>

ኤርሚያስን ኣመልጋን ያውቁታል? ይበሉ ይተዋወቁት!  (ዋዜማ ራዲዮ)

ኤርሚያስን ኣመልጋን ያውቁታል? ይበሉ ይተዋወቁት!

 

ዋዜማ ራዲዮ
 ‹‹ሁለት ወር ስጡኝና 200 ሚሊዮን ብር ሰብስቤ እመጣለሁ!!!›› አመንነው! እውነት ለመናገር ኤርሜን አለማመን ከባድ ነው!!!
 
ኤርሜያስ ከብዙ ብር ሌላ ብዙ ዕውቀት፣ ብዙ ሕልም፣ ብዙ እቅድ፣ ብዙ ቅዠት…፡፡
የአገሬ ሐብታም ቁርጥ ካላንቆራጠጠው ሀብታም የሆነ አይመስለውም፡፡ ሆዱ የየካ ተራራን ካለከለ የበለፀገ አይመስለውም፡፡ ኤርሚያስ ስጋ መብላት ከተወ ዘመን የለውም፡፡ ሰውነቱ ላይ ሩብ ኪሎ እንኳ ትርፍ ስጋ አትገኝም፡፡
የ50ኛ ዓመት ልደቱን ካከበረ ዘጠኝ አመት አለፈው! እሱ ግን አሁንም 33 ነው የሚመስለው፡፡ ዉሃ ነዋ የሚጠጣው፡፡ ኩልል ያለ ዉሃ! ያውም እራሱ ያመረተውን ዉሃ! ኮንኮርድ እየተዝናና ዉሃ የሚጠጣ ሀብታም ካለሱ አይቼ አላውቅም፡፡
እግዚአብሔር ዉሃን ፈጠረ፤ በጊዮን በኩል ወንዝ ሆነህ ፍሰስም አለው፡፡ ከዝንተ ዓለም በኋላ ያን ዉሃ መለስ ዜናዊ ገደበው፤ ኤርሚ በላስቲክ አሽጎ ቸበቸበው፡፡ ሃ ሃ…ኤርሚ ብልጧ!
 ስው የሄደበትን መንገድ መሄድ ይታክተዋል፡፡ ጥርሱን የነቀለው በነጭ ካፒታሊዝም ነው፡፡ ደንበኛ የዎልስትሪት ቆማሪ፡፡
ነገር ሲሰክን አይወድም፡፡ በትንሹ አይረካም፡፡ ዛሬ ፋብሪካ ከፍቶ ትርፍ እየተንፎለፎለለት ድንገት ተነስቶ ሊዘጋው ይችላል፡፡ ግድ የለውም፡፡ አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ ‹‹ገዢ ፈልግ›› ይለኛል፡፡ ‹‹አብደሀል?›› አልኩት፡፡በዉዳቂ ብር የገዛውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ሽጥልኝ ያለኝ ቀን ነው እንደዚያ የደፈርኩት፡፡ አፌን አውጥቼ ‹‹አብደሀል ወይ›› አልኩት፡፡
‹‹ምን ላርግ- ሥራው ትርፍ ብቻ ሆነብኝ!›› አለኝ፡፡ ያን ቀን ሰውዬው የፈረንጅ ቡዳ የለከፈው ንክ ዲያስፖራ እንደሆነ ጠረጠርኩ፡፡ ነጋዴ እንዴት ትርፍ ይጠላል?
‹ዋና ጉዳይ ገዳዩ›› ሆኜ ለተወሰኑ ጊዜያት ሰርቻለሁ፡፡ አንዴ 25 ውየሚሆኑ የማርኬቲን ሠራተኞቹን ሰብስቦ እያወያየን ድንገት ይህን ተናገረ፤ ‹‹ምንም ነገር አትፍሩ፣ እኔ ጋር መስራት ካልወደዳችሁ ጥላችሁኝ ሂዱ፤ ሁለት ጊዜ የመኖር ዕድል የላችሁም፡፡ የራሳችሁን ነገር ሞክሩ! ዘላለም ለኔ አገልጋይ መሆን የለባችሁም እኮ፡፡ ሕይወትን መጋፈጥ ልመዱ፡፡ እኔ በበኩሌ ሺ አመት እንደ አይጥ ከመኖር አንድ ቀን እንደ አንበሳ ሆኖ መሞትን እመርጣለሁ››
ሰውየው ብዙ እንግዳ ባህሪያት አሉት፡፡
የአቶ አስፋውን ክራውን ሆቴል ያፈራረምኩት ለታ ‹‹ኤርሜያስ…ምነው ግዢ አበዛህ! ደፈርከኝ አትበለኝና ገንዘብ አወጣጥህን አልወደድኩትም፡፡ ሰዎቹ ቀዳዳ ካገኙብህ አንድ ቀን አያሳድሩህም-ዘብጥያ ነው የሚወረውሩህ›› አልኩት፡፡ ስስ ከንፈሩን ገለጥ አድሮጎ ሳቀና መልስም ሳይሰጠኝ አለፈኝ፡፡ ቆይቶ ጨዋታውን ከዘነጋነው በኋላ ወደ ጆሮዬ ተጠጋና እንዲህ አለኝ- ‹‹አይገርምህም! ቅድም ያልከኝ ነገር ትንሽ ትንሽ ናፈቀኝኮ…››
‹‹ምኑ?››
‹‹ዘብጥያ መውረዱ፣ ጥሩ እረፍት ይሆነኝ ነበር ብዬ አሰብኩ፡፡ በጊዜ ማጣት ጀምሬ የተውኳቸው መጻሕፍት ነበሩ…›› ብሎኝ ተከዘ፡፡ ሰውየው ያመዋል እንዴ?!
እንደዚያ ብሎኝ ሲያበቃ ከአመታት በኋላ በደቡብ ሱዳን በኩል ወደ ዱባይ ፈረጠጠ ሲሉኝ አዘንኩበት፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን እንደሚመለስ ዉስጤ ይነግረኝ ነበር፡፡ ይቅርታ ባያረጉለት እንኳ ፕላስቲክ ሰርጀሪ ተሰርቶም ቢሆን አሻፈረኝ ብሎ ይመለስ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ኤርሚያስን ድሮም ሳውቀው ብርን የሚያፈቅርበት መንገድ ከሌሎች ሀብታሞች ይለያል፡፡ ከብርና ከክብር ይልቅ በአዲስ መንገድ ሄዶ ስኬት መቀዳጀት ይወዳል፡፡ ከዉጤት ይልቅ ሂደት ያዝናናዋል፡፡
ማልዶ ከእንቅልፉ ይነሳና አስቸኳይ የቦርድ ስብሰባ ጥራልኝ ይለኛል፡፡ አባላቱን ሰብስቦ የሆነ የእብድ ሐሳብ ያቀርብላቸዋል፡፡ ‹‹ ከንግዲህ አሸዋና ሲሚንቶ እያቦካን አንኖርም፡፡ አዲስ ነገር መሞከር ይኖርብናል፡፡›› አዳሜ በድንጋጤ ይቁለጨለጫል፡፡ ለመሆኑ ከናንተ ዉስጥ ማግኒዢየም ቦርድ የሚያውቅ አለ? በስቲል ስትራክቸር ሰርተን በስድስት ወር 150 ቤት እናስረክባለን፡፡›› ሌላ መቁለጭለጭ፡፡
የሆነ ማለዳ መጣና አክሰስ ሪሶርት ሆቴል ከነገ ጀምሮ መገንባት እንጀምራለን አለ፡፡ ደነገጥን፡፡ ምንድነው ደግሞ ‹‹ሪሶርት ሆቴል?›› አልነው፡፡
‹‹ብዙ ዲያስፖራ አገር ቤት ሲመጣ ማደርያ የለውም፡፡ ዘመድ ቤት ማደር ደግሞ ነጻነቱን ይጋፋል፡፡ ሆቴል አልጋ መያዝ ኪሱን ይጎዳዋል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ድያስፖራ 3ሺ ዶላር እናስከፍለዉና ኩፖን እንሰጠዋለን፡፡ ያ ኩፖን የምንገነባው ሪሶርት ሆቴሉ ዉስጥ ለ25 ዓመታት በነጻ እንዲገለገል ያስችለዋል፡፡ እድሜውን ሙሉ በዓመት ለአንድ ሳምንት አዲሳባ ሲመጣ የሚያርፍበትን ሆቴል እንሰራለታለን፡፡
ተቁለጨለጭን፡፡ ‹‹ሁለት ወር ስጡኝና 200 ሚሊዮን ብር ሰብስቤ እመጣለሁ፡፡›› አመንነው፡፡ እውነት ለመናገር ኤርሜን አለማመን ከባድ ነው
Filed in: Amharic