>

ትልቅ ትምህርትን ያስተማረኝ…. ታላቁ የሕይወቴ ሿሿ… ! ! ! (አሰፋ ሃይሉ)

ትልቅ ትምህርትን ያስተማረኝ…. ታላቁ የሕይወቴ ሿሿ…!!!

አሰፋ ሃይሉ
 …. የሚሆነውን ከመስማትና ከመከታተል ሳልቦዝን ከፍርድና ከፍረጃ ርቄ ስለዚህ ሰው ብዙ ነገሮችን ለመረዳት ጣርኩኝ፡፡ ብዙ ነገሮችን አውጠነጠንኩ፡፡ ብዙ ነገሮችንም ለማጤን ሞከርኩ፡፡ እያንዳንዱ ያሳለፍነው ነገር ባለ ብዙ ምዕራፍ መፅሐፍ የሚወጣው የማስመሰልና የማምታታት ሿሿ ታሪክ ነው…!
ስህተቴን ለማመን ወደ ኋላ አልልም፡፡ አዎ ድብን አድርጌ ተሣስቼያለሁ፡፡ በጣም ተሳስቼ ነበር፡፡ ሕልሜ ታላቅ ቅዠት፣ የጣልኩት ተስፋም ታላቅ ስህተት ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ስም እየማለ ይገዘት በነበረ አንድ ቀጣፊ ካድሬ ላይ እምነቴን ጥዬ… በታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው ሿሿ መሠራቴን አምናለሁ፡፡ ሿሿ ተሠርቼያለሁ በእውነቱ፡፡
በእርግጥ ስህተቴን ካወቅኩ ጥቂት ቀደም ብያለሁ፡፡ የቡራዩን ጭፍጨፋ ለማውገዝ ከወጣነው ሰላማዊ ሰልፈኞች መካከል አምባሳደር ሲኒማ ፊት ለፊት በዓይናችን ፊት 5 ንፁሃን ያዲሳባ ልጆችን በስናይፐር አስቀንድቦ ያስገደለ ዕለት፡፡ የዚያችው ዕለት ሰው ለሥልጣንና እና ለጥላቻው ማስታገሻ እስከምን ክፋት ድረስ ሊጓዝ እንደሚችል ሁሉ ነበረ ወለል ብሎ የተገለጠልኝ፡፡ በማግስቱም ‹‹ጠ/ሚ አብይ ሆይ፣ ከአዲሳባ ልጆች ላይ እጅህን አንሣ!›› የሚል ፅሑፍ በፌስቡክ ገፄ ላይ ለጠፍኩ፡፡ ከብዙ ካድሬዎች የስድብና የማስፈራሪያ ናዳ አስተናገድኩ፡፡ በዚያ ፅሑፍ የተነሣ በግልም ሆነ በሥራ ሕይወቴ ብዙ ጦሶችን ተቀብያለሁ፡፡ በደስታ ነው፡፡ ነገር ግን ያንጊዜም ቢሆን ድርጊቱን ከማውገዝና በብርቱ ከመምከር ባለፈ የሿሿ ሠሪውን ሰብዕና እኩይ ነው ብዬ ጨክኜ ለመደምደም አልቻልኩም ነበር፡፡
ከዚያም በኋላ በዚሁ ሰው እዝ ሥር ለቁጥር የሚያስቸግሩ ሸፍጦችና ወንጀሎች ባደባባይ ሲፈፀሙ ተመለከትን፡፡ ብዙ ሰዎች ያለ ጠባቂ፣ ያለ ተከላካይ ታረዱ፣ ሞቱ፣ ተጨፈጨፉ፡፡ በዚህ ሰው በአንዲት የከፋች የመርዶ ቀን የተፈፀመው እኩይ ሤራ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ በክፋቱ ወደር አይገኝለትም፡፡ የሚሊቴሪ ፋቲግ ለብሶ፣ የአማራ ቴሌቪዥን የሚል ሎጎ ያለው ማይክሮፎን ፊት ለፊቱ አስቀምጦ፣ በቴሌቪዥን ገጭ ብሎ፣ የጄ/ል አሳምነው ፅጌን (እና የሌሎቹን) ግድያ በለመደ ምላሱ ሲያቀነባብር፣ ፍጥጥ ብሎ በዚያን ዕለት የባህርዳሩን የሴራ ኦፕሬሽን በቤቱ ቁጭ ብሎ እየመራ የነበረውን ጄ/ል ሳዕረ መኮንንን.. ጄ/ል አሳምነው ፅጌ ከባህርዳር ሆኖ አስገደለው ሲለን፣ እንዲያ በቴሌቪዥን ቀርቦ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሠራውን አሳዛኝም አሳፋሪም ድራማ ስመለከት የዚህ ሰው ከመጠን ያለፈ ስግብግብነትና ይሉኝታ-ቢስነት ራቁቱን እንደቀረ ታየኝ፡፡ ባየሁትና በተመለከትኩት ነገር ህሊናዬ እጅጉን ተሳቀቀ፡፡
ከዚያ በኋላ ግን የሚሆነውን ከመስማትና ከመከታተል ሳልቦዝን ከፍርድና ከፍረጃ ርቄ ስለዚህ ሰው ብዙ ነገሮችን ለመረዳት ጣርኩኝ፡፡ ብዙ ነገሮችን አውጠነጠንኩ፡፡ ብዙ ነገሮችንም ለማጤን ሞከርኩ፡፡ እያንዳንዱ ያሳለፍነው ነገር ባለ ብዙ ምዕራፍ መፅሐፍ የሚወጣው የማስመሰልና የማምታታት ሿሿ ታሪክ ነው፡፡ ወደር የማይገኝለት ሿሿ፡፡ እንዲያ ከመነሻው ልቤ ከብዙ ሚሊዮኖች ልቦች ጋር አብሮ ሰፍ ያለውን አሰብኩት፡፡ ክፋቱን፣ ተንኮሉን፣ ትያትሩንና የሁሉም የመጨረሻ ግብ ወደ ምን ለማምራት እንደሆነ አለምኩት፡፡ እና መንፈሴን ደከመው፡፡ ለበርካታ ተከታታይ አሰርት ዓመታት አንድዬ ሁሉ ሞልቶ የተረፈው ለኢትዮጵያችን ምነው ታላቅ ቀጣፊ እንጂ ታላቅ መሪ አልሰጣት አለ? ብዬ አምላክን አማረርኩ፡፡
በሂስና ግለሂሴ ቀጥዬአለሁ፡፡ ሁሉም የሃሳብ መንገዶች የሚያመለክቱኝ ወደዚያው ወደ አንድ አቅጣጫ ነው፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ ስም ሲጠራልኝ፣ ባንዲራችን በአደባባይ በነፃነት ሲውለበለብልኝ፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር እየተባለ ሲደሰኮርልኝ፣ የእስራት የግርፋት የግድያ ዘመን አብቅቷል ሲባልልኝ፣ በንግግር ፀሐፊዎች የተከሸኑ ቃላት ሲሸከፍልኝ፣ ሀገር፣ ሀገር፣ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ የሚል ፕሮፓጋንዳው ቀንና ሌሊት ሲነዛልኝ፣ ያች ከብዙዎች ጋር ሀገርን የተራበች ነፍሴ ደስ ተሰኝታ፣ በሰውየው ላይ ተስፋ ሰንቄ፣ ደርሶ ሆይ ሆይ ሆይ… ብዬ የክፋት ዓላማቸውን ከማልጋራቸው እቡያን ጋር አብሬ ያጨበጨብኩት፣ የሰው ልጅ መድማት፣ መታረድ፣ መገደል፣ መታገት፣ የሰው ልጅ ለቅሶና መከራ ህሊናቸውን ከማይቆረቁራቸው በጎሳ ምሽጋቸው ከተሰደሩ ብዙዎች ጋር ያሽቃበጥኩት… ያ ሁሉ የባለፈው ጊዜያት የለውጥ ልፈፋዬ… በሕይወቴ ትልቅ ትምህርትን ያስተማረኝ…. ታላቁ የሕይወቴ ሿሿ ነበር፡፡
አዎን፡፡ ነጭ ስህተቴን አምኜ ተቀብያለሁ፡፡ ያጨበጨብነው ስህተት ነበር፡፡ የጮህነው በስህተት ነበር፡፡ የደገፍነው በስህተት ነበር፡፡ የተዘናጋነው በስህተት ነበር፡፡ የሆንነውን ሁሉ የሆንነው በስህተት ነበር፡፡ የራሴን ስህተት በአንደበቴ ተንፍሼያለሁ፡፡ ብልህ ሰው ከጅል ይማራልና ስህተቶቼ ሌሎች እንደኔው በስህተት ጎዳና ለተመላለሱ ብልሆች አስተውሎ መራመጃ ቢሆንልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ካልሆነም ሁሉም ሰው የየራሱ በጋ አለውና – ሁሉም ከራሱ ይማር፡፡
ይህ የግል እምነቴና አመለካከቴ ነው፡፡ ይህን አመለካከቴን የሚጋሩ ብዙ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል… ይህን የማይጋሩኝም ብዙዎች እንደሚኖሩ አልጠራጠርም፡፡ ትክክለኛ መሪ ላገኛችሁም – መልካም ለውጥ፡፡ መልካም ሐሴት ይሆንላችሁ ዘንድ እመኛኝላችኋለሁ፡፡ የለውጥ ተስፋ ታይቷችሁ ደስ ተሰኝታችሁ ሳለ – ለውጡ በአስመሳዮች እጅ እንደወደቀ (እንደ እኔ) ቁርጣችሁን ለተረዳችሁ ደግሞ – መልካም ትግል እመኝላችኋለሁ፡፡ በስህተታችንም ሆነ በትክክላችን ውስጥ ያለን ሁላችንም ግን – የምንከተለውን አስተውለን እንምረጥ፡፡ አስተውለን እንጓዝ፡፡ አስተውለን እናጨብጭብ፡፡
ሿሿ ይብቃ!

ትውልድ ይዳን!   

Filed in: Amharic