>
1:00 pm - Thursday December 8, 2022

የጠቅላይ ሚንስትሩ የ«ሪፎርም» አማካሪው ጄኔራል አቶ አባዱላ ገመዳ!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የጠቅላይ ሚንስትሩ የ«ሪፎርም» አማካሪው ጄኔራል አቶ አባዱላ ገመዳ!!!

አቻምየለህ ታምሩ

* ለኦህዴድም ሆነ ለኦሮሞ ህዝብ የሚቀርበው ኦነግ ሳይሆን ህወሀት ነው…!!!

አባዱላ
የአባዱላ ነገር እጅግ ይገርማል፤ እውነተኛ ስሙ ወልደ ጊዮርጊስ ገመዳ ነው፤ ወልደ ጊዮርጊስ የክርስትና ስሙ ነው፡፡ እናቱ የአርሲ አማራ ሲኾኑ አባቱ ደግሞ ከራስ ጎበና ልጅ ከደጃዝማች ወዳጆ ጎበና ጋር አርሲ የዘመቱ የሸዋ ኦሮሞ ባላባት የልጅ ልጅ ናቸው። ወልደ ጊዮርጊስ ገመዳ በዘመነ ደርግ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ወደ ሰሜን ግንባር የሀገር መከላከያ አባል በመኾን ዘምቶ ነበር። ግና ብዙም ሳይሳካለት በሻቢያ ተማረከ። ሻቢያ ከማረካቸው ሌሎች የኢትዮጵያ የሠራዊት አባላት ጋር ኾኖ ለዓመታት የሻቢያ ምሽግ ቆፋሪ ኾኖ ቆይቷል። ኋላ የኢ.ሕ.ዴ.ኑ ያሬድ ጥበቡ ደርሶለት እንጀራ አወጣለት።
የኢ.ሕ.ዴኑ መሪ ያሬድ ጥብቡ አባዱላን፣ ባጫ ደበሌን እና ሌሎች የሻቢያ ምርኮኞችን ከምሽግ ቆፋሪነት አውጥቶ ወደ ኢ.ሕ.ዴ.ን ፋኖነት እንዲዛወሩ በማድረጉ ሕይወታቸውን እስከመጨረሻው ድረስ ለወጠው። ወያኔ ሻቢያን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ ክንፈና መለስ ደራ ላይ ኦ.ሕ.ዴ.ድን ሲመሰርቱ እናቱ ያወጡለትን ስም ቀይረው «አባዱላ» የሚል የዘመቻ መሪነት ስም አወጡለትና የፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅት የጦር መሪ አደረጉት። ሕገ መንግሥት ተብዬው ከፀደቀ በኋላ ደግሞ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፕሬዚደንት ሲኾኑ  ብርጋዴር ጄነራልነት ታደለውና የወያኔ መከላከያ ሚንስትር ኾነ።
ወልደ ጊዮርጊስ ወደ አባዱላነት ስሙን የቀየረው «ስም ትለውጣለች» እየተባለች ቁም ስቅሏን ስታይ በከረመችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባወጣችለት ስም እንዳይጠራ ነው። እውነቱ ግን ስሙ የተቀየረው ከግዕዝ ወደ ኦሮሚኛ እንጂ ከኦሮሚኛ ወደ ግዕዝ አልነበረም። አባዱላ ክርስትና የተነሳው በተወለደ በ40 ቀኑ ነው፤ አርባ ቀን ሳይሞላው በፊት ስም አልነበረውም፤ በአርባ ቀኑ ወልደ ጊዮርጊስ ተባለ። ከዚያ መለስና ክንፈ አባዱላ አሉትና «አማራ ስሜን እንድቀይር አስገድዶኝ…» እንዲል እያደረጉ ፖለቲካ ሠሩበት። እውነቱ ግን ስሙን እንዲቀይር ያስገደዱት መለስና ክንፈ እንጂ የመጀመሪያና የአርባ ቀን ስሙማ ወልደ ጊዮርጊስ ነበር። ባጭሩ የአባዱላ ስም ተቀየረ ከተባለ ከግዕዝ ወደ ኦሮሚኛ እንጂ ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ወይንም ግዕዝ የቀየረው ስም የለውም።
አባዱላ ስሙን ቀይሮ ማተቡን ከበጠሰ በኋላ የታመነ የወያኔ ሎሌ ኾነና «ለኦሮሞ ሕዝብ የሚቀርበው ኦ.ነ.ግ ሳይኾን ሕ.ወ.ሓ.ት ነው» እስከ ማለት ደረሰ። በወያኔ ተዘጋጅቶ ዶ/ር ነጋሶ እንዲጭኑለት የተደረገውን የ‹ብርጋዴር ጄነራል›ነት ማዕረግም በመለስ ቀጭን ትእዛዝ ተሻረና ማዕረጉ ተቆርጦ፣ ወደ ሲቪልነት ተቀይሮ፣ አቶ ተባለ። አባዱላ የ‹ ብርጋዴር ጄነራል› ማዕረግ የጫነው በወቅቱ ፕሬዚደንት በነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ሲኾን፣ ጄነራልነቱን ትቶ አቶ የተባለውም በዚሁ በዶ/ር ነጋሶ ፕሬዚደንትነት ዘመን ነው። ይሁን እንጂ አባዱላ ከጄነራል’ነት ወደ አቶ’ነት የወረደው የሕገ መንግሥት ተብዬው ፕሮቶኮል በሚጠይቀው መሠረት በፕሬዚደንቱ ትእዛዝ ሳይኾን በመለስ ዜናዊ ትእዛዝ ነበር። በዚህ የተቆጡት ዶ/ር ነጋሶ «ሕገ መንግሥቱ በሰጠኝ ሥልጣን እኔ የሰጠሁትን የብርጋዴር ጄነራልነት ማዕረግ ማንሳት ካለብኝ ማንሳት ያለብኝ እኔ በመኾኔና አባዱላ ወደ አቶነት እንዲወርዱ የተደረገው በኔ የፕሬዚደንትነት ዘመን በመኾኑ፤ እኔ እስካላወረድኳቸው ድረስ ለኔ አሁንም ጄነራል ናቸው፤ ሳገኛቸውም አቶ አባዱላ ሳይኾን ጄነራል አባዱላ ነው የምላቸው» ሲሉ በዳንዲ የነጋሶ መንገድ ነግረውናል።
አባዱላ አቶ እንደኾነ በመለስ ትእዛዝ ኦሮሚያ የሚባለው ክልል ፕሬዚደንት ኾነ። ቆይቶ ደግሞ አፈ-ጉባዔ ኾነ። የአማራና የኦሮሞ ወጣቶች በሀገር ውስጥና በውጪ ተናበው ባንድነት ወያኔን መፋለም ሲጀምሩ «የምኒልክን ባንዲራ ይዘው ከወጡ ነፍጠኞች ጋር ባንድነት የሚቆሙ ሰዎች ለኦሮሞ ሕዝብ ሊቆረቆሩ አይችሉም» በማለት የኦሮሞ ወጣቶች ከአማራ ልጆች ጋር ለተቃውሞ መውጣታቸውን በወያኔ ቴሌቪዥን ቀርቦ አወገዘ። ልብ በሉ! አባዱላ «የምኒልክን ባንዲራ» እያለ የሚያብጠለጥላት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እርሱ ራሱ ከሁሉ በፊት «ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ፤ ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ» እያለ በመዘመር ሕይወቱን ሊገብርላት የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል በመኾን ወደ ሰሜን ግንባር ሲዘምት ያውለበልባት የነበረችውንና ደርግ ከወደቀ በኋላም የወያኔ ጄነራል ኾኖ ሻቢያና ወያኔ ጥጋባቸውን መቻል አቅቷቸው በበላይነትና በበታችነት ስሜት ተወጥረው በተበጣበጡ ጊዜ በጄነራልነት ማዕረግ የጦር መሪ ተብሎ ባድመ ይዟት የዘመተውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ነው።
«የምኒልክን ባንዲራ ይዘው ከወጡ ጋር ባንድነት የሚቆሙ ኦሮሞዎች ለኦሮሞ ሕዝብ ሊቆረቆሩ አይችሉም» በሚለው የአባዱላ የወያኔ ዘመን ንግግር መስፈርት መሠረት አባዱላ ለኦሮሞ ሕዝብ አይቆረቆሩም ካላቸው ሰዎች በፊት ለኦሮሞ ሕዝብ ከማይቆረቆሩት ቀዳሚው እርሱ ራሱ ነው። ምክንያቱም «ለኦሮሞ ሕዝብ ሊቆረቆሩ አይችሉም» ካላቸው የኦሮሞ ወጣቶች በፊት እርሱ ራሱ ወልደ ጊዮርጊስ ሳለ መጀመሪያ በቀይ ኮከብ ዘመቻ በደርግ ዘመን፣ በመቀጠል አባዱላ ኾኖ በወያኔ ዘመን በባድመ ጦርነት ወቅት «የምኒልክ ባንዲራ» ያላትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ ወደ ሰሜን የዘመተና ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላም «የምኒልክ ባንዲራ» ያላትን ባድመ ላይ የሰቀላት እርሱ ራሱ ነበርና ነው። ስለዚህ ራሱ ባወጣው መመዘኛ አባዱላ ለኦሮሞ ሕዝብ ከማይቆረቆሩት መካከል ቀዳሚው ነው ማለት ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ «ድርጅቴና ሕዝቤ ክብሩ ተነክቷል» ብሎ የአፈ-ጉባኤነት ሥልጣኔን ለቅቄያለሁ አለ። ብዙም ሳይቆይ በተፋበት ወንበር ላይ ተመልሶ ተቀመጠና እንደገና አፈ-ጉባኤ ኾነ። ክብሩ ተነክቷል ባለው ሕዝብ ላይ ወያኔ የጭፍጨፋ አዋጅ ሲያወጣ በአፈ-ጉባኤነት ተሰይሞ ያስፈጽም የነበረው እርሱ ራሱ ነበር። በተፋበት ወንበር ላይ እንደገና ከተቀመጠ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ከአፈ-ጉባኤነቱ ተነስቶ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የዐቢይ አሕመድ የደኅንነት አማካሪ ኾኖ የUNDP ደሞዝ ተከፋይ ኾነ። ልብ በሉ! UNDP ረብጣ ዶላር ደሞዝ እየከፈለ የኢትዮጵያን አገዛዝ  እንዲያማክሩና ለሪፎርም ተብዬው አጋዥ እንዲኾኑ ተብሎ እንዲቀጠሩ የታሰቡት ሰዎች የእውቀትና የሞያ ሰዎች ወይም ቴክኖክራቶችን ነበር። ዐቢይ አሕመድን ግን ሌጣውን አባዱላ ገመዳን የሪፎርም ተብዬው የደኅንነት አማካሪ አድርጎ በመሾም ከUNDP ረብጣ ዶላር የወር ደሞዝ እንዲከፈለው አድርጎታል።
በሌላ አነጋገር አባዱላ የUNDP ረብጣ ዶላር የወር ደሞዝ የሚከፈለው ከውጪ እንደገቡት የምርጫ ቦርድ ሰራተኞች እንደነ ብርቱካን ሚደቅሳና ውብሸት አየለ፣ እንደ የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ሌንጮ ባቲ ወዘተርፈ ሪፎርም ተብዬውን በ«እውቀት» እና በ«ክህሎት» እንዲያግዝ ነው። ሀገራችን የእውር ድንብሯን እየሄደች ወደ ገደል እየገባች ያለችው በሌጣው አባዱላ ጭንቅላት ታስቦ ለዐቢይ በሚሰጠው ምክር (the blind leading the blind) እየተመራን ስለኾነ ነው።
አባዱላ በዚህ ባዲሱ ሥልጣኑ ላይ ተቀምጦ የአንድ ወር «ደሞዝ» እንኳ ሳይበላ በሰበር ዜና ጡረታ መውጣቱ ተነገረለት። ይኹን እንጂ እስካሁን ድረስ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት አማካሪ ተብሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ በተሰጠው ቢሮ ከወር ሁለት ቀን እየገባ እየወጣ የሪፎርሙ አማካሪ ተብሎ የUNDP ረብጣ ዶላር የወር ደሞዝ ይከፈለዋል። አባዱላ በሰበር ዜና ጡረታ ወጣ ከተባለ ከሁለት ወር በኋላ በጓሮ በር ዞሮ በዐቢይ አሕመድ ደብዳቤ በሹመት ላይ ሹመት በመደረብ «የጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ መልዕክተኛ» ኾኖ በመሾም እንደገና ተከሰተ። በዚህ ሹመቱም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ልዩ መልዕክት በመያዝ ወደ ደቡብ ኮርያ ዋና ከተማ ሲዖል አቅንቶ ነበር። ከሲዖል እንደተመለሰ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ኾኖ ሦስተኛ ሹመቱን ደረበ። ከሰሞኑ ደግሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢነቱ ላይ አራተኛ ሹመቱ የኾነውን የደቡብ የክልል ዞኖች የሚያነሱትን የክልልነት ጥያቄ እንዲከታተል የተቋቋመውን የዐቢይ አሕመድ ኮሚቴ እንዲመራ ተመርጧል። በዚህ በአዲሱ ሹመት መሠረት አባዱላ ገመዳ የደቡብ ክልል ተብዬው ቀጣዩ የነፍስ አባት ኾኗል። ይገርማል! እንደ አባዱላ ሹመትን ቁም ስቅሉን ያሳየ ሰው ይኖር ይኾን?!
ባጭሩ ፋሽስት ወያኔ በፈጸመው ግፍና ወንጀል እንዲሁም ዝርፊያ ሁሉ አባዱላ እጁ አለበት። ሆኖም ግን የአባዱላ ጌቶች ዋነኞቹ ወንጀለኞች ተገፍተው መቀሌ እንዲመሽጉ ሲገደዱናና አንዳንዶቹም ለፈጸሙት ወንጀል መያዣ ሲወጣባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የቆመው ሥርዓት የአፓርታይድ አገዛዝ በመሆኑ ግን  የወንጀልና የዘረፋ ተባባሪያቸው እንዲሁም ዋና ተዋናዩ  አባዱላ  የጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት ሪፎርም አማካሪ ሆኖ በወያኔ ዘመን ከሚያገኘው የታወቀ የዘር ደመወዝ በብዙ መቶ እጥፍ የሚልቅ ረብጣ ዶላር ከUNDP እየዛቀ  ለኦሕዴድና ለኦሮሞ ሕዝብ ከኦነግ ይልቅ ሕወሓቶች  ይቀርባሉ  ካላቸው የወንጀል ግብረ አባሮቹ ተለይቶ ቤተ መንግሥት ውስጥ ቢሮ ተከፍቶለት ሽር ብትን እያለ ይገኛል። በረከት ሰምዖንን፣ አባይ ፀሐዬንና ስዩም መስፍን ወንጀለኛና ዘራፊ  ሆነው አባዱላ ገመዳን ግን  የለውጥ አማካሪና ነጻ ሰው ያደረገው ኢትዮጵያ ውስጥ የቆመው በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የአፓርታይድ አገዛዝ ወገን በመሆኑ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ በሕግና በእውነተኛ ዳኛ  ፊት አባዱላ ከሕዝብ ጠላቶቹ ከነበረከት ሰምዖን፣ ከነአባይ ፀሐዬና ከነስዩም መስፍን ያልተናነሰ የሕዝብ ጠላት፣ ወንጀለኛና ዘራፊ፤ አልፎም ዛሬ  ወንጀለኛ ተብለው ከታሰሩ ሰዎች  ሁሉ የከፋ ጨካኝ አውሬ ነው።
Filed in: Amharic