>

የስዩም ክህደት! (አርአያ ተስፋማርያም)

የስዩም ክህደት!

 

አርአያ ተስፋማርያም
 
የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ስዩም መስፍን ከሰሞኑ በትግርኛ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለዋል። ” ኢሳያስ እንደሚለው ትግራይን በሃይል እወራለሁ ካለ የትግራይ ህዝብ፣ ህወሀት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ የፌዴራል ስርአቱን የሚደግፉ አይፈቅዱም። ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ሃይል ከኢሳያስ ጋር ተመሳጥሮ ህዝብን በመከፋፈል በሚፈፅመው ድርጊት ኢሳያስ በሃይል እገባለሁ ይላል። ይህ ሃይል አገርና ሉአላዊነትን አሳልፎ በመሸጥ ሊከሰስ ይገባል” ሲሉ አስቂኝና አሳፋሪ ዲስኩር አሰምተዋል።
 ከማንም በፊት ስዩም መስፍን ለፈፀሙት ክህደትና ውሸት መጠየቅና ለፍርድ መቅረብ የነበረባቸው እሳቸው ናቸው! “ባድመ ተፈረድልን” ብለው በውሸት ለህዝብ ተናግረው ሰልፍ እንዲወጣ አድርገዋል። ለአገር ሉአላዊነት መስዋእት በሆኑ ጀግኖችና በህዝብ እንዲሁም በአገር ላይ ትልቅ የክህደት ወንጀል ፈፅመዋል! እሳቸው በወቅቱ የዋሹበት ሉአላዊነት መከበር በግንባር ከተፋለሙ ኢትዮጵያዊያን አንዱ የወቅቱ ወታደራዊ መኮንን የነበሩት አብይ አህመድ ናቸው! ስዩም መስፍን ከማንም በፊት በጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ተይዘው መከሰስና ለፍርድ መቅረብ ይገባቸው ነበር! ይህን የክህደት ዲስኩር መቀሌ መሽጎ የሚዘላብደው ስዩም ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጥም። ስዩም በረሃ የወለደው ልጁ መብራቱ ስዩም አሜሪካ የተመቸ ኑሮ እየገፋ ዛሬ የክህደት ካባ አጥልቆ ስለአገር ሉአላዊነት ጠበቃ በመምሰል የደሃውን ልጅ ለማስጨረስ የውሸት ዲስኩር ያሰማል።
 በነገራችን ላይ ስዩም መስፍን በአውስትራሊያ መኖሪያ ገንብቷል። ቪላው በሪል ስቴት ደረጃ የተገነባ ሲሆን ግንባታውን በውክልና ያከናወነው የቀድሞ የድርጅቱ ታጋይ ኬኔዲ ነው። ስዩም ገንዘቡን ያስወጣው በአንድ አውስትራሊያዊ ዜጋ ሲሆን ይህ ነጭ በትግሉ ዘመን ከስዩም ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለውና ሁለት ልጆቹ በመቀሌ “ኢንጂነር” ተብለው ከፍተኛ ደመዋዝ በዶላር እንደሚከፈላቸው ታውቋል። ቦሌ ከሳይ ኬክ ቤት ገባ ብሎ የነበረውና አሁን አዜብ መስፍን የምትኖርበት የስዩም መስፍን ቤት በ1996 ዓ.ም የኢራን ምንጣፍ በሁለት ሚሊዮን ለ”ባህላስ ካርፔት” ከፍሎ እንዳስነጠፈ ማረጋገጫ አለ። በወቅቱ መረጃው በኢትኦጵ ጋዜጣ ይፋ ተደርጓል። አንድ ቀን ለፍርድ ከሚቀርቡ የክህደትና ውሸት ቋት ሌቦች አንዱ ስዩም መስፍን ነው።
Filed in: Amharic