>

የዓባይ ነገር....! (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

የዓባይ ነገር…

 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም

ዝም ማለት አቃተኝ፤ ዱሮም ቢሆን የአባይ ነገር ያንገበግባል፤ በቅርቡ እንኳን ሁለት ማዶ ለማዶ የሚተያዩ ንጉሦች (ምኒልክና ተክለ ሃይማኖት) ተፋልመውበታል፤ ዓባይ ውስጥ ሃይማኖት ገብቶበት ኢትዮጵያንና ግብጽን ጦር ለማማዘዝ ሲሞከርበት ነበር፤ በቅርቡም ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ አንድ በርሚል ውሀ በአንድ በርሚል ዘይት እንለውጣለን እያለ ሲፎክር ነበር፤ዓባይ ዝም ብሎ ይዥጎደጎዳል! አንዱ የዘንድሮ ምሁርም በቴሌቪዥን ዓባይ ማለት ውሸታም ማለት ነው ሲል በድንጋጤ ሰማን!

ዛሬ በአባይ ጉዳይ የተፋጠጡ አገሮች ኢትዮጵያና ግብጽ ናቸው፤ በመጀመሪያው አጥር ውስጥ የከበቧቸው አገሮች አሜሪካ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራም ናቸው፤ ያደፈጡ አገሮችም በዙሪያቸው አሉ፡– ሩስያ፣ ሳዑዲ አረብያ፣ ፋርስ፣ ቱርክ፣ ትንሽ ራቅ ቢልም ፓኪስታን፤ ከሁሉም በላይ ወሳኝነት ያላት ቻይና አለች፡፡

የትናንት ወዳጅ ዛሬ ጠላት ወይም የጠላት ወዳጅ ይሆናል፡፡

በቲቪ የምሰማቸው ሁሉ ጥሩ ጠጅ የጠጡ ይመስላሉ፤ አገርን ከጦርነት ጥፋት ማዳን ኢትዮጵያዊነት የማይመስላቸው ብዙ ሰዎች ያሉ ይመስለኛል፤ ኤርትራ ጋር ለመዋጋት ብዙ ቀረርቶ ሰምተናል፤ ያንን የጦርነት ጥሪ በመቃወም ብቻዬን ነበርሁ፤ ያንን ጦርነት ለማበረታታት አንድ መቶ ሺህ ዶላር የለገሱ (!) ስደተኞች ነበሩ፤ ያ ገንዘብ ለሞቱት ቀብር እንኳን አይበቃም ነበር፤ የሞቱት የወደቁበትን አፈር ቅመው ቀርተዋል፤ ልጆቻቸው በኑሮ እየተገረፉ ነው፤ ክብራቸውን ጥለው ደሀነትን የሸሹ ስደተኞች ዛሬ ክብር ወይም ደሀነት! የሚል መፈክር ይዘው በአሜሪካ ምድር አደባባይ ወጥተው ነበር፤ እንደሚገባኝ ክብር ለነሱ፣ ደሀነት ለኛ ምድራችን ላይ ላለነው ማለታቸው ነው፤ እነሱ በአሜሪካ ያጡትን ክብር እኛ ገና አላጣነውም፤ እነሱ በአሜሪካ ያገኙትን ገና ያልገባቸውን ደሀነት እኛ አንፈልገውም፡፡
ኢትዮጵያውያን ከግብጻውያን ጋር ሆነው ስለዓባይና ሌሎች ድንበር-ዘለል ወንዞች ያሉትን ዓለም-አቀፍ ሕጎች በማክበር ሕዝቦቻቸውን ከጥፋት ለማዳን ይችላሉ፤ ዓለም-አቀፍ ሕግን ለመርገጥ በተለያየ መልኩ ዓለም-አቀፍ ጡንቻ ያስፈልጋል፤ የዓባይ ውሀ ሌላ ግብጽም ብትፈጠር የሚበቃ ይመስለኛል፡፡

Filed in: Amharic