ከዘመነ ኮህን ወደ ዘመነ መኑንሺን !!!
ዳንኤል ሙሉነህ
ዘመነ ኮህን እኤአ በ1991 በ ወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒቴር የአፍሪቃ ክፍል አለቃ በነበሩት በአቶ ሄርማን ኮህን በኢትዮጵያ ወታደራዊው መንግስት ላይ በጦር ሜዳ ድል የተቀዳጁት የህወሃትና የሕዝባዊ ግንባር እና ምንም አይነት አይነት ለድሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ባላበረከተው ነገር ግን በወቅቱ የጦር ክንፍ በነበረው ኦነግ ብቻ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት በሰጡት ቡራኬ ይጀመራል።
የዘመነ ኮህን ዋና መገለጫ የአትዮጵያና የኤርትራ በሁለት አገር መከፈልና የኢትዮጵያን በ9ኝ በቁዋንቁዋ ክልሎች መከፋፈል ሲሆኑ ሌሎች ደግና ክፉም ጎኖች ነበሩት። በደግ ጎኑ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የ ኢንፍራስተራክቸር ግንባታ፥ የትምህርትና፥ የጤና አገልግሉት መስፋፋት ያሳየችበት ወቅት ነው። በክፉ ጎኑ ቅጥ ያጣ የሕዝብ እድገት፥ አይን ያወጣ የጎሳ አድልዎና በደል የየበዛበት ዘመን፥ የመንግስት ቁጥጥር እጅ ረዝሞ፥ ረዝሞ ቤተሰብ ደረጃ የወረደበት፥ ብዙ ሺህ ሕዝብ ለስደትና ለእስር የተዳረገበትና በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በተካሄዱ አላስፈላጊ ጦርነቶች በብዙ መቶ ሺህ የተማገዱበት ዘመን ነበር።
ያ ዘመን ለ27 አመት ሥልጣን ላይ የቆየው የህውሃት መንግስት ከሥልጣን መወገድ ጋር አክትሟል።
ዘመነ መኑንሺን ኢትዮጵያ በወንዝዋ ልዑላዊነት ላይ የአሜረካ ግምጃ ቤትና የዓለምን ባንክን የአባይን ግድብ አስመልክቶ ከግብጽ ጋር ለምታረገው ንግግር እንደ ታዛቢና አደራዳሪ በኖቬምበር 2019 ስትቀበል ይጀምራል።
ዘመነ መኑሺንና መከራችንን ልናረዝመውም ልናሳጥረውም የምንችለው እኛ ራሳችን ነን።
ግምጃ ቤቱና ባንኩ ድህነታችንን አይተው፥ አባይን አታለው ከእጃችን ለመንጠቅ የሸረቡትን ሴራ ያከሸፈው ሕዝባችን እና በንቃት የኢትዮጵያን ልዑላዊነት በመላው አለም የጠበቁት የኢትዮጵያ ምሁራን፥ ጋዜጠኞች፥ ወጣቶችና አክቲቪስቶች ናቸው።
በዚህ ወሳኝ የትግል ወቅት፥ የዐብይ አስተዳደርና ደጋፊ ፖለቲከኞቹ፥ ተከታይ እንጂ መሪዎች አልነበሩም። But that’s okay… ዋናው ነገር መደማመጣችን እና እርስ በርሳችን በድርድሩ ላይ አንድ አይነት አቁዋም መውሰዳችን ነው።
ለወደፊቱ ግን…
የመኑሺንን ዘመን ለማሳጠር የኢትዮጵያ መንግስት እሰካሁን በማን አለብኝነትና በንቀት ፥ የባለሙያዎችን አሳብ ወደ ጎን መጣሉንና የሕዝብን ስጋት ማጣጣሉን ማቆም አለበት። የምስጢራዊ ስምመነት የመፈራረም ባሕሉነም እርግፍ አርጎ መተው አለበት።
የጠቅላይ ሚኒስር ዐብይ አህመድ አስተዳደር፥ እርሳቸውም በአንድ ወቅት ለሕዝብ ለማስገንዘብ እንደሞከሩት፥ የሚመሩት መንግስት አሻጋሪ፥ ጊዜያዊ መንግስት ነው።
ጊዜያዊ መንግስት ደግሞ፥ ለኢትዮጵያ፥ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር ዘለቄታዊ ትርጉም ያለው ስምምነት ሊፈራረም ስልጣንም መብቱም የለውም።
የዐብይ አህመድ አስተዳደር ይህንን የስልነጣኑን ገደብና ውሱንነት ለሌለው ዓለም ሕዝብ ማሳወቁ አስፈላጊ ነው። ይህንን ቢያደርጉ፥ እሳቸውንም ወደ ሚፈልጉት የልማት ዘመቻ እንዲያተኩሩ ይረዳቸዋል፥ ልዑላዊነታችንን የሚዳፈረውን የመኑንሺን ዘመንንም በምንፈልገው መንገድ ለመሻገር ይረዳናል።