>

የቂሊንጦ ማስታወሻ...!!!

የቂሊንጦ ማስታወሻ…!!!

ዛሬ በጠዋት ወደቂሊንጦ እስር ቤት አምርተን ነበር – ከጓደኛዬ ኤፍሬም ደሳለኝ ጋር። የጉዞው ዓላማም በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችንን ለመጠየቅ ነበር።
በቂሊንጦ ዞን አራት ውስጥ፣ በሙስና ወንጀል የተጠረጠረውና የክስ ሂደት ላይ የሚገኘው ኤርሚያስ አመልጋ፣ እንዲሁም በሰኔ 15/ 2011 ዓ.ም በባህርዳር እና አዲስ አበባ ከተማ በተከሰተው የግድያ ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው እነ ክርስቲያን ታደለ፣ በለጠ ካሳ፣ ሲሳይ አልታሰብ፣ አስጠራው ከበደ፣ አየለ አስማረ፣ ….ና ሌሎችን ጨምሮ 18 እስረኞች ይገኙበታል።
ቂሊንጦ እስር ቤትን ለዓመታት አውቀዋለሁ። በቆሸሸው፣ ዛሬም ድረስ ባልዘመነውና ጭካኔ በተሞላበት የኢትዮጵያ ፓለቲካ ሳቢያ፣ በጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ የግፍ እስር ሰለባ የሆኑ በርካታ ወገኖቼን ተመላልሼ ጠይቄበታለሁ።  እኔም ተመላልሼ ታስሬበታለሁ።
 የኢትዮጵያ እስር ቤቶች፣ አንዳቸውም ቢሆኑ እንኳን፣ ለአፍታ የሚናፈቁ አይደሉም፣ ያስጠላሉ ብል ይቀለኛል። ዛሬም ይሄንን እስር ቤት፣ ከሶስት ዓመታት በኅላ ለጥየቃ በትዝብት ተመለከትኩት። የዓመታት የማያስደስቱ ትውስታዎችንም ጫረብኝ። በፍርድ ሂደት፣ ከወራቶች አንስቶ ዕድሜ ይፍታህ ድረስ የፓለቲካ እና የህሊና የግፍ እስረኞች የሀሰት ፍርድን አስተናግደውበትም ያውቃሉ። የግፍ እስርና የግፍ ፍርድ ሃገርና ህዝብን ጎዳ እንጂ አልጠቀመም። ይሄንን በተግባር አይተናል። ዛሬም የፓለቲካ እስረኞችን በቂሊንጦ ማየት፣ ግራ ቀኙን ማገናዘብ ለሚችል ህሊናና ሰብዓዊነት ከልቡ ለሚሰማው ሰው አያስደስትም ብዬ አስባለሁ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የፓለቲካ እስረኞችን የማናይበት ጊዜ አሁንም ይናፍቀኛል። ነገ ከነገ ወዲያ መምጣቱም አይቀር፣ አምናለሁ!
እንዲህም ሆኖ፣ ከላይ የጠቀስኳቸውንና ሌሎች እስረኞችን ከኤፍሬም ጋር ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ አግኝተን አውግተናቸዋል። ኤርሚያስ አመልጋም ሆነ እነክርስቲያን ታደለ በጥሩ መንፈስ እና ብርታት ውስጥ ሆነው ማየታችን በበጎ ጎኑ እጠቅሰዋለሁ። ከወራቶች በፊት በአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን አብረውኝ የታሰሩ ወገኖቻችንን፣ ዛሬም በአክብሮት እና በእርጋታ – እየሳቁ ጭምር ሳያቸው፣ የእስሩን አሳዛኝነት ዛልዘነጋ ደስ ብሎኛል።
ከአመለ ሸጋው፣ ከትሁቱ፣ ከአዋቂው፣ በበደሉት ሰዎች ላይ ቂምና ጥላቻ ካልያዘው፣ ዛሬም ስለ ሀገር እድገት እርቆ ከሚያስበው ኤርሚያስ አመልጋ ጋርም ከ40 ደቂቃ በላይ ስለተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች አውግተናል። ኤርሚያስ ስቆ ያስቃል። ኮስተርም ብሎ፣ በቁም ነገር ቁም ነገሮችን በአስተውሎት ይናገራል። በእርጋታ ያዳምጣል፣ ባደመጠው ሃሳብ ላይ ሃሳቡን ያጋራል። ….
ለሀገር ብዙ ስራዎችን አስቦ እና አቅዶ የሚሰራ እንደኤርሚያስ አይነት አርቆ አላሚ ሰዎችን በእስር ቤት የሽቦ አጥር ውስጥ ማየት የምር አሳዛኝ ነው። አንዳንዴ፣ እንደዚህ አይነት ሰዎች በጎ ዓላማቸውን እንዳያሳኩ እርግማን (እንደ ሀገር) ያለብንም ይመስለኛል።  “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ ….” የሚለውን ብሂል ያስታውሰኛል።
 ከሰኔ 15ቱ አሳዛኝ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የታሰሩት እነክርስቲያን፣ በኤርምያስ በጣም ደስተኞች መሆናቸውን፣ በኢኮኖሚ ዘርፍ ጉዳይ ከእርሱ ብዙ መማራቸውን፣ ዘወትር ጠንከር ያለ ስፖርት እያሰራቸው እንደሚገኝ፣ ….ወዘተ በጋራ አጫውተውኛል። …..
….የሆነ ሆኖ፣ የእነኤርሚያስንና ክርስቲያንን የተወሰኑት ሃሳቦች እንዲህ ጽፌ ላጋራችሁ አሰብኩ። እነሆ:-
“ያለፋትን 14 ወራት ያለአግባብ ታስሬያለሁ። ቀላል ጊዜ አይደለም። መታሰር የራሱ አሉታዊ ጎን እንዳለው ሁሉ የራሱ ጥሩ ጎንም አለው። ለምሳሌ እኔ:- በመታሰሬ ብዙ ነገሮችን እንድረዳና እንድገንዘብ አድርጎኛል። ትናንት ጠንካራ ነበርኩ። ዛሬም ይበልጥ ጠንክሬያለሁ፣ አልተሰበርኩም። ብርታት ይሰማኛል። ነገሮች ለበጎ ናቸው ብዬ የማስብባቸው ጊዜያቶችም አሉ። እስር አስፈሪ ይመስላል፣ ግን አያስፈራም። እኔም አልፈራም። በተለይ በዚህኛው እስር ብዙ ልምድ አግኝቼበታለሁ። በሌላ በኩል፣ በቀጣይ የምሰራቸውን ጉዳዮች ለይቼ አውቄያለሁ። ስወጣ እሰራለሁኝ። ብርቱ ነኝ። ደህና ነኝ። ስፖርት እሰራለሁ። ከእነክርስቲያንና ሌሎቹም ጋር ጥሩ ጊዜያትን በማማር አሳልፋለሁ። በቅርቡ እንደምንፈታም አስባለሁ። …..”
– ኤርሚያስ አመልጋ
“ከዚህ በኅላ፣ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲን በተግባር ጨብጠን ነው ‘እንቁጣጣሽ እንኳን በደህና መጣሽ’ ማለት ያለብን። አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት አካሄድ አላዋጣንም። እንደ አንድ ሀገር ዜጎች፣ ሁላችንም አሸናፊ ለምንሆንበት ነገር መስራትና በሰላም መታገል ያሻናል። እስራችንን በተመለከተም፣ ለአሳሪዎቻችንም፣ ለእኛ ለታሳሪዎችም፣ ለሀገራችንም የሚበጀው እኛን መፍታት ነው። ….ከእስር እንፈታለን ብዬ አስባለሁ። …..”
 – ክርስቲያን ታደለ
“ዜጎች በግፍ  ሲታሰሩ፣ የአንድ ሀገር ዜጎች የግፍ እስረኞች ፍትህ እንዲያገኙ እኩል መታገልና ድምጽን ማሰማት አስፈላጊ ነው። የፍትህ ጥያቄ በወገንተኝነት መሆን አይገባውም። ….”
በለጠ ካሳ
“በምርመራ ወቅት ፍርድ ቤት ስንቀርብ፣ ይቀርብብን የነበረው ውንጀላ የፊልም ስክሪፕት ይመስለኝ ነበር። ….ብዙ አሳልፈናል። አሁን ይበቃል። ፍቱን”
አስጠራው ከበደ
“እስራችንና የቀረበብን ክስ አግባብ አይደለም። ይሄንን ብዙ ሰው የተረዳ ይመስለኛል። አሁንም ከእስር ልንፈታ ይገባል ብዬ አማናለሁ። ….”
“የአድዋ ድል ኢትዮጵያን ያዋለደ ሃይል ነው”
 
– ሲሳይ አልታሰብ
 …..
ሰላም! 
ፈጣሪ ሃገራችንን ይጠብቅ! 
Filed in: Amharic