>

ሳልሣዊ ኢሕአዴግ! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

ሳልሣዊ ኢሕአዴግ!

 

በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) “ጠርዝ ላይ” የሚል ርዕስ በሰጡት መጽሐፋቸው ‘ቀዳማዊ ኢሕአዴግ’ እና ‘ዳግማዊ ኢሕአዴግ’ የሚል መለያ ተጠቅመው ነበር። አሁን ኢሕአዴግ ብልፅግና ፓርቲ ሆኖ ከመጣም በኋላ ደግሞ ኢሕአዴግ በሚለው የቀድሞው ሥሙ እየጠሩት መቆየት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፤ ምክንያታቸውም የሥም ለውጥ ብቻ ነው። ብዙዎች “the more things change, they remain the same” የሚል የእንግሊዝኛ ተረት መተረት አብዝተዋል። ይሄ ወዴት ያመጣናል? ወደ ሳልሣዊ ኢሕአዴግ!
ዳግማዊ ኢሕአዴግ ቀዳማዊ ኢሕአዴግ የሠራቸውን ጥፋቶች በማረም ተቀባይነት ለማግኘት ሞክሯል። የፖለቲካ እስረኞችን ፈትቷል፣ የሕግ ማሻሻያዎችን አድርጓል፣ ሰዎች ሳይፈሩ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አድርጓል፣ የአደባባይ ሰልፎችን ፈቅዷል። ወዘተ… ዳግማዊ ኢሕአዴግ ሥልጣኑ እየተደላደለ ሲመጣ ግን ወደ ቀደመ ግብሩ የተመለሰ የሚያስመስሉትን ሥራዎች ሠርቷል። የፖለቲካ እስሮች፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን መገደብ፣ መረጃ ማፈን፣ የመሰብሰብ መብቶችን ለማደናቀፍ የተደራጁ ቡድኖችን በቸልታ ማለፍ (ቀጥሮ ማሠማራትም ሊባል ይችላል)፣ ወዘተ. ይኼ ሁሉ ሲሆን ግን ብዙዎቻችን ለውጡን እመራዋለሁ ላለው ቡድን Benefit of the doubt ስንሰጠው ከርመናል። ሳልሣዊ ኢሕአዴግ ሲወለድ ግን ነገሮች ፍንትው እያሉ መጡ፤ በበኩሌ ቀድሜ እንደ ፈራሁት እና እንደገለጽኩትም “የለውጥ ኀይሉ” ሥልጣኑን እያደላደለ በመጣ ቁጥር ለለውጥ ያለው ፍላጎት እየተዳፈነ መጥቷል። ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣም የዴሞክራሲ ፍላጉት ጭራሽ እንደሌለው እንደሚያሳየን ከአሁኑ ምልክቶች እየታዩ ነው።
ብልፅግና ፓርቲ ሳልሣዊ ኢሕአዴግ ነው። ርዕዮተ ዓለሙ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እምነት ነው። እምነታቸው ደግሞ የሚገለጸው ባብዛኛው መደመር በሚለው መጽሐፍ ላይ ተገልጿል። መደመር መጽሐፍ ሲመረቅ ጀምሮ ነው መንግሥታዊ ሀጢያቱ የተጀመረው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጽሐፍ ምረቃቸው ለባዛር ሚሌኒየም የተሰበሰቡ ድርጅቶችን አስወጥተዋል። የመንግሥት መዋቅሮች መደመርን ለማስተዋወቅ እና ለማሻሻጥ ውለዋል። ሳልሣዊ ኢሕአዴግ ከተመሠረተም በኋላ የመንግሥት መዋቅሮች ለፓርቲ አባላት ሥልጠና ውለዋል። በመንግሥት እና በፓርቲው መካከል ያለው ጋብቻ በዳግማዊ ኢሕአዴግ ግዜ ከፈረሰ በኋላ በሳልሣዊ ኢሕአዴግ ግዚ ቅልጥ ባለ ሠርግ ዳግም ታውጇል። ከሁሉም አሳፋሪው እና ትልቁ ቅሌት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዴሞክራሲ መርሖዎች ቅንጣት ታክል ደንታ እንደማይሰጣቸው ያሳዩበት ግን (በብልፅግና ፓርቲ ከተለጠፈው ምሥል አይቼ እንደተረዳሁት) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የፓርቲ አባላትን ሥልጠና ለመስጠት አባሎቻቸውን ሲሰበስቡ ነው። ግብዓተ መሬት ዘ ለውጥ!!!
Filed in: Amharic