>

የአቶ መለስ ዜናዊ ልጅ ሰማሃል በትግርኛ ያደረገችውን ዲስኩር ሰማን!... (አርአያ ተስፋ ማርያም)

ሰማሃል “አለች!!!” እኛም ሰማን !!!

 

አርአያ ተስፋ ማርያም
 
የአቶ መለስ ዜናዊ ልጅ ሰማሃል መለስ በትግርኛ ያደረገችውን ዲስኩር እየገረመኝ፣ ንቀትና ትእቢት የተሞላበት ንግግሯ እያቅለሸለሸኝ ሰማሁት። “ጋዜጠኛ” ሳይሆን አብሮ የሚሳደብ “ካድሬ” ነበር “ጠያቂ” ተብዬው። በጥቅሉ የጨመቅኩት ንግግሯ እንዲህ ይላል።
“የኢህአዴግ መንገድ ተጨናግፏል። የመለስን ፎቶ ሊቀዱት ይችላሉ። ግን መለስ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአለም የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ አለም እየተመራበት ነው። ሀ/ማርያም ደሳለኝ ህወሀት አላሰራ ብሎኝ ነበር የሚለው ድሮም ከመለስ ጋር ፎቶ እየተነሳ መለስን እየዋሸ ልቡና ድርጊቱ ግን ሊዮ ሊብራሊዝም ነበር።
 የትግራይ ህዝብ የአስተዳደር ችግር ቢኖርበትም መሪዎቹን አንድ ሆኖ ይጠብቃል። የሜቴክ ሰዎች የታሰሩት ልማት በመስራታቸው ነው። ሙስና ቢኖርም የመለስ ፖሊሲ ሚሊዮነሮች ፈጥሯል፣ ገበሬው ሳይቀር ሚሊየነር ሆኗል።
ዶ/ር አብይ የአሜሪካ ፓፔት፣ ኢሳያስ የአረብ ተላላኪ ነው። ዶ/ር አብይ የተሰጠውን የኖቤል ሽልማት ውድቅ እንዲደረግ ጠንክረን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ አለብን። መለስ ያቀመጠው የብሄር/ብሄረሰቦች መብት ጌድኦ ብትሄድ ተረጋግጧል። አሁን አዲስ አበባ ሳይቀር የማንነት (ብሄር) ጥያቄ አንስቷል። ይህ የመለስ ውጤት ነው። ሰው መብቱን አውቋል።
ጥላሁን ገሰሰ ኦሮሞነቱን ሰርዞ በአማርኛ ይዘፍን ነበር። አማርኛ የሚዘፍን የክልሉ ተወላጅ ይህን ሰርዞ ኦሮሞ ወይም ሌላ ሲሆን አልታየም። ከንጉሱ ጀምሮ የነበሩ አውቶብሶች በሜቴክ ተቀይረዋል።
 በ97. ምርጫ ህገ መንግስቱን አያስፈልግም ብሎ ለመናድ የተነሳው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አሁን ደግሞ ከአንቀፅ 39 በቀር ህገ መንግስቱን እንቀበላለን አለ። ዶ/ር ብርሃኑ ኮንደሚኒየም አያስፈልግም እያለ የመለስን ተግባር ያጣጥል ነበር” ….
 በመጨረሻም “አዲስ አበባ እንድንለቅ በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግስት ቢፈልግም መስዋእት እንሆናለን ብለን ቁጭ ብለናል። መኪና እራሴ ነው የማሽከረክረው። የአዲስ አበባ ነዋሪ አይዞሽ፣ የጀግና ልጅ ይለኛል” ብላለች።
 ይህን ሁሉ ስትቀባጥር አንድም ማስረጃ አላቀረበችም። መለስ በስልጣን እያሉ በገመድ ታንቀው፣ በስለት ታርደው፣ ልጆቻቸው ለችግር የተዳረጉ ባለስልጣናት ትዝ አሉኝ! 
ሀገሪቷን በአጥቷ ካስቀሩ ሞሳኞች በቁጥር አንድ ተርታ የምትቀመጠው የእናትሽ የወይዘሮ አዜብ ሙስና ጉድስ ምነው ትዝ አላለሽ! 
Filed in: Amharic