዝ፡፡
“የሚያዋጣው ችግሩን በደረት በኩል መጋፈጥ ነው፡፡ የሚከፈለውን መሥዋዕትነት ከፍሎ የሰይጣን ክንፉን መንቀል ይገባል፡፡ ማስታመም የተሳሳተ ወንድምን እንጂ የተሳሳተ መንገድን አያስተካክልም፡፡
“ነገሩን በማለቃቀስ አንፈታውም፡፡ የተጠና፣ ቀኖናዊነትን መሠረት ያደረገ፣ ሕዝብን ከችግር ፈጣሪዎች የለየ፤ ከስሜት የወጣ፣ በዘላቂ መፍትሔ ላይ ያተኮረ፤ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያስፈልገናል፡፡ ጉዳዩ የዚህና የዚያ ሕዝብ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህች ቤተ ክርስቲያን እንደ ጧፍ በርተው፣ እንደ ዕጣን ነድደው፣ ቤተ ክርስቲያንንም አጽንተው ያለፉት ከሁሉም የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የመጡ ቅዱሳን ናቸው፡፡ የሚፋረደውም የሁሉም ዐጽም ነው፡፡ የችግሩ ተጠቂዎች ሁላችንም፤ መፍትሔዎችም ሁላችንም ነን፡፡
Filed in: Amharic