>

ክብር - ... ለሀገራቸው፣ ለወገናቸው፣ ለተዋደቁና ለሚዋደቁ - የትናንትም ሆነ የዛሬ የኢትዮጵያ ጀግኖች! (አሰፋ ሃይሉ)

ክብር – ለአንዲትም ቀን – የሀገራቸውን ባንዲራ ከፍ አድርገው ለሀገራቸው፣ ለወገናቸው፣ ለተዋደቁና ለሚዋደቁ – የትናንትም ሆነ የዛሬ የኢትዮጵያ ጀግኖች!

አሰፋ ሃይሉ
ሌተና ኮሎኔል ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም – ወደ ሥልጣን ሲወጣም ሆነ በሥልጣን ዘመኑ – የቱንም ያህል አረመኔያዊ ድርጊቶችን የፈፀመ ጨካኝ ሰው ቢሆንም – ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ያለው ፍቅር ግን ተስተካካይ የማይገኝለት እንደነበረ ሁሉም የሚመሰክርለት ነው፡፡
 መንግሥቱ ኃይለማርያም እውነተኛ ሀገር ጠባቂ ጀግና ወታደር ነበረ፡፡ የሀገር ፍቅርን በሁለመናው የተላበሰ፣ ለሀገሩ ሲል ማናቸውንም ነገር ከመፈጸም ወደኋላ የማይል፣ በሀገሩ ጉዳይ ከማንም ጋር የማይደራደር፣ ብሔራዊ ስሜቱ ከኖረበት ዘመን ብቻ ሳይሆን ከጥንቶቹ ጀግኖች ኃያላን ነገሥታት ንፁህ ብሔራዊ የሀገር ፍቅር ስሜት ጋር የሚስተካከል፣ ከታችኛው ለፍቶ አዳሪ መደብ የወጣ፣ እውነተኛ እና ቆራጥ የኢትዮጵያ ልጅ እንደነበረ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም – በአስራ ምናምን ዓመት የሥልጣን ዘመኑ – ከሚወዳት ሀገሩ ላይ አንዲትም ሰባራ ሳንቲም ለግሉ ጥቅምም ሆነ ለቤተሰቡ ጥቅም ያልሰረቀ፣ ሀቀኛና ሀቀኞችን የሚወድ – ታላቅ የጭቁኖች ወኪል፣ ታላቅ የሀገር ሀብት ባለአደራ ነበር፡፡ የታማኝነት አደራውን ለሀገሩ ተወጥቷል፡፡ እስከቻለው ትንፋሽ ድረስ ሀገሩ እንዳትበታተን ከኢምፔሪያሊስት ኃያላን ጋር አንገት ለአንገት ተናንቋል፡፡ በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የተደገፈውን የሶማሊያ ወረራ ለመቀልበስ እውነተኛ ወታደር፣ እውነተኛ የሀገሩ የቁርጥ ቀን ልጅ ሆኖ፣ በኦጋዴን በረሃ ተንከራቶ፣ ሀገሩን ከወራሪዎች ያዳነ፣ እውነተኛ የኦጋዴን አንበሣ ነበር መንግሥቱ ኃይለማርያም፡፡
የሀገሩን ክብር አሳልፎ ያልሰጠ፣ ለባዕዳን ያላጎበደደ፣ የባዕዳንን ዓላማ ለማሳካት በያቅጣጫው ተሰልፈው ከላይ ከታች በውጊያ የሚለበልቡትን፣ ሀገሪቱን ወደ ጦርነት አውድማነት የቀየሩትን ገንጣዮችና ጎሰኞች ለመመከትና ለመደምሰስ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር›› ብሎ በሙሉ ኃይሉ እየተዋጋም፣ በዚያም መሐል፣ ዛሬ ድረስ የሀገሪቱ ምሰሶ የሆኑ ብዙ ሕዝባዊ ተቋማትን የገነባ፣ ጦርነት ሳይበግረው ብዙ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ፋብሪካዎችን ያቋቋመ፣ ትውልድን አንዱን ከሌላው ሳያበላልጥ – በወረደ የመንደረተኝነት እና የጎሳ ጥላቻ ስሜት ሳይነከር በንፁህ ብሔራዊ የሀገርና የባንዲራ ፍቅር ስሜት ትውልዱን አንፆ ለመገንባት የቻለውን ሁሉ የተጣጣረ፣ ያለውን ሁሉ የሰጠ እና ያደረገ ታላቅ ብሔራዊ ወኔና ታላቅ የሀገር ፍቅርን እና ብሔራዊ ኩራትን የተላበሰ – መቼም የማይተካ የኢትዮጵያ ውድ ልጅ ነበር – ሌተና ኮሎኔል ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም፡፡
በሀገር ፍቅሩ እና በጀግንነቱ የሚያማው ማንም ባይኖርም – ነገር ግን – ኮ/ል ጓድ መንግሥቱ ሰው ነው፡፡ ከሰውም በሀገሩ የመጣበትን ተኩሶ መግደልን ሙያው ያደረገ ጀግና ወታደር፡፡ እና – በሥልጣን ዘመኑ ባገሩ የመጣበት የመሰለውን ሁሉ ዜጋ – በጦርሜዳ እንዳገኘው ተፋላሚ በመቁጠር – እንደ ወገን ሳይሆን እንደ ጠላት ብዙዎችን ደምስሷል፡፡ ከእርሱ የተለየ ሀሳብን የማይቀበል ዓይነተኛ የሶሻሊስት ወታደራዊ አምባገነን ነበረ፡፡ ብዙ በደም የተጠናቀቁ ታሪካዊ ስህተቶችንም ያለምንም ርህራሄ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፈፅሟል፡፡ አስፈጽሟል፡፡ እና በመጨረሻም – ስንቱን በቆራጥነት የመከተና የተቋቋመ ጀግና – ሰው ነውና – ተሸንፏል፡፡ ሲፎክርባቸው እንደኖሩት እንደ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ዮሐንስ ሳይሆን – ነፍሱን እንደሚወድ ከማንኛችንም እንዳልተለየ አንድ ተራ ሰው – በመጨረሻ በሽሽት አፈግፍጓል፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን – በሥልጣን ዘመኑ ከነፈፀማቸው ስህተቶቹ – በአንዲት እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ – እና ትልቅ ትንሽ፣ ይሄ ብሄር ያ ብሄር ሳይል በኖረለትና በተዋደቀለት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ – ለአንዲትም ቀን ያልተደራደረው – በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜቱና አርዓያ በሆነ ከሌብነትና ዝርፊያ በፀዳ የሀቀኝነት ሕይወት የተመላለሰው – ሀገሩን አፍቃሪው – እውነተኛው የኢትዮጵያ ወኔያም ቆራጥ ጀግና ወታደር – ጓድ ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም – አግልግሎቱንና ውለታውን በማይዘነጉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ዘንድ – ሁልጊዜም በጀግንነቱ እና በሀቀኝነቱ ሲታወስ ይኖራል!!
ክብር – ለአንዲትም ቀን – የሀገራቸውን ባንዲራ ከፍ አድርገው ለሀገራቸው፣ ለወገናቸው፣ ለተዋደቁና ለሚዋደቁ – የትናንትም ሆነ የዛሬ የኢትዮጵያ ጀግኖች!
ከፍ ያለ ክብር እና የበዛ ፍቅር – በሕይወት ዘመኑ ለሀገሩ ኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በጀግንነትና በሀቅ ለተዋደቀለት – ለጓድ ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም – እና ለውድ ቤተሰቦቹ – ባለበት፣ ባሉበት ይድረሳቸው!
ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ፀንታ ለዘለዓለም ትኑር!  
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic