>

«ቅዱስ ሲኖዶስ ማንንም የማውገዝ ስልጣን የለውም!" ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ። ምነው አባቴ....?!   (ጴጥሮስ አሸናፊ)

«ቅዱስ ሲኖዶስ ማንንም የማውገዝ ስልጣን የለውም!”

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

ምነው አባቴ….?!  

ጴጥሮስ አሸናፊ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በ OMN የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው «ቅዱስ ሲኖዶስ ማንንም የማውገዝ ስልጣን የለውም፤ ማውገዝ የሚችለው ስልጣነ ክህነት የሰጠው ጳጳስ ብቻ ነው።»  የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አባታችን!
በ325 ዓ.ም በኒቂያ አርዮስ የተወገዘው በሲኖዶስ እንጂ ስልጣነ ክህነት በሰጠው ጳጳስ አልነበረም፣
በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ጳጳሱ ንስጥሮስ የተወገዘው በሲኖዶስ እንጂ ሥልጣነ ክህነት በሰጠው ጳጳስ አልነበረም፤
በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ መቅዶንዮስ የተወገዘው በሲኖዶስ እንጂ ሥልጣነ ክህነት በሰጠው ጳጳስ አልነበረም።
በቅርብ ጊዜ ብፅዕነታቸው በዋና ጸሐፊነት ባገለገሉት ቅዱስ ሲኖዶስ የሐራ ጥቃ አቀንቃኞች በሲኖዶሱ አልተወገዙምን?
ይህ የአባቴ አቡነ ሳዊሮስ ንግግር በቤተክርስቲያን የቀኖና መጻሕፍት  ያልተደገፈ በግብታዊነት የተነገረ ንግግር ነው። ለመሆኑ አሁንስ ቢሆን ውግዘት የት አለ? አራቱ የኦሮሚያ ቤተክህነት ሊቃነመናብርት ሥልጣነ ክህነታቸው በቀኖና እስኪመለሱ ተያዘ እንጂ መቼ ተወገዙ? ኧረ አባታችን ወደ ቀደመ አባትነትዎ ይመለሱ!
ለመሆኑ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በምን መስፈርት የኦሮሚያ ቤተክህነት አቀንቃኝ ሆኑ? የዚህ ቡድን አባል ለመሆን ኦሮሞነት እንደ መመዘኛ ከተቆጠረ ብፁዕ አባታችን በኦሮሚያ ክልል ተወለዱ እንጂ ኦሮሞ አይደሉም። በርግጥ ኦሮሞነት በኦሮሚያ ክልል ለተወለደ ሁሉ የሚሰጥ ከሆነ ይህን መስፈርት ያሟላሉ።
በቀደመ ስማቸው አባ አካለ ወልድ ሞገስ ይባሉ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የተወለዱት በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳበርጋ አዳዳ ባለወልድ ነው። ኦሮምኛና አማርኛ መናገር ስለሚችሉ በወቅቱ የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ስራ አስኪያጅ በነበሩትና ያሁኑ የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ቡድን መሪ በላይ መኮንን ጠቋሚነት በአቡነ ጳውሎስ አዎንታ ለኦሮሚያ ክልል ኮታ ማሟያ በማዕረገ ጵጵስና እንዲሾሙ የተደረጉ ናቸው፡፡ አባ አካለ ወልድ በምንኩስና ዘመቸው በአዲስ አበባ በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው።
Filed in: Amharic