>

የአልጄዚራው ጋዜጠኛ ሞሐመድ ቫል ስለ አባይ ግድብ ይህን ብሏል (ሄቨን ዮሀንስ)

የአልጄዚራው ጋዜጠኛ ሞሐመድ ቫል ስለ አባይ ግድብ ይህን ብሏል

ሄቨን ዮሀንስ
 
 ‹‹ምናልባትም በትዕግስት ለዘመናት የጠበቁት ኢትዮጵያውያን ከዓባይ ወንዝ የትዕግስታቸውን ጥፍጥና የሚቀምሱበት ጊዜ ሩቅ አይሆን ይሆናል፡፡›› 
– በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ዛሬን በትናንት ሚዛን እየለኩ ኢትዮጵያን ለመሞገት የሚሞክሩ ሁሉ ሁለት የዘነጓቸው ነጥቦች አሉ!!!
ጋዜጠኛ ሙሐመድ ቫል
..
የመጀመሪያው ጉዳይ በኢትዮጵያ ዓይናቸውን በእንጨት ጭስ እያጨናበሱ እና እያለቀሱ በትዕግስት የሚጠብቁ እናቶች መኖራቸውን መዘንጋታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግድብ ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ በዚህ በሰለጠነ ዘመን ዳገት ወጥተው እና ቁልቁለትን ወርደው ሕይወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ጭራሮ ለቅመው እንጨት ሰብረው በእሳት ጭስ እየተፈተኑ ‹‹እራት እና መብራት›› የሚሹ እናቶች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡
ሁለተኛው እና ከዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ይህ ትውልድ ለአፍታ ሊደራደርበት የማይፈልገው ጉዳይ ደግሞ ግድቡ የእያንዳንዱን ድሀ ኢትዮጵያዊ ኪስ እና መቀነት ነክቷል፡፡ ግድቡ በብድር ወይም በምዕራባውያን ልግስና የሚገነባ ሳይሆን ነገን ተስፋ አድርጎ ከዛሬ ጠኔ ጋር ትግል በገጠመ ድሀ ኢትዮጵያዊ አንጡራ ሀብት ነው፡፡ ከወታደር እስከ አርሶ አደር፣ ከተማሪ እስከ አስተማሪ፣ ከቀን ሠራተኛ እስከ ጡረተኛ፣ ከሕጻናት እስከ አዛውንት፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ዛሬውን እየቀጣ ነገን የተሻለ ለማድረግ አዋጥቷል፤ ኖሮት ሳይሆን ሳይኖረው አምስት አስር ተሰብስቦ እየተገነባ ያለ ግድብ መሆኑን ማስታወስ ቀርቶ ማሰብ የሚፈልጉ አይመስሉም፤ የወቅቱ አደራዳሪዎች ወይም ሞጋቾች፡፡
ከሰሞኑ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው ግድብ አካባቢ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተዘዋውሮ የተመለከተው የአልጀዚራው ጋዜጠኛ ሙሐመድ ቫል የአገሬዎቹን ኑሮ ተመልክቶ ‹‹አሁንም ኋላቀር በሆነ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ የሚኖሩ›› ሲል ይገልፃቸዋል፡፡ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ምቹ የመኖሪያ ቤት የሌላቸው ሕዝቦች፤ ከዚህ አስከፊ የኑሮ ምስቅልቅል ለመውጣት ግድቡን በትዕግስት ይጠብቃሉ፡፡ የትዕግስታቸውን ልክና ወሰንም ‹‹ከአዕምሮ በላይ›› ሲል ይገልጸዋል፡፡
የግድቡን አጠቃላይ ሂደት የመጎብኘት ዕድል ያገኘው ጋዜጠኛ ሙሐመድ ቫል የነዋሪዎቹን ትዕግስት ከግድቡ ሠራተኞች የቀን ከሌት ጥረት ጋር አስናስሎም አንድ ፕሮጀክት ለመጨረስ የሚተጉ ሳይሆን ወገኖቻቸውን ከጨለማ ዘመን ለማሻገር የሚታትሩ መሲሆች ያደርጋቸዋል፡፡ ግድቡ ሦስት የተለያዩ የግንባታ ክፍሎች አሉት፡፡
የእያንዳንዱ ግድብ አፈፃፀም የተለያየ ቢሆንም አጠቃላይ ግንባታው 71 ነጥብ 2 በመቶ መጠናቀቁን ያትታል ጋዜጠኛው፡፡
ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ በውኃ ሲሞላ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ጋዜጠኛ ሙሐመድ ቫል በዘገባው እንደሚለው ይህም ኢትዮጵያ የእነዚያን ታጋሽ ዜጎቿን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለሰባት የአፍሪካ እና ምዕራብ አውሮፓ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ የማቅረብ አቅም ይኖራታል፡፡ “ከኃይል አቅርቦት ባለፈም የሀገሪቱ መፃኢ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ተስፋ ከተጣለባቸው ምሰሶዎች አንዱ ነው” ሲል ዘርፈ ብዙ አስፈላጊነቱን ያትታል ሙሐመድ ቫል በዘገባው።
ከዓባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት አንዷ የሆነችው ሱዳን ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ የሚያደርስባት ጉዳት አለመኖሩ በባለሙያዎች መረጋገጡን ያወሳል፡፡ ነገር ግን አቋሟ ወጥ አለመሆኑን የሚናገረው የአልጀዚራው ጋዜጠኛ ግብጽን ግን አሁንም የዓባይ ወንዝ ታሪካዊ እና ብቸኛ ተጠቃሚ አድርጋ እንደምትመለከት ያትታል፡፡ ግብጽ ሄሮዳተስ ‹‹የዓባይ ስጦታ ናት›› ትርክት አልወጣችም የሚለው ሙሐመድ ቫል አሁን እንኳን ዘመንን የዋጀ ምክንያት ማቅረብ እንደተሳናት ያብራራል፡፡የግድቡ አጠቃላይ ቅርፅ መልክ እየያዘ ባለበት በዚህ ወቅት ከሚቀጥለው ክረምት ጀምሮ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ 74 ቢሊዮን ኪዩ ቢክ ሜትር ውኃ በግድቡ ለመሙላት ኢትዮጵያ ማቀዷን ዘገባው ያትታል፡፡
አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት በተሸጋገሩበት የሰሞኑ የዋሽንግተን ውይይት የግብጽ አንዱ መደራደሪያ የውኃው ሙሌት ጊዜ ከሦስት ዓመታት ወደ ሰባት ዓመታት ከፍ ይበል የሚል እንደሆነ ያወሳል፡፡በዚህ ሁሉ የነገሮች ዑደት ውስጥ ግን ይላል ጋዜጠኛው ለዘመናት ከማኅፀኗ እየፈሰሰ የሚነጉደው የዓባይ ወንዝ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠብታው የሚገታበት ጊዜ የተቃረበ ይመስላል፡፡
ዝነኛው የዓባይ ወንዝ ለሚሊዮን ዓመታት ከአብራኳ ለምታፈልቀው ሀገረ ኢትዮጵያ ሊገብር የተገደደበት ጊዜ መቃረቡ እውን ይመስላል፡፡ “ምናልባት በትዕግስት ለዘመናት የጠበቁት ኢትዮጵያውያን ከዓባይ ወንዝ የትዕግስታቸውን ጥፍጥና የሚቀምሱበት ጊዜ ሩቅ አይሆን ይሆናል” ይላል፡፡
Lovelew Beya Man ላቭሊው በያ ማን
Filed in: Amharic