>

የሕይወት ዛፍ ገነት ኢትዮጵያ! ላይጥሉሽ ይታገሉሻል! ላይገድሉ ያቆስሉሻል!!! (ዳንኤል ቶማስ)

የሕይወት ዛፍ ገነት ኢትዮጵያ! ላይጥሉሽ ይታገሉሻል! ላይገድሉ ያቆስሉሻል!!!

ዳንኤል ቶማስ
ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እየተመራች ያለችው በኢትዮጵያውያን ባለስልጣናት እንዳልሆነ ብዙዎቻችን ዛሬ ድረስ የተረዳን አልመሰለኝም::ባለስልጣናቱ ሆነ ብለው በዚች አገር ላይ የሚያከናውኑት ዘርፈ ብዙ እኩይ ተግባራትም ተልዕኮ ሰጥተው በላኩዋቸውና ስልጣኑን ባስያዙዋቸው አካላት ፍላጎትና ትእዛዝ እየተፈጸመ ያለ መሆኑን ለመረዳት የተዘጋጀን አልመሰለኝም:: ለዚያም ነው ችግሮችን ሁሉ ከአገር ውስጥ የብሄር ፓለቲካ ፍትጊያ አንጻር ብቻ እየመዘንን በተለያዩ ጊዜያቶች በተለያዩ ግለሰብና ቡድኖች ላይ ጣታችን በመቀሰር ተወስነን የምንገኘው::ሌላው ቀርቶ አቤቱታችንን የምናቀርበው ለማን እንደሆነ እንኩዋ በቅጡ አልተረዳንም::
በዚህ ሁኔታችን እንዲህ እንድንሆንና እንዲህ እንድናስብ የሚፈልጉ ሃይላት ስኬታማ ሆነዋል:: እኛም የዋህነቱን አብዝተንላቸዋል::አንዳንዱ “አብይ አገር መምራት አልቻለም ህግ ማስከበር አቅቶታል አገር እየፈረሰ እያየ በቸልታ እያለፈ ነው” ይላል:: አገር ለማፍረስ ብሄራዊ አንድነትን ለመበጣጠስ ቃል ገብቶ እንደነገሰ ዘንግቶት!  አንዳንዱ ግጭት የሚያስነሱ ወንጀለኞችና ችግር ፈጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋል  አለባቸው” ይላል::
እንደ ተቀጣጣይ እሳት በሚቆጠረው አገሪቱ ላይ ተዘርግቶ በነበረው አደገኛ ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ላይ ቤንዚል ለማርከፍከፍ ተመርጠው መሾማቸውን ረስቶት! ሁሉም የተጣሉና የማይስማሙ መስለውነገር ግን ተናብበው እየሰሩ እንዳለ መገንዘብ ተስኖት! አገር የማፍረስ ተልዕክዋቸውን እየተወጡ እንዳሉ ዘንግቶት!
  አንዳንዱ ጃዋር ለፍርድ ይቅረብ ብሎ ተልዕኮ ሰጥተው ለላኩት ለእንግሊዝና ለአሜሪካ መንግስት አቤቱታውን ያቀርባል::”በዘር ማጥፋት ክሰሱልን” ብሎ በአደባባይ ይጮህል:: ጃዋርን አሜሪካ ውስጥም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲ አይ ኤ እንደሚጠብቀው መረጃ ስለሌለው::
 አንዳንዱ “ጃዋር በአሜሪካ መንግስት ታክስ በማጭበርበር ይፈለጋል ጉዱ ነው የታባቱ እንደሚገባ!” ብሎ ሃሴት ያደርጋል:: የአሜሪካን የታክስ አሰባሰብ ዘዴ ባለመረዳትና እንደ እኛ አገር በክላሰር ደበሎ ቀበሌኛ አሰራር አሜሪካ ውስጥ ያለ እየመሰለው::
  አንዳንዱ አብይ አህመድ ለፈጸመውና ወደ ፊትም ለሚፈጽመው ሴራ ሲባል የተሰጠውን የዓለም የሰላም ኖቬል ሽልማት መውሰዱን ከአገር ጋር አገንኝቶ ምንም ቢሆን ሽልማቱ ለኢትዮጵያ ክብር ነው ለአገራችን ጠቃሚ ነው ብሎ ይሞግታል:: የሰላም ኖቬል እንዲህ በቅጽበትና በተራ ተግባር እንደማይሰጥ ባለመገንዘብ::
  አንዳንዱ የኢትዮ ኤርትራ እርቅ ብቻውን ለዓለም የሰላም ኖቬል እንደሚያሳጭ ያምናል:: ስለ ሰላም ኖቬል ምንም አይነት ግንዛቤ ስለሌለው::
አንዳንዱ ለውጡ ለውጡ ይላል:: ስለ ለውጥና ስለ ነውጥ ትርጉዋሜ ባለመረዳት::  አንዳንዱ ኢትዮጵያ ሳተላይት አመጠቀች በሚል ዜና በደስታ ተውጦ ሲዘል ይታያል:: ምንም አይነት ሳተላይት ኢትዮጵያ እንዳላመጠቀች ለመረዳት ባለመቻል::
  አንዳንዱ ስለ ህዝቅኤል ጋቢሳ ሌላው ስለ በቀለ ገራባ ከፊሉ ስለ ፕሮፌሰር ፈይሳ ገሚሱ ስለ ቄስ በላይ ሌላው ስለ ሌላው ብሽሽቅ ንግግር እያነሳ ስለ ጅልነታቸው ይተነትናል::እነእርሱ ሆነ ብለው አስቂኝና አወዛጋቢ ንግግር በየተራ እየተናገሩ አጀንዳ በማቀበል ሌላውን ተልእኮዋቸውን በመፈጸም ላይ እንዳሉ ባለመገንዘብ::
አንዳንዱ አብይን አላሰራ ስላሉት ነው ውህደቱን ለማ ተቃወመው ገለመሌ እያለ ይደሰኩራል::ሁሉም ተሳማምተው ነገር ግን የተጣሉ መስለው በቅጡ ተናብበው እየሰሩ እንደሆነ መረዳት ተስኖት::
  አንዳንዱ ስለ ቤተክርስቲያን ቃጠሎ አንዳንዱ ስለ መስጅድ ቃጠሎ እያነሳ ይጥላል::  አንዳንዱ አብያተክርስቲያናት ሲቃጠሉና ሲውድሙ ጥቃቱ በኦርቶዶክስ ላይ ብቻ የተሰነዘረ እየመሰለው በተራ የቃላት ውግዘት ያልፈዋል::ሌላው መስጅድ ሲቃጠል ጥቃቱ በእስልምና ላይ ብቻ የተሰነዘረ እየመሰለው በተመሳሳይ ቃል እውግዞ ዝም ይላል::
 እንዲህና እንዲያ እያለ ዛሬ አንዱ ነገ ሌላው ሲቃጠል ሲያይ ያለፈው ቃጠሎ የመልስ ምት እየመሰለው “የታባቱ ይበለው” ይላል:: ያም ይሄም እሪሪሪ ይላል:: ጥርስ ይነካከሳል:: በቃጠሎ ብዛት ማን እየመራ እንዳለ በማሰብና በመቁጠር ማን ማን መሪ ማን ተመሪ እንደሆነ አስቦ ደርሶ የድል አድራጊነት ስሜት ሲሰማው ይታያል:: በስተመጨረሻ የአሸናፊውም የተሸናፊውም የሐይማኖት ተቁዋማት ሙሉ በሙሉ እንደሚወድሙ ለመገንዘብ ባለመቻል!
  አንዳንዱ “መንግስት የእኛ ሲቃጠል ዝም ብሎ የእነሱ ሲቃጠል መግለጫ ሰጠ” እያለ ነገሩን በመድልዖ የሚፈጸም አድርጎ ወስዶ  አጉረምርሞ ያልፋል:: ጥቃቱ በመላው ኢትዮጵያዊ ሐይማኖተኛ ላይ እየተሰነዘረ እንዳለ ባለመረዳት::  ጥፋትና ውድመቱ በአገር ደረጃ የመጣ እንጂ አንዱን አውድሞ አንዱን ብቻ በማስቀረት እፎይ ለማለት ሲባል የሚከናወን እንዳልሆነ ረስቶት!
  ይህ በራሱ በመላው ህዝብ ዘንድ ፈጥኖ መታወቅ ነበረበት::መጥፎ ዕድል ህኖ ግን በብዙዎች ዘንድ ሊታወቅ አልቻለም::  የምዕራባውያንን አጀንዳ አንግበው አገሪቱን እየገዙ ያሉት ባለስልጣናትም ይህ የምዕራባውያን ተልዕኮዋቸው እንዳይታወቅባቸው ሆነ ብለው የሚፈጥሩዋቸውን ችግሮች በሙሉ ድንገተኛና እነሱ ያላሰቡት ችግር እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ::እጃቸው እንደሌለበት  ለማስመሰል ይሞክራሉ::
በየጊዜውና በየቦታው የሚፈጠሩ ከባባድ ችግሮችም አገራዊ ቅርጽ ተላብሰው  እንዲቀጥሉ ይፈልጋሉና ህዝቡን በተለያየ የግል ግምት ተዘፍቆ እንዲቆይ ለማድረግ የሚጠቅማቸውን ዘዴ ይጠቀማሉ:: ለዚህም ነው በፓለቲካው ዘርፍ አንዳች ችግር ሲፈጠር ህዝቡ ብሄር ከብሄር ጋር በመጋጨቱ ምክንያት የተፈጠረ ችግር አድርጎ የሚወስደው::እንደዚያ የሚመስላቸውና በመንግስት ሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ለመታለል የተዘጋጁ ዜጎችም በርካታ ናቸውና ሃሰታቸው ሰምሮ በጥፋት ላይ ሌላ ጥፋት በውድመት ላይ ሌላ ውድመት እያደረሱ እንዲቀጥሉ በርከፍቶዋል::  በሐይማኖቱ ዘርፍም ተመሳሳይ ነው:: አንዳች ውድመትና ቃጠሎ ሲከሰት ሐይማኖተኛ ከሐይማኖተኛ በመጋጨቱ ምክንያት የተከሰተ ችግር የሚመስላቸው በርካቶች ናቸው::እውነታውግን ሌላ ነው::
በዚህ መልኩ በየወቅቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሙሉ ጥቂት ግለሰቦችና የተለያዩ ቡድኖች የሚፈጥሩዋቸው ችግሮች እንደሆኑ አድርገን እንድናስብ ሁኔታዎችን አመቻችተዋልና እኛም እንደዚያ እያሰብን ሳናውቀው የሴራቸው ተባባሪና አስፈጻሚ እስከመሆን ደረጃ ልንደርስ ችለናል:: ሴራቸውን አለማወቅና እነሱ በቀየሱልን ቦይ ዝም ብሎ መፍሰስ….. የሴረኞቹ ተባባሪና ይልቁንም አስፈጻሚ እንደመሆን ይቆጠራልና!
በዚህ አይነት መንግስታዊ ሴራ ምክንያት ብዙዎች ፓለቲከኞች ብዙ ይላሉ::ብዙ አክቲቪስቶችም የተለያየ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ: ይህ አይነቱ ግምታዊ ትንታኔና ተቆርቁዋሪነትን መሰረት አድርጎ የሚሰነዝር ሃሳብ ጥቆማና መላምት ደግሞ ህዝቡን ከማወዛገብና እርስ በርስ ጥርስ እዲነካከስ ከማድረግ አልፎ እንዳይደማመጥና እንዳይናበብ መሰናክል ሆኖበታል::ይህ በራሱ የመንግስታዊው ሴራ ውጤት ነው:: ምክንያቱም መንግስት ሆነ ብሎ ችግር ፈጥሮ የችግሩን ምንጭ እያወቀ እስከደበቀ ድረስ ህዝቡ በራሱ ግምታዊ ድምዳሜ ከመንጎድ ውጭ ሌላ ምርጫ አይኖረውም:: ይህንንም ባልስልጣናቱ ያውቃሉ:: ይፈልጉታልም::ህዝቡምእነሱ እንደሚፈልጉት እየሆነላቸው ነው::
ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ወቅት በመንግስት ደረጃ እየተታለለ ያለ ህዝብ መሆኑ ታውቆ ጫናውን መንግስት ላይ ብቻ ማድረግ አለበት እንጂ አንዴ ጃዋር በሚባል ንፍጥ ግለሰብ ማሳበብ ሌላ ጊዜ በሌሎች  ግለሰብና ቡድኖች ላይ ጣት መቀሰር እነሱን አውግዞና ሰድቦ ወደ ዝምታ መመለስ ፍሬ አልባ ጫጫታ ይባላል:: ማብቃትም አለበት::አሰልችም ነው!
ህዝብ እውነታውን እያወቀው በተግባርም እያየው መንግስት ደግሞ ከህዝብ በላይ ማወቅ እንደሚችል እየታወቀ ነገር ግን አውቆ ዝም ካለ መጠየቅ ያለበት መንግስት እንጂ ግለሰብና ቡድን አይደለም::  መፍትሄው ህዝባዊ አብዮት ከሆነም ህዝባዊ አብዮት ማስነሳት የሚቻለው በመንግት ላይ እንጂ በመንስጥ ጥበቃ በሚደረግላቸው በተራ የመንደር ውሪዎች ላይ አብዮት ማስነሳት አይቻልም!
 እናም እውነታው አንድ እና ነው! እውነታውም እያንዳንዱ ችግርም ሆነ ሁሉም አይነት አገራዊና ህዝባዊ ጥቃትና ውድመት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግጭት ግድያ አፈና እገታ ቃጠሎ ወዘተ…..በመንግስት (በገዥው ፓርቲ) ፍላጎትና ይሁንታ ሆነ ተብሎና ታስቦበት የሚከናወን መሆኑ ነው:: ይህ በመላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ መታወቅ አለበት:: መታወቅ ባይችል እንኩዋ መታሰብ አለበት::
ይህን ለማሰብና ለመድረስ ደግሞ የግድ የአክቲቪስት ትንተናና የፓለቲከኞች የግል ማብራሪያ አሊያም እንዲህ አይነት የጽሁፍ ግፊት አያስፈልገውም::ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አገሪቱ ላይ በተግባር እየሆነ ያለውን ነገር መለስ ብሎ ማሰብ መመርመርና ማገናዘብ መቻል ብቻውን በቂ ነው::ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የደረሱ ጥፋትና ውድመቶች የፈራረሱ የሐይማኖት ተቁውማት የተገደሉ የተፈናቀሉ ዜጎች ብዛት ወዘተ….ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነገሮች ያለአንዳች መፍትሄና ህጋዊ እርምጃ እንዲሁ በዝምታና በማድበስበስ መታለፋቸውን እንደ ምሳሌ አንስቶ መዘዘር ይቻላል::ተዘርዝረው ስለማያልቁ ግን ያን ማድረግ አይቻልም::
ስለዚህ ሁሉም ተናብበው ይቆምራሉና በአገርና በህዝብ ላይ እየቆመሩ እንዳሉ ህዝቡ ማወቁን ቢያንስ ሊያውቁት ያስፈልጋል:: ህዝቡ ይህንን ያላወቀ መሆኑን ማሰባቸውም ነው ፋታ ቢስ የሆነ ተከታታይና ተደራራቢ ችግር እየፈጠሩ አገር የማፍረስ የህዝብ አንድነትን የመበጣጠስ ተግባራቸውን በቀላሉ ተግባራዊ እያደረጉ እንዲቀጥሉ ያገዛቸው::ይህ ስለሆነ በጋራ ማስቆም ብቸኛው መፍትሄ ነው::
በርግጥ ግን ይህን ለምን ያደርጋሉ? እንዴት የገዛ አገራቸውን ሰላም ጠሉ? ከመንግስት አቅም በላይ ያልሆነ ችግር እንደሆነ እየታወቀ ለምን ከአቅም በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሳየትና ማስቀጠል አስፈለገ? እንዴት የገዛ አገራቸውን ህዝብ ማናከስና ማቆራረጥን መረጡ? የሐይማኖት ተቁዋማትን ማውደም ለምን አስፈለጋቸው? የህዝብ ጥያቄ ያልሆኑ ነገሮችን የህዝብ ጥያቄ አስመስሎ ማቅረብና የግጭት ምንጭ ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ነውጠኛ ቡድኖች ለምን ድጋፍና እውቅና ሊቸራቸው ቻለ? ለምን የሰሜኑ ህዝብብተከፋፍሎ እንዲቀር ተፈለገ? ይህ ሁሉ ውድመት እየደረሰ ባለባት አገር ላይ መሪው ለምን የዓለም ሰላም ሽማልማት እንዲሰጠው ተፈለገ?ፓርቲዎች ስማቸውንም ግብራቸውንም ለውጠው ራሳቸውን እንዲያከስሙ የተደረገበት ምክንያት ምንድነው?የሚገደሉ ሰዎች የአገዳደላቸው ሚስጥር በመንግት ደረጃ ለምን ይፋ እንዳይሆን ተፈለገ? የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ(የዓላማ መስቀያ) በገዛ ዜጎቹዋ በገዛ ምድሩዋ በአደባባይ ሊቃጠል የቻለበት “ትክክለኛ” ምክንያት ምንድነው? በዚህስ ምዕራባውያን ለምን ደስ ተሰኙ? ምዕራባውያን ምን ያተርፋሉና ነው ይህን ላደረጉና ላስደረጉ ባለስልጣናት ድጋፍ የሚሰጡት? የተባለው ለውጥ ለውጥ ሳይሆን ነውጥ መሆኑ በዓለም ፊት እየታወቀ ዜጋ ዜጋውን በገጀራ እያስፈራራ ያለባት አገር መሆኑዋ እየታወቀ ይህም የለውጡ ውጤት መሆኑ እየታወቀ ነገር ግን እንደ ትክክለኛ ለውጥ ተቆጥሮ የዓለም መንግስታትን ትኩረት የሳበበት ምክንያት ምንድነው?ከዓረብ አገራት እስከ አውሮፓና እስከ ሰሜን አሜሪካ ከሩቅ ምስራቅ እስከ ላቲን ያሉ አገሮች መንግስታት ለዚህ አይነቱ ደም አፋሳሽ ለውጥ ልዩ ድጋፍ መስጠታቸውና ያልተለመደ አድናቆት መቸራቸው ስለ ምን ነው???
የኢትዮጵያን ወቅትዊ የፓለቲካ ቁማር በጥልቀት ለመገንዘብ የእነዚህንና የእነዚህን መሰል አወዛጋቢና ግራ አጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያስፈልጋል:: የእነዚህን ጥያቄዎች ትክክለኛና አሳማኝ የሆኑ መልሶች ለማግኘት ደግሞ ሌላ ምንም አይነት አማራጭ የለም!ከዚህ መጻህፍ በስተቀር!!! አንብቡት አስነብቡት!!!ከታከታችሁ ለትውልድ አስቀምጡት!!! በልበ – ሙሉነት ይሄን የምለው ለምን እንደሆነ ያነበቡት ያውቃሉ!!
Filed in: Amharic