>
12:46 am - Wednesday July 6, 2022

ሰው! ".. ብዙ ምስጢር እንዳላወጣ እንጂ 17 መርፌ ብለህ ዘፍነሃል ብሎ ጥርሱን የነከሰው ህወኃት..." (የኑስ መሀመድ)

ሰው!

 “.. ብዙ ምስጢር እንዳላወጣ እንጂ 17 መርፌ ብለህ ዘፍነሃል ብሎ ጥርሱን የነከሰው ህወኃት…”

የኑስ መሀመድ
      እኔ ስለ ቴዲ ስተነፍስ ያው ስለሚወደው ነው እንደሚባል የታመነ ነው። ቢሆንም ግን ልተንፍስ። እንደውም አንዴ ስለያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት በሰራሁት ፕሮግራም ላይ “ሙዚቃ ሕይወቴ” የተሰኘውን ስራውን ለማጀቢያነት (under scoring) ተጠቅሜው ስብሰባ ላይ የኑስ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የቴዲ አፍሮን ሙዚቃዎች መጠቀሙን መተው አለበት የሚል ሂስ ካንዱ አለቃ ተሰንዝሮብኝ ያውቃል። አንድ የማይዋሸው ሐቅ ቴዲ ልሳናችን በመሆኑ ለሱ ያለኝ አክብሮት ጥልቅ ነው። ነገር ግን እንደቀረበብኝ ትችት ምክንያት ፈጥሬ የእሱን ሙዚቃ አስኪጄ አላውቅም። እነሱ ግን አድዋ በደረሰ ቁጥር ጥቁር ሰው አይተላለፍም ብለው አግደው…የጥቁር ሰውን ቪድዮ ክሊፕ ምስሉን ሰርቀው ለሌላ ፕሮግራም ሲጠቀሙበት ሌብነታቸው አይሰቀጥታቸውም ነበር። ያም ሆነ ይህ ቴዲ “ፌቨር” እንዲደረግለት አይፈልግም ሙዚቃው በተለቀቀ በማክሮሰከንዶች ውስጥ በአራቱም የዓለም ማዕዘን በሚገኙ ኢትዮጽያውያን ዘንድ ተፈልጎ ሚደመጥ ነውና።
     አንዴ፣ አንድ ቆዬት ያለ የሐገር ፍቅር ድምጻዊ  ቃለመጠይቅ እያደረኩ ስለ አንጋፋው ድምጻዊ ጥላሁን ገሰሰ የነገረኝን አልረሳውም። የጥላሁን ሙዚቃ እንደተለቀቀ ከመላው ሀገሪቱ ጥላሁን “ምን ዘፈነ?” ሳይሆን “ጥላሁን ምን አለ?” ተብሎ ነበር የሚጠየቀው። የቴዲ አፍሮም እንዲሁ ነው። ቴዲ አፍሮ ምን ዘፈነ ሳይሆን “ምን አለ?” ነው ሚባልለት። ሰው የጥላሁንን ቅኔ ለመስማት እንደሚጓጓው ሁሉ የቴዲ አፍሮንም ቅኔ ለመስማት እንቅልፉን አጥቶ ነው ሚያድረው። በነ አልማዝንና…መሰል ስራዎቹ ጥላሁን ገሰሰ ለእስር ተዳርጎ እንደነበር እሙን ነው። ከዚ ከድምጻውያን እስርና እንግልት ጋር በተያያዘ የቴዲን ያክል ባይሆንም በርካቶች ከጸበሉ ቀምሰዋል። ለምሳሌ ቀደም ባለው ጊዜ ድምጻዊ ፍሬው ኃይሉ “እየተኙ ነቁ” በተሰኘው ተወዳጅ ስራው ወጥመድ ውስጥ ገብቶ ነበር።
    የቴዲ አፍሮን ነገር አንዴ ከጀመርኩት ለመግታት ይተናነቀኛል… ብዙ ምስጢር እንዳላወጣ እንጂ 17 መርፌ ብለህ ዘፍነሃል ብሎ ጥርሱን የነከሰው ህወኃት “ደጉ” የተባለ ምስኪን ሰውን ገድለሃል የሚል የፈጠራ ክስ አዘጋጅቶ ድምጻዊውን ከ17 መርፌ አንዷን ቅመሳት እያለ ለጆሮ ሚከብዱ ግፎችን ይፈጽሙበት እንደነበር ማዕከላዊ ይሰራ ከነበረ ሰው ስምቻለሁ። ቴዲ ግን ዋጠው። ዳግማዊ ቴዎድሮስ ነውና የግፍ ሽጉጣቸውን ጨልጦ የኪነትን ነቀርሳ ድል አደረገ። እንደኛ ለበቀል አይናገር አይጋገር እንጂ ቴዲ ለጊዜው ዘፈኖቹን ገታ አድርጎ ያደረሱበትን እንግልት ይፋ ቢያወጣው ወያኔ ኢህአዲግን ለሰላምታ ይቅርና ለዐይንም በተጸየፍናት። ብቻ ሁሉም አልፏል። አሁን እነሱም በሚወዱት ህዝባቸው መሃል ብቻ ናቸው ቴዲም ከሚወደውና ከሚወዱት ሕዝቦች መሃል ነው።
    ቋጥኝ የሚያክል ብሶት ተሸክሞ በጽናት መቆም የሚችለው ቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ የሚል አልበሙን ለቆ የነጭን ሙዚቃ ከቢልቦርድ ሰንጠረዥ አንሸራቶ በመጣል ያገሩን ስም ከፍ አድርጎም አስጻፈ። ለዚህም የውለታ አልጠየቀንም ይልቁንስ በምትኩ ኮንሰርት ከለከልነው። የሆነ ሆኖ አዲሱ ወጀብ ቴዲ አፍሮ ሙዚቃዎቹን ለአድናቂዎቹ ከማቅረብ አልገደበውም። እነሆ ከባህርዳሩ ስቴዲዬምና ከሚሊኒየሙ አዳራሽ ቀጥሎ ይህንን የነጭን ሙዚቃ ከቢልቦርድ አንሸራቶ የጣለውን አልበም ለ3ኛ ጊዜ ሊያቀርብ ነው። ታሪካዊ ቅዳሜ። ከቦብ ማርሌ ልደት በኋላ ፤ አስርት ዓመታት አልፈው የተገኘ የደስታና የብሶት እህታ ምሽት።
   ምን ልላችሁ ነበር…ጽሁፉን የጀመርኩት…? ረሳሁት! ሌላ ጊዜ ብመለስ ይሻላል። ላሁኑ ግን ተወደደም ተጠላም…ቴዎድሮስ ካሳሁን ኮንሰርቱን  ውቅያኖስ ውስጥም ያዘጋጀው። የጦር ቀጠና ውስጥም ይዝፈነው። ተከፍሎ ማያልቅ ውለታው አለብንና ከሙዚቃ ትርዒቱ አልቀረንም!!!
Filed in: Amharic