>

ዛሬን በቃሊቲ - ከእስረኛው ጋዜጠኛ ጋር ..... (ኤልያስ ገብሩ) 

ዛሬን በቃሊቲ – ከእስረኛው ጋዜጠኛ ጋር …..

ኤልያስ ገብሩ 

“የታሰርኩት በግፍ ነው፣ የግፍ እስረኛ ነኝ ብዬ አምናለሁ። አንደኛዬን በትናንቱ በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን ብታሰር ይሻለኝ ነበር። ትናንት ዜጎችን ሲያስሩ፣ ሲያሳስሩ፣ ሲያሰቃዩ፣ ሃገር ሲዘርፋ የነበሩ ተፈትተው እኔ እዚህ በመገኘት አፍሬያለሁ። ለውጥ አይተናል ባልንበት ዘመን በመታሰሬ የምር አዝኛለሁ።”
 – ፍቃዱ ማህተመወርቅ /የግዮን መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር/
——-
ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ዛሬም ዘርፈ ብዙ መከራን ይዛለች። ጣጣዋም አልተቋጨ።  አንዱ መከራና ጣጣዋ ፓለቲካ ወለድ እስር ነው። የፓለቲካና የህሊና እስረኞችን በህዝብ – ወለድ አንጻራዊ ለውጥ ሳቢያ፣ አንመለከትም ብለን አስበን ነበር። ግን አልሆነም። ዛሬም አለ።
ቢያስን ቢያንስ፣ የፓለቲካ ወለድ የእስር መስመር በአሁን ወቅት መዘጋት ነበረበት። ግን አልሆነም፣ አልተዘጋም፣ ዛሬም አለ – ቁጥሩ ቢቀንስም።
በዚህ አረዳድ፣ የጊዮን መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍቃዱ ማህተመወርቅን አንዱ ሰለባ ነው።
ፍቃዱን ዛሬ ጠዋት እኔ፣ እስክንድር ነጋና በሃይሉ ግርማ ቂሊንጦ እስር ቤት በማምራት ጠይቀነው ተመልሰናል።
ለዓመታት በፓለቲካ ወለድ እስር ላይ የነበረው እስክንድር ነጋ፣ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም ከእስር ከተፈታ በኅላ፣ ቃሊቲ እስር ቤት ሲመጣ ዛሬ የመጀመሪያው ነው። ተጠያቂ የነበረ ዛሬ ጠያቂ ሆኗል። ለዓመታት በጥብቅ የእስር ቤት ስፍራ ከሌሎች የተመረጡ የፓለቲካ እና የህሊና እስረኞች ጋር ለውስን ደቂቃዎች እስክንድርን ይጠብቁ የነበሩ በርካታ የጥበቃ ባለሞያዎች እስክንድርን ሲያዩት፣ ድንጋጤ እና ግርምት ተፈጥሮባቸው አይቻለሁ። በትልቅ አክብሮት ሲያናግሩት፣ ሊያናግሩት ሲንቀሳቀሱና እጁን ይዘው ጭምር ለደቂቃዎች በትህትና ሲያናግሩት ተመልክቼ ታዝቤያለሁ። በቻሉት ሁሉ ሊንከባከቡት ሲጥሩ ጭምር። እስክንድርም በቅንነትና በትህትና በፈገግታ ጭምር ሁሉንም አናግሯቸዋል። ለበዳይ መሰል አጸፋ አለመመለስ ታላቅነት ይመስለኛል።
እኛም (ጠያቂዎች) ያኔ፣ እነ እስክንድርን (አንዷለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ እማዋይሽ ዓለሙ፣ ሂሩት ክፍሌ፣ …..) ለመጠየቅ ስንሄድ እኚሁ የቃሊቲ ጥበቃ አባላት ላይ ይታይ የነበረው እብሪት፣ ትዕቢት፣ የቁጣ ቃላት፣ የበታችነት ስሜት የወለደው የ”በላይነት” ስሜት ….ደስ የማያሉና የማያስከብሩ ተግባራትን መለስ ብዬ በትውስታ አስቤ ‘አይ የሰው እስስታዊ ባህሪ’ ብያለሁ – በውስጤም ታዝቤያቸዋለሁ! የባህሪ ለውጣቸው ከልብ ከሆነ ደግ፣ መልካም ….
በእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተፈትሸን ከገባን በኅላም “በቃሊቲ ከተጠያቂነት ወደጠያቂነት ስትመጣ ምን ተሰማህ? ብዬም እስክንድርን ጠየኩት። እስኬውም እንዲህ ሲል መለሰልኝ:-
“በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በሚኖሩና በምንኖር ኢትዮጵያውያን ለዓመታት በተደረገ ህዝባዊ ትግል፣ አንጻራዊ ለውጥ መጥቶ ከእስር ወጥቻለሁ። ከእስር ስለወጣሁም ይኸው አሁን ለዓመታት በግፍ በታሰርኩበት ቦታ እስረኛን ለመጠየቅ መጥቻለሁ። የፍቄ እስር፣ ለውጡ የሽግግር ሳይሆን የሽግሽግ ለመሆኑ አስረጅ ነው። በዚህ ረገድ ገና ብዙ ትግል እንደሚጠብቀንም ያመለክታል።”
….እስክንድር እየተረመደ በአግራሞት ቃሊቲን በትውስታ ስሜት ውስጥ ገብቶ ብዙ ነገሮችን በማየት ይቃኝ ጀመር። “አከባቢው እምብዛም የተለወጠ ነገር የለውም” አለ። እውነቱን ነውና ያኔ ለዓመታት የማውቀው የዞን ሁለት መጠየቂያ ስፍራ ለውጥ የለውም። ያው እንደነበረ …..
 አስታውሳለሁ፣ ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል ወደአሜሪካ ከማቅናቷ በፊት በተለይ ከአቤል ዓለማየሁ ጋር ለጥየቃ ቃሊቲ ስንመጣ፣ ከልጃቸው ናፍቆት ጋር ተመላልሳ ትጠቅየው ነበርና በጥየቃ ቦታ እንገናኝ ነበር። አሁን 14 ዓመት የሆነው ልጃቸው ናፍቆት፣ ያን ጊዜ ገና አዳጊ ልጅ ነበር። በቃሊቲ የሽቦ መጠየቂያ ውስጥ ሲያስቸግር ትዝ ይለኛል። ተመስገን ያ ጊዜ አለፈ። እውነተኛ ስሜቱ የሚገባው በመከራ ዓመታት በውስጡ ላለፋበት ነው ብዬ አምናለሁ።
……
….ፍቄንም አስጠራነው። ጠባቂ ፓሊሱ “እኔ ጋር ሆናችሁ አናግሩት” አለን። እኛም ክፍት _ቦታ ፈልገን ጠበቅነው። ከ10 ደቂቃ በኅላ ፍቃዱ መጣ። ያኔእነእስክንድርን፣ አንዷለም አራጌን የምንጠይቅበት ቦታ ላይ። በትውስታ መገረሜ አልቀረም።
ፍቄ፣  ስቆ ሰላም አለን። እኛም አጸፋውን መልሰን ጨዋታ ልንጀር ስንል ….የእስር ቤቱ ፓሊሶች፣ “እዚህ ጋር ኑ” በማለት ንግግራችንን አቋረጡ። ግልባጩ የምትነጋገሩትን መስማት አለብን መሆኑ ነው። ገርሞን ተሳሳቅን። ሄድን። ለምን? አልናቸው። ‘እዚህ ጋር ክፍት ነው ብለን ነው” አለ አንዱ ፓሊስ፣ እያፈረ ጭምር። ፍቃዱ መሰል ነገር ገጥሞት እንደማያውቅ ገለጸ።
እስክንድርም፣ “ለውጥ አለ በሚባልበት፣እናንተም በምትሉበት በዚህ ጊዜ፣ እንዴት እኛ ላይ በፊት የምታደርጉትን ዛሬም ትደግሙታላችሁ?! ያሳዝናል” በማለት በግልጽ ነገራቸው። አንዱ ፓሊስ ‘ከላይ ታዝዘን ነው” ሲል በለሆሳሳ ድምጽ ተናገረ። እስክንድርም፣ “ለአለቆቻችሁ ንገሯቸው፣ ትናንት ሲደረግ የከረመ፣ ዛሬም መደገም የለበትም”። ፓሊሶቹ ግን ጆሯቸውን ቀስረው ማድመጣቸውን ቀጠሉ …..
….ከፍቄ ጋር:- ስለክሱ፣ ስለፍርዱ፣ ስል እስር ሁኔታ፣ ስለጤናው ….ወዘተ ጠይቀነው አወጋን። በፊት ይገባለት የነበሩ መጽሄቶች አሁን ተከልክለዋል። ህክምና በአግባቡ እንደማያገኝና የህክምና ችግር መኖሩንም ገለጸልን።
እስሩንም አስመልክቶ በእውነት እንዲህ ብሎናል:-
የታሰርኩት በግፍ ነው። የግፍ እስረኛ ነኝ ብዬ አምናለሁ። አንደኛዬን በትናንቱ በህወሃት ዘመን ብታሰር ይሻለኝ ነበር። ትናንት ዜጎችን ሲያስሩ፣ ሲያሳስሩ፣ ሲያሰቃዩ፣ ሀገር ሲዘርፏ የነበሩ ጭምር ከእስር ተፈትትተው እኔ እዚህ በመገኘቴ አፍሬያለሁ። ‘ለውጥ አይተናል’ ባልንበት ዘመን በመታሰሬም የምር አዝኛለሁ።”
ፍቄን የቤተሰቡ አካላት፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ (የቀድሞ ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ)ና ግርማ ተስፋው (የቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ) ሊጠይቁት ስለመጡ ጠባቡን ቦታ ሰላምታ ተለዋውጠን ለቀቅንላቸው። ፍቄን “አይዞህ፣ በርታ። የምትፈታበት ጊዜ ቅርብ ነው” በማለት እጁን በሽቦ መሃል ጨብጠን ተለየነው። ትንሽ እንደሄድንም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝና ግርማ ሰይፋን አገኝናቸው። ሰላምታ ተለዋውጠን ቃሊቲን ለቅቀን ወጣን።
ፍቃዱ ማህተመወርቅ (ጋዜጠኛ)፣ የህወሃት/ ኢህአዴግ የፓለቲካ ጦስ እስረኛ ነውና ፍትህ እንላለን። በእስር ትርፍ የለም። ህወሃትም ከስሮ የሀገር ውስጥ ስደተኛ ሆኗል። ከህወሃት ውድቀት ትምህርት ውሰዱ።
[መብራት በሌለበት የተጻፈ ነው።]
Filed in: Amharic