>
7:37 pm - Wednesday June 7, 2023

"መጫፈ ቁልቁሉ" እና የዘመናችን ቁልቁል ተጓዥ ‹‹ልሂቃን››!! (አሰፋ ሃይሉ)

“መጫፈ ቁልቁሉ” እና የዘመናችን ቁልቁል ተጓዥ ‹‹ልሂቃን››!!

 
“Mana Ormaa bareedaorra, godo ofi wayya”
“ከሰው አዳራሽ የራስ ጎጆ ይሻላል!!!”
         (— የኦሮምኛ ምሣሌያዊ አነጋገር)
አሰፋ ሃይሉ
የአማርኛ ፊደላት ለኦሮምኛ ተናጋሪው ማኅበረሰባችን የክርስቶስን ወንጌል የገለጡለት ባለውለታው ናቸው፡፡ ኦሮምኛን ቋንቋን በአማርኛ ፊደላት መጻፍ እንደሚቻል አናሲሞስ ነሲብ የተባለው ባለ ብሩህ አዕምሮ የኦሮሞ ተወላጅ (ከጀርመናዊው ሚሲዮናዊ አሳዳጊው ጋር ሆኖ) መጽሐፍ ቅዱስን ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ ‹‹መጫፈ ቁልቁሉ›› ብሎ በመተርጎም በተግባር አስመስክሯል፡፡ አናሲሞስ ነሲብ መጫፈ ቁልቁሉን ተርጉሞ በማሳተም የክርስቶስን የወንጌል ቃል ለኦሮሞ ወገኖቹ ያዳረሰው ከዛሬ 113 ዓመት በፊት ነበር፡፡ በ1899 ዓመተ ምህረት፡፡
በዚያ ዘመን በአናሲሞስ ቅን ልቦና የተከተቡት የአማርኛ ፊደላት እስከዛሬም የኦሮሞን ማኅበረሰብ ከፈጣሪው ጋር አግባብተው እያኖሩት ነው፡፡ በህይወቴ ብዙ ክርስትያን ኦሮሞ ወዳጆች አፍርቼያለሁ፡፡ ብዙ ቤተሰቦችንም አውቃለሁ፡፡ በሆነ የሕይወቴ ዘመንም ለእምነት በተሳብኩበት ሥፍራ አብዛኞቹ ፓስተሮችና ወንጌላውያን የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ፡፡ ከእነዚያ ሁሉ መሐል በአማርኛ ፊደል በመጠቀማችን የጎደለብን የፈጣሪ ፀጋ አለ የሚል አንድም የኦሮሞ አማኝም ሆነ መንፈሳዊ መሪ አላጋጠመኝም፡፡
ፕ/ር (እና ዶ/ር) ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ የአማራና የኦሮሞ እውነተኛው የዘር ሀረግ ምንጭ ብሎ ባሳተመው መጽሐፉ የአማርኛን ፊደላት ‹‹የግዕዝ ፊደላት›› እያለ በመጥራት የግዕዝ ፊደላት ኦሮምኛን ለመግለጽ ከእንግሊዝኛ ቋንቋም፣ ከላቲን ቋንቋም ከአረማይምክ ቋንቋም ሆነ ከየትኛውም ቋንቋ ይበልጥ የተመቸ መሆኑን የሚገልጽ ሰፊ ሳይንሳዊ ትንተናውን አቅርቦት እናገኛለን፡፡ የአማርኛን ፊደላት የግዕዝ ብሎ መሰየሙ አይከፋም፡፡ ማንን ላለማስከፋት እንደሆነ ምክንያቱ ይታወቃልና በምንም ስም ይጠራ ያ አያጨቃጭቀንም፡፡
አንድ የሚገርመኝ ነገር ግን አለ፡፡ አናሲሞስ ነሲብ ከመቶ ዓመት በፊት የታየው ነገር ከሀገሩ ከኢትዮጵያ አኩሪ የፊደል ጥበብ ተጠቅሞ – ተዝቆ የማያልቀውን የፈጣሪን በረከት ለወገኑ ለማዝነብ ነበረ፡፡ የሚገርመኝ የአናሲሞስ ነሲብ አይደለም፡፡ ማንኛውም ችሎታውና ቅን ልቦናው ያለው ሰው ማድረግ የሚገባውን በጎ ተግባር ስላደረገ፡፡ የሚገርሙኝ ከአናሲሞስ ነሲብ ከመቶ ዓመት በኋላ የመጡት የኦሮሞ ልሂቆች ናቸው፡፡ ዓለሙን ሁሉ የወደደውን የክርስቶስን ወንጌል ይሰብካሉ፡፡ ነገር ግን እናት ምድራቸው ኢትዮጵያ ያፈራችውን አኩሪ ፊደሏን በዓይናችን አንይ ባይ ናቸው፡፡ ለምን? የእኛ ቋንቋ እንዴት ከአማርኛ ፊደል ይዋሳል? የሚል እኩይ እና ከሠይጣን ልቦና የፈለቀ የበታችነት መንፈስ ነው ምክንያቱ፡፡
እነዚህ የክርስቶስን የዓለም ወንጌል እየደገሙም፣ በጥበት ተለክፈው የቀሩ አክራሪ የኦሮሞ ልሂቃን ሲሆን ሲሆን ከመቶ ዓመት በፊት ከእነርሱ ቀድሞ የኖረው አናሲሞስ ለኦሮምኛ ተናጋሪው በአማርኛ ፊደላት ተጠቅሞ የፈጣሪን ወንጌል ለሕዝባችን ካዳረሰ፣ እኛ ደግሞ ለህዝባችን ምን የተሻለ ፀጋ እንስጠው? ብለው በመጨነቅና በመጠበብ ፋንታ ይዘውለት የመጡት የአማርኛ ፎቢያን ነው፡፡ የተውሶ ላቲንን ነው፡፡ ያም ላቲን በአማርኛ ጥላቻ የመጣ ላቲን ነው፡፡ እንዴ?! የሰው ልጅ አዕምሮ እንዴት በጥላቻ ይሄን ያህል ይታመማል? የምር ይሄ ሕመም እኮ ነው፡፡ ከባድ ህመም፡፡
እስቲ ይታይህ! ከአንተ መቶ ዓመታት በፊት የኖረው ወገንህ ለወገኑ የሀገሩን ፊደል ተጠቅሞ መልካምን የፈጣሪን ቃል ሲያዘንብላቸው፣ አንተ ያንን የሀገርህን ፊደል ከተፀየፍከው ወይ የራሱን የኦሮምኛ ፊደል አልፈጠርክለት? ወይ ከአናሲሞስ የተሻለ መልካም ወንጌልን አላመጣህለት? የአናሲሞስ ነሲብ መልካምነት ቢቀርብህ – እንዴት ከመቶ ዓመት በኋላ ሌላን ነገር ሳታሻሽል ጥላቻን ብቻ አሻሽለህ የተገኘህ አጉል ልሂቅ ልትሆን በቃህ? ይሄ ከባድ ህመም ነው፡፡ የሌሎች ሀገራት ልሂቃን እኮ ሌላ ቀርቶ በዚህ በ20ኛው ክፍለዘመን አዲስ ፊደላት ያሉት ራሱን የቻለ የመግባቢያ ቋንቋ የፈጠሩ አሉ፡፡
ለዚህ ‹‹ኤስፔራንቶ›› የተባለውን አዲስ የተፈጠረ ቋንቋ እንደ ምሳሌ አነሳለሁ፡፡ የኮምፒውተር ቋንቋ ከአናሲሞስ ነሲብ በኋላ በኖርንበት በ20ኛው ክፍለዘመን የተፈጠረ አዲስ ራሱን የቻለ ቋንቋ ነው፡፡ እኛ በኪቦርድ ላይ የምንጫናቸው ሆሄያት ለእኛ ተብለው የተቀመጡ ምልክቶች ናቸው እንጂ ኮምፒውተሩ የሚግባባበት የራሱ ሰዋስው፣ ፊደልና ቋንቋ አለው፡፡
እንግዲህ እነዚህን የጠቀስኩት አክራሪዎቹ የኦሮሞ ልሂቃን ባደረባቸው የአማርኛ ጥላቻ የተነሳ ባህርማዶ ተሻግረው ራሳቸውንና እናስብለታለን የሚሉትን ማኅበረሰብ የላቲን ፊደል ተገልጋይ ለማድረግ የታተሩትን ያህል ለምን ከቻሉ – ከአናሲሞስ በተሻለ – አዲስ የኦሮሞ ፊደልን አልቀረፁም? ዋነኛ ጠላታቸው አማርኛ ቋንቋና ፊደል ከሆነ ቢያንስ አናሲሞስ የኦሮምኛ ቋንቋ ከእብራይስጥም፣ ከእንግሊዝኛም፣ ከአማርኛም ባልተናነሰ ሁኔታ የፈጣሪን ወንጌል ለመግለጽ የሚችል ምሉዕ ቋንቋ እንደሆነ በችሎታው፣ በዕውቀቱ፣ በጥበቡ፣ በልፋቱ፣ በፀጋው ሠርቶ አስመስክሯል፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት!!
ታዲያ እነርሱስ ለምን ፕሮዳክቲቭ የሆነ ክሪኤቲቭ የሆነ የፈጠራ ችሎታቸውን ተጠቅመው በዕውቀታቸው ለሕዝባቸው አንድ ታላቅ ውለታ አልሠሩም? አናሲሞስ የተባለ ቅን ምሁር ለወገኑ ታላቅ ሥራን ሠርቶ ካለፈ ከመቶ ዓመት በኋላ… መቶ ዓመት ሙሉ ተዘፍዝፎ ከርሞ – የተለያዩ አካዳሚያዊ ማዕረጎች ደርድሮ – ይህን ያህል ሚሊየኖች ሕዝብ ለሚናገረው የኦሮምኛ ቋንቋ –  አንድ እንኳ ነጠላ ፊደል፣ አንዲት ሆሄ ለመፍጠር ያልቻለ የልሂቃን ተብዬዎች ጥርቅም አፍን ሞልቶ ምሁር አለኝ ለማለት አያሳፍርም ወይ? አዕምሮ ጥላቻን ብቻ ሲያመርት መጨረሻው ይሄ የፈጠራ ኃይል መምከን አይደለም ወይ? ይሄ የውርደት ውርደት አይደለም ወይ?!!! እናንት በክርስቶስ ያላችሁ የሀገሬ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ክርስትያኖች ወንድሞቼና እህቶቼ – ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላላችሁ? እኔ – በዚሁ አበቃሁ!!
የጌታችን፣ የመድኃኒታችን፣ የጌታ እየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና ፀጋ – ከሁላችን ጋር ይሁን!
ፈጣሪ አምላክ – ለኢትዮጵያውያን ሁሉ – ከጫፍ ጫፍ – የቅንነትን እና የፈጠራን ኃይል፣ የጥበብንና የመስጠትን ጸጋ – አብዝቶ ያላብሰን!
የጥበብ እናት ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም ትኑር!!
Filed in: Amharic